በመኮንን አለማው
በሦስት አገራት ማለትም በካናዳ ፣ በአሜሪካ እና በሜክሲኮ የሚካሔደው መጪው የ2026 ዓለም ዋንጫ እየተቃረበ ነው።
ይህ 48 ሀገራትን የሚያሳትፈው የዓለማችን ታላቁ የእግር ኳስ መድረክ ውድድር ከሰኔ 2026 አጋማሽ ጀምሮ በአምስት ሳምንታት ውስጥ ተከናውኖ ይጠናቀቃል።
ለዚህ ትልቅ ውድድርም IFAB በዳኝነቱ ላይ ትልቅ እገዛ ያደርጋሉ ያላቸውን አዳዲስ ህጎች በማውጣት ለህዝብ ይፋ አድርጓል።
በዚህ ከ IFAB በተሰጠው መግለጫ በዋናነትም በአለም ዋንጫው ላይ የሚተገበሩ አዳዲስና ጥብቅ የዳኝነት ህጎች ይፋ ተደርገዋል።
ከእነዚህ መካከል አፍን መሸፈን እና ሜዳ ጥሎ መውጣት በቀጥታ ቀይ ካርድ ያሰጣሉ ተብሏል።
ይህ ህግ የወጣው በቅርቡ የተከሰቱ ጉዳዮች ተመርኩዞ ነው።
ለማስታወስ ያህል ሞሮኮ ከሴኔጋል ባደረጉት የአፍሪካ ዋንጫ ፍፃሜ ጨዋታ ላይ በዳኝነት ስርዓቱ ላይ ደስተኛ ያልነበሩት ሴኔጋሎች ሜዳ ለቀው ወጠው እንደነበረ ይታወሳል።
በኋላም በቡድኑ አምበል ሳዲዮ ማኔ አማካኝነት ወደሜዳ የተመለሱት የቴራንጋ አምበሶቹ ዋንጫውን ወደ ሴኔጋል መውሰዳቸው ይታወሳል።
ይሁን እንጂ ከቀናት በኋላ በተወሰነ የካፍ ውሳኔ መሠረት የሴኔጋል ተጫዋቾች በጨዋታው ወቅት ሜዳ ጥለው በመውጣታቸው ዋንጫውን ለሞሮኮ እንዲመልሱ ተጠይቀዋል።
ሆኖም ሴኔጋል ጉዳዩን ወደ አለም አቀፉ የስፖርት ፍርድ ቤት የወሰደው ሲሆን እስካሁንም መቋጫ አልተገኘለትም።
ታዲያ ይህንን አነጋጋሪ ችግር የፈጠረው ሜዳ ለቆ የመውጣት ጉዳ በአለም ዋንጫው ላይ ከመቅፅበት የማያዳግም እርምጃ እንደሚወሰድበት ይፋ ተደርጓል።
ሌላው ደግሞ በቅርቡ የቤኔፊካው ተጨዋች ጂያንሉክ ፕሬስቲያኒ ቪንሰስ ጁኒየር ላይ የዘረኝነት ጥቃት የሰነዘረበት መንገድ በአለም ዋንጫው ላይ አዲስ ህግ እንዲወጣ አስገድዷል።

አርጀንቲናዊው ጂያንሉክ ፕሬስቲያኒ አፉን በማልያው በመሸፈን እና ከካሜራ እይታ በመደበቅ ቪኒሽየስን ጁኒየር ላይ የዘረኝነት ጥቃት አድርሶ ነበር።
በዚህም ፊፋ ጉዳዩን በወቅቱ መርምሮ ተጨዋቹ ላይ የስድስት ጨዋታዎች ቅጣት መጣሉ ይታወሳል።
ከዚያ በኋላ ፊፋ ለዩኤፋ ቅጣቱ በአለምአቀፍ ደረጃ ተፈፃሚ እንዲሆን ያቀረበውን ጥያቄ መቀበሉ ተገልጿል።
ይህንንም ተከትሎ ጂያንሉክ ፕሬስቲያኒ ለአርጀንቲና ጥሪ የቀረበለት ሲሆን ነገር ግን ሁለት የመጀመሪያ የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ያመልጡታል።
አርጀንቲና በዓለም ዋንጫው መክፈቻ ከአልጄሪያ እና አውስትራሊያ ጋር ትጫወታለች።
ይህንን ተከትሎ የፊፋ የዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ ፒየርሉኢጂ ኮሊና እግር ኳስን ተገቢ ካልሆኑ አከራካሪ እና አነታራኪ እንዲሁም የዳኝነት ስርዓቱን ከሚፈታተኑ ውስብስብ ችግሮች ለማጽዳት ያለመውን እና በመጭው የአለም ዋንጫ ላይ የሚተገበሩ አዳዲስና ጥብቅ የህግ ማሻሻያዎች ይፋ አድርገዋል።
ኮሊና ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ “ጨዋታውን በተቻለ መጠን ለማጽዳት እየጣርን ነው” ያሉ ሲሆን በዚህም በውድድሩ ላይ የሚተገበሩት ዋና ዋና የህግ ለውጦችን በሰፊው እንመልከት።
በፀብ እና ጭቅጭቅ ወቅት አፍን መሸፈን ቀይ ካርድ በቀጥታ ያሰጣል።
ተጫዋቾች ሜዳ ውስጥ በሚፈጠሩ አለመግባባቶች ወቅት ስድብ ወይም ያልተገቡ ቃላትን ተናግረው በካሜራና በዳኞች እንዳይያዙ አፋቸውን በእጃቸው ወይም በጀርሲያቸው ሸፍነው ከተገኙ በቀጥታ በቀይ ካርድ ከሜዳ ይሰናበታሉ።
በዳኛ ውሳኔ ቅር በመሰኘት በተቃውሞ ሜዳውን ጥሎ የሚወጣ ተጫዋች ወይም ተጫዋቾች እንዲወጡ የሚያደርግ የአሰልጣኞች ቡድን አባል በቀጥታ ቀይ ካርድ ይመለከታል።
በተጨማሪም በዚህ የዓለም ዋንጫ ውድድር ላይ የVAR አዲስ ሚና ይፋ ተደርጓል።
ከዚህ ቀደም የተለመደው አሰራር ተቀይሮ ዳኞች በስህተት የሰጧቸውን የማዕዘን ምቶች በቪዲዮ እገዛ ውሳኔውን መሻርና መቀልበስ ይችላሉ።
የውሃ እረፍት እና የህክምና ህግ ጉዳይም በአለም ዋንጫው ውድድር ላይ አዲስ ትኩረት ተሰጥቶበታል።
ጨዋታ እንዳይዘገይ በሜዳ ላይ የሚደረጉ የህክምና እርዳታ ህጎች የተሻሻሉ ሲሆን በእያንዳንዱ አጋማሽ 22ኛው ደቂቃ ላይ ለ3 ደቂቃ የሚቆይ አጭር የውሃ እረፍት ይደረጋል።
ይህንን ህግም የፊፋ የዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ ፒየርሉኢጂ ኮሊና በበላይነት ይመሩታል።
ይህንን አዲስ አሰራር በበላይነት እየመሩ በውድድሩ የሚሳተፉ 170 የዳኝነት አካላትን በማያሚ የመጨረሻው የዝግጅት ወቅት ሴሚናር ያደርጋሉ።
በውድድሩ ላይ ለሚሳተፉ 48ቱም ብሔራዊ ቡድኖች አሰልጣኞች በወርክሾፕ ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት ለእያንዳንዱ ተጫዋች ተመሳሳይ ገለጻ ይደረጋል።
በተጨማሪም የትኛው የእጅ ንክኪ ፍጹም ቅጣት ምት እንደሚያሰጥ ተጫዋቾችና አሰልጣኞች ግልጽ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ሁሉንም አይነት ሁኔታዎች ያካተቱ የቪዲዮ ክሊፖች ተዘጋጅተዋል።
ቢሆንም ግን ኮሊና በዳኞች መካከል የትርጉም ልዩነቶች ሊኖሩ ስለሚችሉ ይህ የቪዲዮ ማብራሪያ መቶ በመቶ ፍፁም ምላሽ ላይሰጥ እንደሚችል አምነዋል።