ዋሽንግተን በአፍሪካ የሚገኙትንና የቪዛ ማመልከቻዎችን የሚያስተናግዱ ዲፕሎማሲያዊ ኤምባሲዎች በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ እየተዘጋጀች መሆኑን ተሰምቷል።
የአሜሪካ መንግሥት ወደ ሀገሪቱ ለመግባት ቪዛ ለሚጠይቁ በሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን አዲስ የስደት ቁጥጥር ማሻሻያ ይፋ አድርጓል፡፡ ኢትዮጵያ ግን ከዚህ ማሻሻያ ውጭ ሆናለች፡፡
በዚህ በሳምንታት ውስጥ ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ በሚጠበቀው አዲስ መዋቅራዊ ለውጥ መሠረት ቀደም ሲል በአህጉሪቱ የቪዛ ማመልከቻዎችን ሲያስተናግዱ የነበሩት የኤምባሲዎች ቁጥር ከ50 ወደ 20 ዝቅ እንዲል ይደረጋል።
ከነዚህ ሀገራት መካከል ግብፅ እና ሱዳን በዚህ የቪዛ አገልግሎት ቅነሳ የተካተቱ ውስጥ የተካተቱ መሆናቸው ታውቋል፡፡
ይህ የአሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ አሠራር ለውጥ በተለይም የቪዛ አገልግሎት በአገር ውስጥ በሚቋረጥባቸው የአፍሪካ ሀገራት ለሚኖሩ አመልካቾች ወደ አሜሪካ የመጓዝ ዕድላቸውን በእጅጉ እንደሚቀይረውና የጉዞ ሁኔታዎችን እንደሚያጠብበው ይጠበቃል።
በተጨማሪም እርምጃው የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የስደተኞች ቁጥጥርን ይበልጥ ለማጥበቅ እና የቪዛ ማጣሪያ ሂደቶችን ለማጠናከር ከያዘው ሰፊ ዕቅድ አካል አንዱ ነው ተብሏል።
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ አዲሱ የቪዛ መገደብ ፖሊሲ ሳያገኛት ሙሉ የቪዛ አገልግሎት የመስጠት አቅሟን ይዛ እንድትቀጥል ከተመረጡት 20 የአፍሪካ ከተሞች መካከል አንዷ ሆናለች።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ያፀደቁት ይህ መመሪያ በይፋ የሚጀመርበት ቀን ባይገለጽም የሽግግር ሂደቱ በዚሁ በሰኔ ወር ውስጥ እንደሚጀምር ለዲፕሎማቶች ባለፈው ዓርብ በተደረገ የውስጥ የስልክ ጥሪ ተነግሯቸዋል ተብሏል።
የአሜሪካ መንግሥት የቪዛ ማረጋገጫዎችን በጥቂት ማዕከላት ላይ ብቻ ማሰባሰቡ የደኅንነት ፍተሻውን ጥራት ለማሻሻልና የአሜሪካን ብሔራዊ ጥቅሞች ለማስከበር ይረዳል ባይ ነው።
ሆኖም የቪዛ አገልግሎት ከሚቋረጥባቸው ሀገራት የሚነሱ ተማሪዎች፣ ቱሪስቶች፣ የንግድ ተጓዦች እና ስደተኞች ቪዛ ለማግኘት ድንበር አቋርጠው ወደተመረጡት 20 ክልላዊ ማዕከላት ለመጓዝ ስለሚገደዱ ይህ ውሳኔ ተጨማሪ ወጪን፣ የጊዜ መስተጓጎልንና የእንቅስቃሴ ፈተናን ያስከትላል ተብሎ ተሰግቷል።
የቪዛ አገልግሎት የሚቀነስባቸው ኤምባሲዎች ሙሉ በሙሉ ሳይዘጉ ለአሜሪካ ዜጎች የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍና የፓስፖርት አገልግሎት መስጠታቸውን የሚቀጥሉ ሲሆን በተጨማሪም የዲፕሎማቲክ ቪዛዎችንና ልዩ የሀገር ጥቅም ያለባቸውን ጉዳዮች ብቻ ያስተናግዳሉ።
በዚህም መሰረት ሙሉ የቪዛ ማስተናገድ አቅማቸውን ይዘው የሚቀጥሉት 20ዎቹ የአፍሪካ ከተሞች ውስጥ ኢትዮጵያ፣ ኮትዲቯር፣ ጋና፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሴኔጋል፣ ታንዛኒያ፣ ጅቡቲ፣ ኡጋንዳ እና ሩዋንዳ ተጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ናይጄሪያ፣ ቶጎ፣ አንጎላ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ላይቤሪያ፣ ኬንያ፣ ሞሪሸስ፣ ኬፕ ቨርዴ እና ካሜሩን ይገኙበታል።