Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ዜና

ኢትዮጵያ በጅቡቲ የነዳጅ ዴፖ ግንባታ ላይ ኢንቨስት ልታደርግ ነው

SM Samuel Mulgeta Jun 1, 2026 Updated 3h ago 2 ደቂቃ ንባብ 391 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
ኢትዮጵያ በጅቡቲ የነዳጅ ዴፖ ግንባታ ላይ ኢንቨስት ልታደርግ ነው

ለዚሁ ግንባታ የሚጣው ፈንድ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እንደሚሸፈንም ታውቋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በጂቡቲ ደቡብ ምስራቅ ክፍል በሚገኘው አዲሱ የዳመርጆግ ፈሳሽ ጭነት ወደብ ላይ ለሚገነባው መጠነ-ሰፊ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ዴፖ አስፈላጊውን የፋይናንስ መዋጮ በማድረግ ቀጥተኛ ተሳትፎ ሊያደርግ መሆኑ ተሰማ።


ይህ እርምጃ የኢትዮጵያን የነዳጅ አቅርቦት ዋስትና በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሳድገው ታምኖበታል።


በአሁኑ ወቅት ዘመናዊው የመርከብ ማቆሚያ ጄቲ ግንባታ በማጠናቀቂያ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የጂቡቲ ባለሥልጣናት አስታውቋል።


ተቋሙ ሥራ ከመጀመሩ በፊት ለሚገነባው የነዳጅ ማጠራቀሚያ የኢትዮጵያ መንግሥት በሚቀጥለው የበጀት ዓመት የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል ብሎ ይጠብቃል።


ለዚህም የአህጉሪቱ ግንባር ቀደም የሉዓላዊ ሀብት ፈንድ ከሆነው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ጋር ውይይት እየተደረገ ሲሆን የገንዘብ ድጋፉ በቅርቡ ይረጋገጣል ተብሎ ይገመታል።


ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለኃይል አቅርቦት ፍጆታዋ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በዶራሌህ አቅራቢያ የሚገኘውን የሆራይዘን ጂቡቲ ተርሚናል ትጠቀማለች።


ይሁን እንጂ በዓመት 4.5 ሚሊዮን ቶን የመያዝ አቅም ያለው ይህ ነባር ተርሚናል በፍጥነት እያደገ የመጣውን የኢትዮጵያ የነዳጅ ፍላጎት ማሟላት አልቻለም።


በአንጻሩ አዲሱ የዳመርጆግ የነዳጅ ጄቲ በዓመት 25 ሚሊዮን ቶን የመያዝ አቅም የሚኖረው ሲሆን እስከ 12 የሚደርሱ የባሕር መርከቦችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ ይችላል።


ይህም በአጠቃላይ ወደ ሁለት ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የሚጠጋ የማጠራቀሚያ አቅም ስለሚኖረው እየሰፋ የመጣውን የኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦት ሎጂስቲክስ ችግር በዘላቂነት ይፈታል ተብሎ ይጠበቃል።


የኢትዮጵያን ስትራቴጂካዊ የነዳጅ ምርቶች በባቡር በፍጥነት ለማጓጓዝ እንዲቻል የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር አዲሱን የዳመርጆግ ነዳጅ ተርሚናል ከናጋድ የባቡር ጣቢያ ጋር የሚያገናኝ የ17 ኪሎ ሜትር መስመር ለመገንባት አቅዷል።


ይህ የባቡር መስመር ዝርጋታ 90 ሚሊዮን ዶላር ገደማ እንደሚፈጅ የተገመተ ሲሆን ቀጥታ የነዳጅ ትራንስፖርት ወደ ኢትዮጵያ ለመዘርጋት ወሳኝ ሚና ይጫወታል።


በተጨማሪም የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር  በዳመርጆግ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ፕሮጀክት ላይ ለጄት ነዳጅ አያያዝ የሚሆን መሠረተ ልማትን ጨምሮ  የ49 በመቶ ድርሻ ለመግዛት ፍላጎት እንዳለው ምንጮች ጠቁመዋል።


ይህ ታላቅ ዕቅድ በሁለት ምዕራፎች የተከፈለ ሲሆን የተጣራ የነዳጅ ምርቶችን ከጂቡቲ ወደብ ወደ ኢትዮጵያ የድንበር ከተማ ደወሌ በቧንቧ ማስገባት የመጀመርያው ነው።


ሁለተኛው ምዕራፍ  ደግሞ የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ጋዝ እና ድፍድፍ ዘይት በኦጋዴን ከሚገኙ የማውጫ ቦታዎች በጂቡቲ ኮሪደር በኩል ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ የሚያስችል የጋዝ እና የነዳጅ ቧንቧ መስመር መዘርጋት ናቸው።


ይህ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተጀመረው አዲስ የልማት ምዕራፍ፣ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ዕድገት ከማገዙም በላይ የኃይል አቅርቦት ዋስትናዋን በአስተማማኝ ሁኔታ እንደሚያረጋግጥ የዘርፉ ባለሙያዎች እየገለጹ ይገኛሉ።

SM
ስለ ጸሐፊው

Samuel Mulgeta

41 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።