በመኮንን አልማው!
የአለማችን ተወዳጁ እንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች በተለይም ታላላቆቹ በሙሉ በአርባዎቹ እድሜ ውስጥ ያሉ አሰልጣኞችን መቅጠራቸው ግርምትን ያጭራል።
አርሰናል ፣ ማንችስተር ሲቲ ፣ ማንችስተር ዩናይትድ ፣ ሊቨርፑል ፣ ቸልሲ እና ቶተናም ሆትስፐር የዚህ አካል ናቸው።
ሊጉ ከዚህ ቀደም እድሜ ጠገብ በሆኑት እንደ ፔፕ ጋርዲዮላ ፣ አርሰን ቪንገር ፣ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን እና ዥርገን ክሎፕ የመሳሰሉ አንጋፋ አሰልጣኞች ነበር የሚታወቀው።
ታዲያ ከቅርብ አመታት ወዲህ ግን ከ50 እና 60 አመት በላይ አሰልጣኞችን በዚህ ሊግ መመልከት እየቀረ መጥቷል።
ምናልባት በሊጉም ሆነ በመላው አውሮፓ ከፍተኛ ልምድ የነበራቸው ስፓኒያርዱ ታክቲሽያን አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላም ከቀናት በፊት ከክለባቸው ማንችስተር ሲቲ ጋር በመለያየት ሊጉን ተሰናብተዋል።
በተለይ በሊጉ ያሉ ለዋንጫ የሚጠበቁ እና በተለምዶ (BIG 6) የሚባሉት ክለቦች አሁን ላይ ምርጫቸውን ወጣት አሰልጣኝ እያደረጉ ነው።
ከሁለት አመት በፊት በተወዳጁ አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ ይመራው የነበረው ሊቨርፑል ዛሬ አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር ተስማምቷል።
ሊቨርፑል ክሎፕን አሰናብቶ አርኔ ስሎትን ከቀጠረጰበኋላ የሊጉ ሻምፒዮን ለመሆን በቅቶ ነበረ። ሆኖም አመራሮቹ ክለቡ በዚህ አመት ያሳለፈውን አስቸጋሪ ጊዜ በመገምገም ከቀናት በፊት አሰልጣኙን አሰናብተው ነበር።
ታዲያ ዛሬ በተሰማ ዜና የመርሲሳይዱ ክለብ ሊቨርፑል ጎልማሳውን አሰልጣኝ አንዶኒ ኢራኦላን ለመሾም ከስምምነት መድረሱ ተገልጿል።
የአሰልጣኝ አንዶኒ ኢራኦላን ቅጥር ንግግር የሊቨርፑል ስፖርቲንግ ዳይሬክተር ሪቻርድ ሂውዝ እየመሩት መሆኑ ተነግሯል።
የ 43ዓመቱ አሰልጣኝ አንዶኒ ኢራኦላ ሊቨርፑልን የመረከብ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ተገልጿል።
አንዶኒ ኢራኦላ በበርንማውዝ የሰሩት ነገር ሊቨርፑል ከሚፈልገው ጋር ይገጥማል የሚል እምነት አድሮባቸዋል ተብሏል።
የሊቨርፑል ሀላፊዎች በማጥቃት ላይ የተመሰረተ ጉልበት ያለው እና ፈጣን የእግርኳስ አጨዋወት ለመከተል ማሰባቸው ተነግሯል። ለዚህ ደግሞ ኢራኦላ ቀዳሚ ተመራጭ ሆነዋል። እናም ክለቡን መረከባቸው አይቀሬ ይመስላል።
በተመሳሳይ በቅርቡ የምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ ጎልማሳውን አሰልጣኝ ዣቢ አሎንሶን በሀላፊነት መሾሙ ይታወሳል።
እ.ኤ.አ ህዳር 25 ቀን 1981 የተወለደው ስፔናዊው አሰልጣኝ ዣቪ አሎንሶ 44 አመቱ ነው።
በአርባዎቹ እድሜ ውስጥ የሚገኘው አሰልጣኝ ዣቢ አሎንሶ ሰማያዊዎቹን ለሚቀጥሉት አራት አመታት ለማሰልጠን ከሳምንት በፊት ፊርማውን አኑሯል።
የቀድሞው የቸልሲ አሰልጣኝ የነበረው ጎልማሳው አሰልጣኝ ኢንዞ ማሬስካም እንዲሁ ፔፕ ጋርዲዮላን ተክቶ ማንችስተር ሲቲን መረከቡ አይዘነጋም።
ይህ ጎልማሳ አሰልጣኝ ኢንዞ ማሬስካ ማንችስተር ሲቲን በሶስት አመት ኮንትራት ለማሰልጠን መስማማታቸው እና ስራ መጀመራቸው ይታወሳል።
ሌላኛውን የለንደን ክለብ በቅርቡ የተረከበው አሰልጣኝ ሮቤርቶ ዲዘርቢም እንዲሁ ሌላኛው የሊጉ ጎልማሳ አሰልጣኝ ነው።
ቶተናም ሆትስፐርን በውድድር አመቱ ማብቂያ ወቅት በመረከብ ከመውረድ ለጥቂት የታደገው ሮበርት ዲዘርቢም እድሜው 46 ነው።
እ.ኤ.አ ሰኔ 6, 1979 ላይ በጣሊያን ብሬሺያ የተወለደው ዲዘርቢ በቶተናም ሆትስፐር ቤት እሰከ 2031 የሚያቆየውን የ5 ዓመት ኮንትራት ተፈራርሟል።
እንዲሁም በቅርቡ ማንችስተር ዩናይትድን በቋሚነት የተረከበው አሰልጣኝ ማይክል ካሪክም በእድሜ ከተጠቀሱት እኩያ ነው።
እ.ኤ.አ ሐምሌ 28 ፣ 1981 የተወለደ ማይክል ካሪክ 44 አመቱ ሲሆን በቀያይ ሰይጣናቱ ቤት የሁለት አመት እና ተጨማሪ አንድ አመት ውል ፊርማ መስማማቱ ይታወቃል።
ማንችስተር ዩናይትድን በ15 የሊግ ጨዋታዎች በጊዜያዊነት የመራው አሰልጣኝ ማይክል ካሪክ ቡድኑን ከሁለት አመት በኋላ ለሻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎ ማብቃትም ችሏል።
የሻምፒዮኖቹ አሰልጣኝ ሚካኤል አርቴታ በበኩሉ በአርባዎቹ እድሜ ውስጥ የሚገኝ የሊጉ አሰልጣኝ ነው።
እ.አ.አ መጋቢት 26 ቀን 1982 በሀገረ ስፔን የተወለደው የአርሰናል ዋና አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ አሁን ላይ እድሜ 44 ዓመቱ ነው።
ክለቡን አርሰናልን በውድድር አመቱ ለፕሪምየር ሊጉ ሻምፒዮንነት እና ለሻምፒዮንስ ሊጉ ፍፃሜ ያበቃው ሚካኤል አርቴታ ፣ ምንምኳ በሊጉ ለ7ኛ አመት እያሰለጠነ የቆየ ቢሆንም በቀጣይም በሊጉ መቆየቱ የማይቀር ይመስላል።
የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል በአመቱ መጨረሻ ለአሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ትልቅ ኮንትራት ሊያቀርቡ መሆኑ ተነግሯል።
አዲሱ ውል አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታን ከ ዓለም ከፍተኛ ተከፋይ አሰልጣኞች መካከል አንዱ እንደሚያደርገውም ተገልጿል።
ክለቡ ለአሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ከፍተኛ የደሞዝ ጭማሪ ለማድረግ ማቀዱ የተሰማ ሲሆን ክፍያውም አሰልጣኝ ዲያጎ ሲሞኒ በአትሌቲኮ ማድሪድ ከሚያገኙት ክፍያ ጋር የተቀራረበ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
ታዲያ ከ20 የሊጉ ክለቦች መካከል በተለምዶ (BIG 6) የሚባሉት አርሰናል ፣ ማንችስተር ሲቲ ፣ ማንችስተር ዩናይትድ ፣ ሊቨርፑል ፣ ቸልሲ እና ቶተናም አሰልጣኞች በሙሉ በአርባዎቹ እድሜ ውስጥ ይገኛል።
ታዲያ ይህ የአሰልጣኞች ተመሳሳይ እድሜ ላይ መገኘት እና ሊጉ ወደ ጎልማሳ አሰልጣኞች ፊቱን ማዘሩ ሚስጥሩ ምን ይሆን?
ክለቦችስ በእነዚህ ጎልማሳ አሰልጣኞች እየተመራ በቀጣይ የሚያሳዩን ስኬት ምን ይመስል ይሆን?
የትኛው ጎልማሳ አሰልጣኝስ ይሳካለታል የሚለውን በቀጣይ አብረን የምናየው ይሆናል።