በመኮንን አልማው
በታላቁ የደስታ መድረክ ላይ ክብር የተሰጠው ሰው እና ያልተጠበቀው የመድፈኞቹ አስደናቂ ተግባር አለምን አነጋግሯል።
ከሰሞኑኑ አንድ ምሽት ላይ በነበረ ትልቅ መድረክ ላይ አንድ የማይታወቅ ሰው የመድረኩ ዋና አሳላፊ ሆኖ ተገኝቶ ነበር።
ይህ ሰው በተሰየመበት ቦታ ላይ ሁሌም የሚገኙት አለም ያወቃቸው ፀሐይ የሞቃቸው ዝነኛ እና እውቅ ሰዎች ብቻ ናቸው።
ታዲያ ከሰሞኑኑ አነጋጋሪ የሆነው ጉዳይ የተከሰተው ግን ከዚያ ፍፁም ተቃራኒ ነበር። በእንግሊዝ ምድር ክርስታል ፓላስ ስቴዲየም ሴል ኸረስት ላይ ነበር ይህ የሆነው።
አርሰናል ከ22 አመታት በኋላ ባሳካው የፕሪምየር ሊጉ ሻምፒዮና ምሽት ድላቸውን ሲያከብሩ አንድ ፍፁም የማይታወቅ ሰው በዚያ ቦታ አጋፋሪ ሆኖ መገኘት በብዙዎች ዘንድ ጥያቄ ፈጥሮ ነበር።
ይህ ሰው ጠቆር ፣ አጠር ፣ ወፈር ያለ ፣ የራስ ቅሉ ላይ አንዲት ዘለላ ፀጉር ያልተስተዋለበት ፣ አይኖቹ መስታውት ላይ መነጽር የደቀነ ፣ ቀልጠፍ ለማለት የሚቸገር የሚመስል ግን ለታዳሚው አይን አዲስ እና እዚህ ግባ የማይባል አይነት ነው።
ሆኖም በአርሰናሎች ማሊያ ደምቆ ከመድፈኞቹ እኩል ፊቱ በደስታ እየበራ ከዋንጫው ጋር ይታይ ነበር።
ይባስ ብሎ የ2025/26 ሻምፒዮን ለሆኑት ለመድፈኞቹ ሜዳሊያ ያጠልቅ ጀመር። በመጨረሻም ለክለቡ አምበል ማርቲን ኦዴጋርድ ዋንጫውን ከቡድን አጋሮቹ ጋር ከፍ እንዲያደርግ ሰጭ የነበረው እሱ ነው።
የአለማችን ቀዳሚ እና እጅግ ተወዳጅ በሆነው የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የውድድር አመቱ ሻምፒዮናዎችን ዋንጫ ለማቀበል እና አንገታቸው ላይ ሜዳሊያ ለማጥለቅ የተመረጠው ሰው ማነው?

ይህ ሰው ስሙ ኢማኑኤል ነሚቻ ይባላል። አርሴናል በ2003/04 ለመጨረሻ ጊዜ ዋንጫ ሲወስድ 5 አመቱ ነበር። አሁን ደግሞ የ27 ዓመት ሰው ነው።
ከኢምሬትስ ስታዲየም 10 ደቂቃ የሚፈጅ የመንገድ ርቀት ላይ በምትገኘው በኢስልተን ይኖራል።
የሰሜን ለንደን ዩናይትድ ተጫዋችና አምባሳደርም ነው።
ሰሜን ለንደን ዩናይትድ ማለት ከ13 አመት በፊት የተቋቋመ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ተጫዋቾች ቡድን ነው። መስራቹና ዋና አሰልጣኙ ሀሮልድ ቤኔት ይባላሉ። እድሜያቸው ከ5-30 አመት የሆናቸውን ታዳጊና ወጣቶችን በእግር ኳስ ጥላ ስር አቅፈው ያሰለጥናሉ። የቤኔት ሴት ልጅም የቡድኑ አካል ናት። አርሴናልም ማህበራዊ ሀላፊነቱን ለመወጣት ይህንን ተቋም ይደግፋል።
ያ እሁድ ምሽት የተጫዋቾቹ አንገት ላይ ሜዳሊያ ያጠለቀው ፣ ለ22 አመታት በናፍቆት የጠበቁትን ዋንጫ ለአምበሉ ኦዲጋርድ ያሳቀፈው እና አብሯቸው ሲፈነድቅ ያመሸው የክብር እንግዳ እና ሸላሚው ሰውም የዚህ አካል ነው።
አነጋጋሪው ኢማኑኤል ድርጅቱ ከተመሰረተ ጀምሮ የቡድኑ አባል የሆነ እና ለሻምፒዮኖቹም የቅርብ ሰው ነው።
የክለቡን አሰልጣኝ ሚካኤል አርቴታን ጨምሮ ተጫዋቾችን ቃለመጠይቅ ያደረገ ፣ በልምምድ ቦታ በተደጋጋሚ እየተገኘ ከቡድኑ ጋር ያሳለፈ የመድፈኞቹ ተወዳጅ ቤተሰብ ነው።
ታዲያ የአርሰናል አመራሮችም ከሱፍ ለባሽ ባለስልጣናት ፣ ከታሪካዊ ተጫዋች እና ከዝነኛ ሰዎች ይልቅ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለበትን ኢማኑኤል ነሚቻን አስቀደሙት።
ለዚህ ታላቅ ሃላፊነት መርጠው ለሚመለከተው አካል አሳወቁ!
የሊጉ ሹሞችም በቀረበላቸው ሃሳብ ሙሉ ለሙሉ ተስማምተው ፣ በታሪካዊ ቀን በአለም ፊት ደማቅ እና የማይረሳ አስመስጋኝ ታሪክ እንዲፃፉ አደረጉ።
ኢማኑኤልም የተጣለበትን አደራ በሚገባ ተወጥቶ ራሱንና የተወከለበትን አላማ በደስታ ፈጽሟል።
ይህ ውሳኔ በአለም ላይ ለሚገኙ ከስድስት ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸው ሰዎች ትልቅ አክብሮትንና አብሮነትን ያሳየ ሆኗል።
ይህ ብቻ አይደለም ለስፖርቱ አለም ትልቅ ክብር እና ገጽታ መገንቢያ ሆኖ ተመዝግቧል።
እግር ኳስ ከመሸነፍ ፣ ከማሸነፍ እና ነጥብ ከመጋራት ባሻገር በርካታ ሰብዓዊነት ያላቸው ተግባራት የሚፈጸምበት አለም እንደሆነ ታይቶበታል።
በእውነትም እግር ኳስ ከጥንት ጀምሮ እጅግ በርካታ መልካም ነገሮች የሚከወኑበት የአለማችን ተወዳጅ ስፖርት ነው።
ለዚህም ከምንም ተነስተው ፣ ኳስ አንከባለው የራሳቸውን እና የቤተሰቦቻቸውን ህይወት ከመቀየር ባሻገር ለዘመዶቻቸው እና ለቀያቸው ማህበረሰብ አለኝታ ፣ ለሀገራቸው ኩራት መሆን የቻሉ የትየለሌዎችን መጥቀስ ይቻላል።
ከየትኛውም ዘርፍ በላይ እግር ኳስ ዘረኝነትን ፣ ጦርነትን እና ኢ-ሰብዓዊ ድርጊትን የሚቃወም ስፖርት ነው።