Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ስፖርት

የኔይማር አስደንጋጭ ጉዳትና የዓለም ዋንጫ ተስፋው

SM Samuel Mulgeta May 29, 2026 4 ደቂቃ ንባብ 160 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
የኔይማር አስደንጋጭ ጉዳትና የዓለም ዋንጫ ተስፋው

ብራዚላውያንንና የእግር ኳስ አፍቃሪያንን ለአንድ ሳምንት በደስታ አስፈንድቆት የጠፋው የኔይማር ጁኒየር መጥፎ ዜና የእግር ኳሱን ቤተሰብ ትኩረት ስቧል።

በመኮንን አልማው!


የእግር ኳስ ጠበብቱ ኔይማር ዳ ሲልቫ ሳንቶስ ጁኒየር ያልተዘጋው የጉዳት መዝገቡ አዲስ ፋይል ከፍቶበታል።

 

Advertisement
Your ad could be here — contact us

ከአለማችን እጅግ ተወዳጁ ከሆኑ ኮከቦች መካከል አንዱ የሆነው እና በእግር ኳስ ጥበቡ ላይ እጅግ ውብ ክህሎት ያለው ድንቁ ተጫዋች ኔይማር ጁኒየር ፣ ባለው የእግር ኳስ ችሎታ በብዙዎች አይን ውስጥ ተስሏል ፤ በብዙዎች ልብ ውስጥ ገብቷል።

 

ከውብ የእግር ኳስ ጠቢብነቱ በመነሳት በርካቶች የሚያደንቁት እና ከእግር ኳስ የሚገባውን ሽልማት አለገኘም በማለት አወንታዊ አስተያየት የሚሰጥበት ነይማር ጁኒየር የመጨረሻው እንደሚሆን በሚጠበቀው የአለም ዋንጫ ተሳትፎው ላይ አዲስ ፈተና ተጋርጦበታል።

 

በብራዚሉ ክለብ ሳንቶስ የእግር ኳስ ፕሮፌሽናልነቱን "ሀ ብሎ ጀምሮ "ፐ" ለማለት የተቃረበው የ33 አመቱ ኔይማር ያለፉትን አመታት መጥፎ ያደረገበት የጉዳት ዜና ዛሬም መሰናክሉ ሆኗል።

 

ከሳንቶስ ወደ ባርሴሎና በማምራት ጥሩ 5 አመታትን ያሳለፈው ኔይማር ፣ ከባርሴሎና ወደ ፒኤስጂ ካመራ በኋላ ብዙዎች እንደጠበቁት ሳይሆን ቀርቶ ደማቅ ማንነቱ ከእግር ኳስ ወዳዱ ማህበረሰብ ገሸሽ ብሎ ነበር።


ካልተሳኩ የፒኤስጂ 6 አመታት ቆይታ በኋላ ወደ ሳውዲ አረቢያ ቢያመራም በሃገሪቷን ታላቅ ክለብ አል ሂላልን ስኬታማ ጊዜ ሳያሳልፍ ቀርቷል።


ነገሮች በሳውዲ ፈታኝ የሆኑበት ኔይማር በተደጋጋሚ ጉዳቶች መፈተኑ እንደተጠበቀው ሳይሆን ቀርቷል።


በዚህም ኔይማር ለሳኡዳረቢያው ክለብ አል ሂላል በመጨረሻው የውድድር አመት በጉዳት ምክንያት የተሰለፈው በ2 ጨዋታዎች ብቻ ነበር፡፡ እሱንም ሙሉ ሳይሆን ተቀይሮ እየገባ በድምሩ 42 ደቂቃ ብቻ ነበር መጫወት የቻለው፡፡ 


ነገር ግን በአመቱ ውስጥ የተሰጠው የገንዘብ ክፍያ 101 ሚሊየን ዩሮ ነበር፡፡


በዚህም አል-ሂላል በተጨዋቹ ሁኔታ ኪሳራ ስለደረሰበት በጋራ ስምምነት ለመለያየት ወሰኑ። በይፋ መለያየታቸውንም አወጁ።


ቀጥሎ ለኔይማር ከልጅነት ክለቡ ሳንቶስ የ"ወደኛ ና" ጥያቄ ቀረበለት። 


ተደጋጋሚ ጉዳቶች ያደበዘዙት ደማቁ ባለተሰጥኦ ሳያቅማማ ተቀበለ። 


በወቅቱ 33ኛ አመቱን የያዘው ነይማር አዲሡን ህይወቱን  በልጅነት ክለቡ ሳንቶስ ሀ ብሎ ጀመረ።


እዛም አልለቅ ካለው የጉዳት ጠኔ ጋር እየታገለ ክለቡን ከመውረድ በመታደግ አስደናቂ ውለታ ውሏል።

 


የአለም ዋንጫ እየተቃረበ ሲመጣ ደግሞ ህልሙ በሆነውና ምናልባትም የመጨረሻው ሊሆን በሚችለው ትልቅ መድረክ ላይ አገሩን ወክሎ ለመገኘት የቻለውን ሁሉ አደረገ።


ሆኖም በመጀመሪያ የካርሎ አንቾሎቲ ስብስብ ውስጥ ስሙ ሳይሰፍር ቀረ።


ባለፉት 10 አመታት መሠረቷን በኔይማር ጁኒየር ላይ አድርጋ ግን ለትልቅ ዋንጫ ያልታደለችው የእግር ኳስ ፈጣሪዋ ብራዚል የ2026 አለም ዋንጫን ከኔይማር ውጪ የምትሞክረው መሠለች።


ሆኖም እግር ኳስን በደስታና በጥበብ የሚያጫውተው ኔይማር በጉዳትና በሰዎች ትችት ተስፋ ሳይቆርጥ ዳግም ለዓለም ዋንጫው ራሱን አዘጋጀ።


የእሱ በሜዳ ላይ መገኘት ለብራዚላውያን ብቻ ሳይሆን ለእውነተኛው የአለም እግር ኳስ አፍቃሪዎችም ደስታን የሚፈጥር መሆኑ ግልጽ ነው።


ለብዙዎች የዘንድሮውን የዓለም ዋንጫ እና የብራዚልን ጨዋታዎች በጉጉት ለመጠበቅ የኔይማር መኖር ትልቅ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ማንም ያውቃል።


ነይማር በበኩሉ በግልፅ "ሀገሬን ለመወከል ማድረግ ያለብኝን ሁሉ እያደረኩ ነው ፣ ቀሪው የኔ ስራ አይደለም" አለ።


ብራዚላውያንም ከተጫዋቾች እስከ ህዝቡ "ነይማር ያሥፈልገናል። እሱን በብሔራዊ ስብስብ ውስጥ ማየት እንፈልጋለን!  ያለኮከባችን አለም ዋንጫን አናስብም" አሉ።


ጣሊያናዊው የቡድኑ አሰልጣኝ ካርሎ አንቾሎቲ ተጨነቁ። ታዲያ ስብሰባቸውን ባለፈው ሳምንት ሲያሳውቁ የዚህ ኮከብ ስም አብሮ ተጠራ።


መላውን አለም አስደሰተ! በርካቶች በእንባ ታጅበው ፈጣሪንና አንቾሎቲን አመሠገኑ።


ኔይማርም ከሶስት አመታት በኋላ ወደ ብራዚል ብሔራዊ ቡድን ስብስብ በመመለሱ የዛኑ ቀን ሌሊቱን ሙሉ በደስታ ሲያለቅስ ማደሩን ተናገረ።


ኔይማር በራሱ የግል ሄሊኮፕተር በመብረር የብሔራዊ ቡድኑን ካምፕ ሲቀላቀል፣ በእሱ መምጣት በቡድኑ ውስጥ የነበረውን ድባብ ፍፁም ቀየረው። ያም ብራዚላውያን ለዓለም ዋንጫው ስኬት የኔይማር መገኘት ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነና እሱን ለማየት እንደጓጉ በግልጽ ያሳያል። 


ወደናፈቀው የብሔራዊ ቡድኑ ስብስብ እና ወደ ግዙፉ የአለም እግር ኳስ መድረክ የተመለሰው ነይማር ይህ ከሆነ በኋላ በሰጠው አስተያየት "አለም ዋንጫውን ለማሸነፍ ህይወታችንን እንሰጣለን! በውድድሩ ቡድኑ አለማውን ለማሳካት በጋራ ቆሞ እንደሚፋለም ቃሌን እሰጣለሁ" አለ።


ይህ ተጫዋቹን ፣ ብራዚላውያንን እና በርካታ እግር ኳስ አፍቃሪያንን ያስፈነጠዘው ደስታ ታዲያ ከ10 ቀናት በላይ አልቆየም።


ኔይማር ከቅርብ አመታት ወዲህ የተጠናወተው መጥፎ የጉዳት ዜና በአዲስ ተሰማ።


ብራዚል ለአለም ዋንጫው የተመረጠው ኔይማር ከትላንት በስቲያ ረቡዕ  ከቡድኑ ጋር ልምምድ እንዳልሰራ ይልቁንም የሕክምና ምርመራዎችን ለማድረግ ወደ ክሊኒክ መሄዱ ሲዘገብ በርካታ ወዳጆቹን ለሀዘን ዳርጓቸዋል።


በዚህ የአለም ዋንጫ ዝግጅት ወቅት በርካታ ብራዚላውያን ወደ ካምፕ እየደረሱ ባለበት ወቅት የኔይማር ወደ ሆስፒታል ማምራቱ የብዙዎችን ልብ ሰብሯል።


ኔይማር ከጉዳቱ አገግሞ ወደ ሜዳ ለመመለስ ከሁለት እስከ ሶስት ሳምንታት ሊወስድበት እንደሚችል የተገለፀ ሲሆን በዚህም ምክንያት ብራዚል የምታደርገው የወዳጅነት ጨዋታ እንደሚያመልጠው ተገልጿል። 


በተጨማሪም ብራዚል ከሞሮኮ የምታደርገው የዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ ጨዋታ ሊያመልጠው እንደሚችል ተዘግቧል።


ይህ ብቻ አይደለም ማባሪያ የሌለው እና በየጊዜው እየታደሰ አቅሙንና ክህሎቱን እንዳያሣይ እንቅፋት የሆነበት ይህ ጉዳት ዳንኩ ሲል ተመልሶ እንደማያገረሽበት ምን ማስተማመኛ አለው? ካርሎ አንቾሎቲስ ከሁኔታው አሳሳቢነት በመነሳት ከስብስቡ እንደማይቀንሱት ምን ዋሥትና አለ?
የሚለው ጥያቄ ለኔይማር ፣ ለብራዚል እና ለመላው እግር ኳስ አፍቃሪያን ትልቅ መርዶ ይዞ እንዳይመጣ ተሰግቷል።

SM
ስለ ጸሐፊው

Samuel Mulgeta

30 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።