በመኮነን አልማው!
በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሶስት ሀገራት አዘጋጅነት የሚካሔደው 23ኛው የአለም ዋንጫ ውድድር ዛሬ ምሽት አራት ሰዓት ላይ በሜክሲኮ መካሄዱን ሲጀምር አዘጋጇ ሀገር ሜክሲኮ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ትጫወታለች።
ሜክሲኮ በአለም ዋንጫ ታሪክ በመክፈቻ ያደረገቻቸውን ሰባት ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለችም። ሜክሲኮ ያኔ በ2010 የደቡብ አፍሪካው ዓለም ዋንጫ ጊዜ ከራሷ ከአዘጋጇ ጋር የመክፈቻ ጨዋታዋን አድርጋ 1ለ1 ነበር የተለያዩት።
ዛሬ በሀገሯ ከ2010 የአለም ዋንጫ አዘጋጇ አፍሪካዊት ሀገር ጋር የምታደርገው ጨዋታ ይጠበቃል። በዚህ አለም ዋንጫ በሶስቱም አዘጋጅ ሀገራት በኩል ሶስት የመክፈቻ ጨዋታ የሚካሔድ ሲሆን የመጀመሪያው መክፈቻ ዛሬ ምሽት ይደረጋል።
በመክፈቻው ሻኪራ እና ቡርና ቦይ ' dai dai ' የተሰኘውን ይፋዊ የዓለም ዋንጫ ዜማ ያቀነቅናሉ። እንዲሁም ሌሎች ታዋቂ አቀንቃኞች ይገኛሉ።
በዘንድሮው የመክፈቻ ዝግጅት ዶናልድ ትራምፕ እንደማይገኙ ተገልጿል።
በዓለም ዋንጫ መክፈቻ ጨዋታ የአዘጋጅ ሀገራት መሪዎች ስታዲየም ሲገኙ መመልከት የተለመደ ቢሆንም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግን የአሜሪካ የመክፈቻ ጨዋታ ላይ የመገኘት እቅድ እንደሌላቸው ተገልጿል።
በመክፈቻ ጨዋታው እሳቸውን በመተካት ሌሎች ሀላፊዎች እንደሚገኙ ተነግሯል። ባለፉት የዓለም ዋንጫ ውድድሮች መክፈቻ ጨዋታ ላይ የአዘጋጅ ሀገራት መሪዎች ተገኝተው ነበር።
ለአብነትም :- በ2022 አለም ዋንጫ የኳታር ጠቅላይ ምኒስትር ኤሚር ተገኝተው ነበር። በ2018 አለም ዋንጫም የሩስያው ፕሬዝዳንት ፑቲን በመክፈቻው መገኘታቸው ይታወሳል። እንዲሁ በ2014 የአለም ዋንጫ የብራዚል ፕሬዝዳንት ሮሴፍ ተገኝተው የሀገራቸውን መክፈቻ ጨዋታ ታድመው ነበር።
አሜሪካ የዓለም ዋንጫ መክፈቻ ጨዋታዋን ነገ አርብ ሌሊት 10:00 ሰዓት ከፓራጓይ ጋር ታደርጋለች። ገና ከወዲሁ አነጋጋሪ እና አወዛጋቢ የሆነው ይህ የአለም ዋንጫ ውድድር በበርካቶች ዘንድ በከፍተኛ ሁኔታ እየተተቸ ሲሆን ትራምፕ እና ኢንፋንቲኖም ምላሽ ሰጠውበታል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይህ የዓለም ዋንጫ ውድድር በታሪክ ምርጡ ይሆናል ብለዋል።
"ኢንፋንቲኖም በታሪክ እንዲህ ሰምሮ አያውቅም ብሎኛል" የሚሉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስለ ዓለም ዋንጫ ያላቸውን አስተያየት ስጥተዋል።
በንግግራቸውም “ የ2026 ዓለም ዋንጫ በታሪክ ስኬታማው ዓለም ዋንጫ ይሆናል “ ያሉት ፕሬዚዳንቱ ስለ ቪዛ እና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች ከጋዜጠኞች ተጠይቀው ሲመልሲ “ጥሩ ሰዎች ብቻ ወደ ሀገራችን እንዲገቡ ተግተን እየሰራን ነው “ ሲሉ መልሰዋል።
የፊፋው ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ በበኩላቸው ትላንት ምሽት በሜክሲኮ ስለውድድሩ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ከ3 አመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከጋዜጠኞች ጋር በተገናኙበት በዚህ ቆይታ "ዓለም ዋንጫው ሁሉንም ሪከርድ ይሰብራል" ሲሉ ተናግረዋል።
"የዘንድሮውን የአለም ዋንጫ ውድድር ከሁሉም የተለየ ነው" የሚሉት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ስለ ትኬት ዋጋ ተጠይቀው ሲመልሱ “የዚህ አመት የአለም ዋንጫ ትኬት ፍላጎት አይተነው የማናቀው ነው። ካለፉት ውድድሮች በአስር አጥፍ ይበልጣል” ብለዋል።
የዓለም ዋንጫ አዘጋጅነቱን ለአሜሪካ በመስጠታቸው ይፀፀቱ እንደሆነ ተጠይቀው የተጠየቁት ኢንፋንቲኖ “በፍፁም አልፀፀትም“ ሲሉ ምላሽ የሰጡ ሲሆን “ የምፀፀትበት አንዳችም ነገር የለም” ብለዋል።
ስለ ቪዛ የተጠየቁት ፕሬዝዳንቱ “አሜሪካ ማንን ወደ ሀገሯ ማስወጣት እና ማስገባት እንዳለባት እኛ መወሰን አንችልም “ሲሉ መልሰዋል። በአዘጋጆች ይህ የተባለለት ነገር ግን በተመልካቹ እና በተሳታፊዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየተተቸ ያለው ይህ የአለም ዋንጫ ዛሬ በይፋ መካሔድ ይጀምራል።
በሜክሲኮ እና በደቡብ አፍሪካ መካከል የሚደረገው የዕለቱ የ2026 ዓለም ዋንጫ የመክፈቻ ጨዋታው በሜክሲኮ ሲቲ ስታዲየም ከምሽቱ 4:0ዐ ሰዓት ላይ ይጀመራል።
የመክፈቻ ጨዋታውን ብራዚላዊው ዳኛ ዊልተን ሳምፓዮ በመሀል ዳኝነት እንዲመሩት ሀላፊነት ተሰጥቷቸዋል።
ከዚህ የመክፈቻ ጨዋታ ቀጥሎ ሌሊት 11 ሰዓት ላይ ደቡብ ኮሪያ ከቼክ ሪፐፕሊክ ይጫወታሉ።