በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቪየና ኮንቬንሽን መሰረት ለኢትዮጵያ የተሰጠውን ዓለም አቀፍ የ "ETH" ኮድ ያካተተው አዲሱ የተሽከርካሪ ሰሌዳ (ታርጋ) ከዛሬ ጀምሮ በይፋ መሰጠት ተጀምሯል።
ይህ አዲስ አሰራር በከተማው በሚገኙ 11 ቅርንጫፎች በኩል የተጀመረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱ እየተሰጠ ያለው አዲስ መኪና ለሚገዙና ቀደም ብለው ተመዝግበው ሰሌዳ በመጠባበቅ ላይ ለሚገኙ ተገልጋዮች መሆኑ ታውቋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ዛሬ በሰጠው መግለጫ አዲሱ የተሽከርካሪ ሰሌዳ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ መለያዎችን፣ ከፍተኛ ጥንካሬንና ሀገራዊ አንድነትን የሚገልጹ ይዘቶችን አካቶ መቅረቡን አስታውቋል።
ከተቋሙ መግለጫ አስቀድሞ የወጣ እና በማህበራዊ ሚዲያ የተዘዋወረ ሰነድ አዲሱ ታርጋ የፊትና የኋላ ሰሌዳዎችን እንዲሁም ቫትን ጨምሮ እስከ 56,000 ብር ዋጋ መቁረጡን ያመለከተ ቢሆንም ተቋሙ ግን ከጋዜጠኞች ለቀረበለት ጥያቄ በሰጠው ምላሽ ዋጋው እንደየተሽከርካሪው ዓይነት እንደሚለያይ አስረድቷል።
በትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር አማካኝነት በአዲስ አበባ የተጀመረው ይህ አሰራር ለክልሎችም በማኑዋል ደረጃ የተላከ ሲሆን ዝግጅታቸውን ያጠናቀቁ ክልሎች በቀጣይ ትግበራውን እንደሚጀምሩ ተገልጿል።
አዲሱ ታርጋ ምን ምን አዳዲስ ነገሮችን ይዟል?
የአዲስ አበባ ከተማ አሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዘገየ በላይ እንደገለጹት እስካሁን ስራ ላይ የነበረው ሰሌዳ በርካታ ጉድለቶች የነበሩበት ቶሎ የሚበላሽና ተመሳሳይ (ፎርጅድ) ምርት የሚሰራበት በመሆኑ አዲሱ አሰራር ይህንን ችግር ሙሉ በሙሉ ያስቀራል።
አዲሱ ሰሌዳ ይዞአቸው የመጣቸው ዋና ዋና አዳዲስ ነገሮች የሚከተሉት ናቸው፡
• የ "ETH" ዓለም አቀፍ ኮድ፡ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ታርጋ ላይ የነበረው "ET" የሚለው መለያ በቪየና ኮንቬንሽን መሰረት ለኢትዮጵያ የተፈቀደ አልነበረም። አዲሱ ሰሌዳ ግን በዓለም አቀፉ ስምምነት ለሀገሪቱ የተሰጠውን ትክክለኛ "ETH" የሚለውን ኮድ ያካተተ በመሆኑ የራሱ ፖለቲካዊ አንድምታ አለው።
• የቺፕስ እና RFID ቴክኖሎጂ፡ ለህግ ማስከበር ስራ ምቹ እንዲሆን ታርጋው ላይ የቺፕስ ቴክኖሎጂ የተገጠመለት ሲሆን በተሽከርካሪው የፊት መስታወት ላይ ደግሞ የRFID መለያ ይደረግበታል። ይህም ስለ ተሽከርካሪው አይነትና ባለቤትነት ትክክለኛ መረጃ በመስጠት ጥፋት አጥፍቶ ለመሰወር የሚደረገን ሙከራ ያጠባል።
• በሰከንድ የሚዘምን መረጃ ፡ አሰራሩ ከግምታዊ መረጃዎች የወጣና በየቀኑ የሚመዘገቡ መረጃዎችን በአንድ ክሊክ ለማወቅ የሚያስችል ነው።
• የመደጋገም ምዝገባን መከልከል ፡ አንድ ተሽከርካሪ በአንድ ክልል ከተመዘገበ ሲስተሙ ራሱ 'ብሎክ' ስለሚያደርገው ሌላ ክልል ሄዶ በድጋሚ መመዝገብ አይችልም።
• ከፍተኛ ጥንካሬ እና ሀገራዊ ይዘት፡ ሰሌዳው ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጎ የተሰራ በመሆኑ ተሽከርካሪዎች የአገልግሎት ለውጥ በሚያደርጉበት ወቅት የሚወጣውን ተጨማሪ ወጪ ያስቀራል። በተጨማሪም ሀገራዊ አንድነትንና ኢትዮጵያን የሚገልጹ ይዘቶች ተካተውበታል።
ዋና ስራ አስኪያጁ አቶ ዘገየ በላይ እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት አዲሱን ታርጋ ለመውሰድ ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች ተመዝግበው የሚገኙ ሲሆን ቀደም ሲል ተመዝግበው ሰሌዳ በመጠባበቅ ላይ ለሚገኙ ተገልጋዮች የሰልፍ እንግልትና የጊዜ መባከን እንዳይኖር ባመለከቱበት ቅደም ተከተል መሰረት ከየቅርንጫፎቹ ስልክ እየተደወለላቸው መጥተው አገልግሎቱን እንዲወስዱ አቅጣጫ መተላለፉን አስታውቀዋል።