ለመምህራን የትምህርት እቅድ የሚያዘጋጅ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የፈተና ጥያቄዎችንና አሳይመንቶችን የሚያመነጭ እንዲሁም የማስተማሪያ ስልቶችን በራሱ የሚያቀናጅ የሰው ሰራሽ አስተውሎት መተግበሪያ ተበልጽጎ በሙከራ ደረጃ ሥራ ላይ መዋሉን ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
“ኤጀንቲክ መምህር ረዳት” የተሰኘው መተግበርያው የሁለተኛ ደረጃ መምህራንን የዕለት ተዕለት የሥራ ጫና በእጅጉ የሚቀንስ እና ሙሉ በሙሉ ያለ ኢንተርኔት ራሱን ችሎ ተግባራትን ማከናወን የሚችል ነው።
ይህ መተግበሪያ በማዕከላዊ ሰርቨር ወይም በክላውድ ቴክኖሎጂ ላይ ከመተማመን ይልቅ በኮምፒውተር ላይ በቀላሉ ተጭኖ የሚሰራና በውስጥ አቅም የበለጸገ የቴክኖሎጂ ውጤት ነው።
መተግበሪያው በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት መሠረት ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉትን መጽሃፍቶች በሙሉ ዳታሴት በማድረግ መጻሕፍቱን ሙሉ በሙሉ እንዲመረምርና እንዲገነዘብ ተደርጎ የተዘጋጀ ቀላል ሞዴል ሲሆን ምንም ዓይነት ከፍተኛ የሃርድዌር ዝርዝር ሳይጠይቅ በቀላሉ በማንኛውም ላፕቶፕ ወይም ዴስክቶፕ ኮምፒውተር ላይ መሥራት መቻሉ ልዩ ያደርገዋል።
ይህ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) መተግበሪያ በርካታ ተግባራትን ማከናወን የሚችል ሲሆን ዋና ዋናዎቹ የትምህርት እቅድ ማዘጋጀት፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የፈተና ጥያቄዎችንና አሳይመንቶችን ማመንጨት፣ እንዲሁም የማስተማሪያ ስልቶችን በራሱ ማቀናጀት የሚችል መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
ይህም መምህራን በተለመዱ የዕለት ተዕለት የቢሮክራሲ ተግባራት የሚያጠፉትን ውድ ጊዜ ሙሉ በሙሉ የሚያስቀርላቸው ሲሆን ከተማሪዎቻቸው ጋር ቀጥታ ለሚኖራቸው ግንኙነት በቂ ጊዜ እንዲያገኙና የማስተማር ብቃታቸውን በማጎልበት የትምህርትን ጥራት ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሏል።
ይህ መተግበሪያ ትምህርት ሚኒስቴር የሚያካሂደው አጠቃላይ የትምህርት ዲጂታላይዜሽን ስትራቴጂ አካል መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን መተግበሪያው ሙሉ በሙሉ በኦፍላይን የሚሰራ መሆኑ የኢንተርኔት ኔትወርክ በሌላቸው የገጠርና ራቅ ያሉ አካባቢዎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ያለምንም መቆራረጥ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል ተገልጿል።
ይህም በከተማና በገጠር መካከል ያለውን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና የትምህርት ጥራት ልዩነት በከፍተኛ ደረጃ ለማጥበብ የሚያስችል ይሆናል።
በዚህም ተማሪዎች በተከታታይ ምዘና የተሻለ ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ ውጤታቸውን ያሻሽላል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በተመረጡ ትምህርት ቤቶች ተሞክሮ አጥጋቢ ውጤት ማስገኘቱን ሚኒስቴሩ ጠቁሟል።
በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት ከሁሉም ክልሎች ለተውጣጡ መምህራንና የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱ ነው የተገለጸው።
በሙከራ ደረጃ ላይ የሚገኘው የዚህ መተግበሪያ ቀጣይ የማስፋፊያ ሥራዎች በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ በሚንቀሳቀሰው “የኢትዮጵያ የትምህርት ለውጥ ኦፕሬሽን” ፕሮጀክት ድጋፍ እየተከናወነ እንደሚገኝ ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።