Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ዜና

ፕሬዝዳንት ትራምፕ የኢራንን ምላሽ “ተቀባይነት የሌለው” ሲሉ አጣጣሉ

A Administrator May 14, 2026 Updated 3h ago 2 ደቂቃ ንባብ 28 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
ፕሬዝዳንት ትራምፕ የኢራንን ምላሽ “ተቀባይነት የሌለው” ሲሉ አጣጣሉ

ግንቦት 3/2018 (ገበያ ሚዲያ) ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን የቀረበችውን የሰላም ስምምነት ጥያቄ “ፈፅሞ ተቀባይነት የሌለው” በሚል ውድቅ ማድረጋቸውን በትናንትናው ዕለት አስታውቀዋል።

ይህ ውሳኔ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተጀመረውን ጦርነት ለማቆም የሚደረገውን ጥረት ያዳከመ ሲሆን በቀጣናው የነበረውን ስጋት ዳግም እንዲያገረሽ አድርጎታል።

ትራምፕ በራሳቸው የማህበራዊ ሚዲያ ገጽ ባስተላለፉት መልዕክት “የኢራን ተወካዮች ተብዬዎች የላኩትን ምላሽ አሁን አንብቤዋለሁ፤ አልወደድኩትም” ብለዋል።

Advertisement
Your ad could be here — contact us

ምንም እንኳን የኢራን መንግስት በፓኪስታን አምባሳደሮች በኩል የተሻሻለ የመርህ ስምምነት ሰነድ ለዋሽንግተን ማድረሱን ቢገልጽም ትራምፕ ግን በሰነዱ ውስጥ ምን ዓይነት ተቃውሞ እንዳላቸው በዝርዝር አላብራሩም።

ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ሁለቱ ወገኖች የ30 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲራዘም እና በኢራን ተዘግቶ የቆየው የሆርሙዝ ባህረ-ሰላጤ በድጋሚ እንዲከፈት ሲወያዩ ቆይተዋል።

ሆኖም ፕሬዝዳንት ትራምፕ ዋነኛ ግባቸው ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዳይኖራት ማድረግ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል።

አሜሪካ የኢራንን የዩራኒየም ክምችት በቅርብ እየተከታተለች ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ “ማንም ወደዚያ ቦታ ቢጠጋ እናውቃለን ደብድበንም እናጠፋቸዋለን” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

በተጨማሪም የኢራንን የኒውክሌር ቁሳቁስ “አቧራ” በማለት የጠሩት ሲሆን  ስምምነት ላይ ለመድረስ ኢራን ይህንን ቁሳቁስ ሙሉ በሙሉ ማስረከብ እንዳለባት ፍንጭ ሰጥተዋል።

ከየካቲት 28 ጀምሮ አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የተቀናጀ ጥቃት መክፈታቸውን ተከትሎ ኢራን በበኩሏ በእስራኤል እና በአሜሪካ አጋር የአረብ ሀገራት ላይ የአጸፋ እርምጃ ስትወስድ መቆየቷ ይታወቃል።

ይሁን እንጂ ምንም እንኳን ባለፈው ወር የተኩስ አቁም ቢታወጅም ግጭቱ ሙሉ በሙሉ አለመቆሙን ፕሬዝዳንት ትራምፕ አምነዋል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው በሰጡት መግለጫ ከኢራን ጋር ያለው ግጭት “ገና አላበቃም” ያሉ ሲሆን ኢራን የኒውክሌር ስጋት ሆና እስካለች ድረስ እስራኤል ጥቃቷን እንደምትቀጥል ጠቁመዋል።

ትራምፕ ይህንን የሰላም ጥያቄ ውድቅ ያደረጉት በዚህ ሳምንት ቤጂንግ ውስጥ ከቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ ጋር ለመገናኘት ቀጠሮ በያዙበት ወቅት ሲሆን ቻይና የኢራን የቅርብ የንግድ አጋር በመሆኗ ይህ ጦርነት እንዲቆም ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት ይታወቃል።

ጦርነቱ በዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ላይ ከባድ ቀውስ ከመፍጠሩም በላይ፤ የአሜሪካን ወታደራዊ ትኩረት ከእስያ ወደ መካከለኛው ምስራቅ በማዞሩ ቤጂንግ ሁኔታውን በቅርብ እየተከታተለችው ትገኛለች።

በአሁኑ ወቅት በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ላይ የድሮን ጥቃቶች እየተሰነዘሩ መሆኑ እና የአሜሪካ የጦር መርከቦች በኢራን የባህር ዳርቻዎች ላይ እርምጃ መውሰዳቸው በቀጣናው ያለው ሁኔታ ጦርነትም ሰላምም የሌለበት አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱን የፖለቲካ ተንታኞች እየገለጹ ነው።

A
ስለ ጸሐፊው

Administrator

12 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።