Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ስፖርት

በተጫዋቾች ድብድብ እና በደጋፊዎች ዘመቻ እየተናጠ ያለው ሪያል ማድሪድ

A Administrator May 8, 2026 Updated 3h ago 6 ደቂቃ ንባብ 25 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
በተጫዋቾች ድብድብ እና በደጋፊዎች ዘመቻ እየተናጠ ያለው ሪያል ማድሪድ

ከሰሞኑኑ በድራማዎች የታጀበው የነጩ መንደር ሰዎች ያልተጠበቀ ሁነት የአለም እግር ኳስ መነጋገሪያ ሆኗል።

በመኮነን አልማው

ከሰሞኑኑ በድራማዎች የታጀበው የነጩ መንደር ሰዎች ያልተጠበቀ ሁነት የአለም እግር ኳስ መነጋገሪያ ሆኗል።

የውድድር አመቱን ያለዋንጫ ለማጠናቀቅ የተገደዱት ሎስብላንኮቹ  ማባሪያ የሌለው አዳዲስ ጉዳዮችን በእየቀኑ እያሰሙን ነው።

Advertisement
Your ad could be here — contact us

የአለማችን ኃያል በሆነው የእስፔኑ ክለብ ውስጥ ባላፉት ሳምንታት ያለ ማቋረጥ አዳዲስ አነጋጋሪ ጉዳዮች ተሰምተውበታል።

የቫልቬርዴ እና የቹኣሜኒ ለማመን የሚከብድ ጠንካራ ድብድብ ፤ በካሬራስ ፊት ላይ በኃይል ያረፈው የሩዲገር ሰፊ መዳፍ ፤ የአሰልጣኝ አርቤላኦ ከ 8 ተጫዋቾች ጋር ንግግር መንሳት ፤ የተጫዋቾች በቋንቋ እና በዜግነት መቧደን ፤ የኪሊያን ሜቫፔ ከህክምና ቡድኑ ጋር አለመተማመን እና የክለቡን ጉዳይ ወደጎን በማለት ከፍቅረኛው ጋር አሸሸ'ገዳሜ ማለት እና በብዙ ሚሊየን የሚቆጠሩ ደጋፊዎች የይልቀቅልን ፊርማ ማሰባሰብን ጨምሮ እኒህ ለአንድ ክለብ የህልውና አደጋ የሚፈጥሩ ሁነቶች ከሰሞኑኑ በሎንስ ብላንኮች ቤት የተፈጠረ አስቂኝ ፣ አስገራሚ እና አሳዛኝ ሁነት ነው።

ከዚህ ቀደም በጥብቅ ስነምግባር የተገነባ እና በኃያልነት ላይ በቆመ አንድነትና መተባበር እንዲሁም ዘረኝነትን አብዝቶ በመቃወም የሚታወቀው ሪያል ማድሪድ አሁን ላይ የራሡ ተጫዋቾች ዘር ፣ ቀለም ፣ ቋንቋ እና ዜግነትን መሰረት ባደረገ ቡድን ተከፋፍለው የአንድነታቸው ነጭ አርማ ላይ ጭቃ መቀባታቸው ተሰምቷል።

በሎስ ማሪንጌዎቹ ቤት እንደመሪ በሚታዩ ትልልቅ ተጫዋቾች መካከል ሳይቀር እየተፈጠረ ያለው ግጭት ደግሞ ዋነኛ ርእሰ ጉዳይ ሆኗል። 

ከ ቅርብ ቀናት በፊት በ መልበሻ ክፍል ውስጥ ለ ብዙ ተጫዋቾች አርአያ የሚሆን ስብዕና ያለው እና በቸልሲ ቤት ጭምር እንደምናውቀው በአመራር ብቃቱ የሚወደሰው አስቂኙ ተከላካዩ አንቶኒ ሩዲገር አልቫሮ ካሬራስን በጠንካራ ጥፊ መማታቱ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

በወቅቱ ለሪያል ማድሪድ መልበሻ ክፍል ቅርብ የነበሩ የመረጃ ምንጮች ስለጉዳዩ በመዘገብ ክስተቱን ለፀሐይ ሲያሞቁት በዚያ ሀያል እና አስፈሪ ክለብ ውስጥ እንዲህ አይነት ነገር መፈጠሩ የዘርፉን አለም ሰዎች 'ጉድ' አስብሎ ነበር።

ይህ የሩዲገር ያልታጠበቀ የጥፊ ርምጃ በወቅቱ መልበሻ ክፍሉን አሳስቦ የነበረ ሲሆን ተጫዋቹም ለቡድን አጋሮቹ እና ለስታፉን አባላቱ  የምሳ ግብዣ በማድረግ እና ይቅርታ በመጠየቅ የተወጠረውን ስጋት ለማርገብ ሞክሮ ነበር። 
ነገር ግን ችግሩ ተባብሶ ቀጠለ'ጂ መሰረታዊ መፍትሔ ማግኘት አልቻለም።
ጥቁሩን ሩዲገርን ተከትሉ በነጩ መንደር የገባው የድብድብ መንፈስ በይቅርታ ፀበል ቢጠመቅም ሌላ መግቢያ በር ፈልጎ በአዲስ ብቅ ብሏል።

ከትላንት በፊት ረቡ ዕለት በልምምድ ስፍራቸው ላይ በ ኦሪዬል ቹዋሜኒ እና በፌዴ ቫልቬርዴ መካከል ፀብ ሊፈጠር ችሏል። ችግሩ እንደተፈጠረ ለክለቡ ቅርብ የሆነው ማርካ ስለጉዳዩ ቀድሞ አስነብቦ የነበረ ሲሆን ከዛ ቡሀላም በርካታ የመረጃ አውታሮች ይህንን ሁነት በተለያዬ መንገድ አረጋግጠዋል። 

የሁለቱ ተጨዋቾች ፀብ ሙሉ ታሪክ 'ሀ' ብሎ የጀመረው ረቡዕ ማለዳ ነው።

ረቡዕ ጠዋት በስልጠና ላይ እያሉ ቹዋሜኒ በቫልቬርዴ ከልክ ያለፈ ጠንካራ ጥቃት እንደተሰነዘረበት ከተሰማው በኋላ ሁለቱ ተጫዋቾች ክርክር ውስጥ ገብተዋል። ክርክሩ ጠንከር ያለ ሰጣ ገባ ታክሎበት ከስልጠናው በኋላ ወደ መልበሻ ክፍል ይዘልቃል። የቡድኑ አባላትም ፀቡን ለማብረድ ጣልቃ በመግባታቸው ነገሩ የረገበ መሰለ።
ትላንት ሐሙስ በነበረው የልምምድ ሰዓት ቫልቨርዴ ወደ ስልጠናው ሲመጣ ከቹዋሜኒ በስተቀር ከሁሉም ጋር እጅ ለእጅ በመጨባበጥ ሰላምታ ተለዋውጧል። ቹዋሚኒ በበኩሉ እጁን ለሰላምታ ቢዘረጋለትም ቫልቬርዴ ግን ለመጨበጥ ፈቃድኛ ሳይሆን ቀርቷል።
በዕለቱ የልምምድ ክፍለ ጊዜም ቫልቨርዴ በቹዋሜኒ ላይ በተከታታይ ጠንካራ ታክሎችን እየወረደ ሲመታው ተስተውሏል። 
በዚህ ጊዜም ቹአሚኒ ቫልቬርዴን "ተው አትተናኮሰኝ ፣  ጥፋት አትስራብኝ" ብሎ ጠይቆታል። ሌሎች ተጫዋቾችም እንዲሁ ቫልቬርዴን "ተው" እንዳሉት እና ተጫዋቹ ግን ሊያቆም እንዳልቻለ ተገልጿል።

በቀጠለው የስልጠና ክፍለ ጊዜም ተጫዋቾች በሁለት ቡድን ተከፍለዋል። የአሰልጣኝ ክፍሉም የሁለቱን ግጭት ላለማባባስ እና ለማርገብ ሲሉ ቫልቨርዴን እና ቹዋሜኒን በአንዱ ቡድን ውስጥ አካተዋቸዋል። በዚህ ጊዜ ቫልቨርዴ ለቡድኑ ጓደኛው "እኔን ከመጋፈጥ ለመቆጠብ ከእኔ ጋር ስለመደቡህ እድለኛ ነህ" በማለት ሲናገር እንደተሰማ ተገልጿል። 

ስልጠናው ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል ሲመለሱ ቹዋሜኒ ቫልቨርዴን እንዲመጣ ይጠራዋል። ቫልቨርዴም በምላሹ ይሰድበዋል። ሁለቱ መጨቃጨቅ ሲጀምሩ ቹዋሜኒ ቫልቬርዴን ለቡጢ ጋበዞታል።
ቫልቨርዴም ሲወድቅ ጭንቅላቱን ጠረጴዛው እየደማ ነበር ተብሏል።
በተጨማሪም ራሱን ስቶ እና አንዳድ ትውስታዎችንም ረስቶ እንደበር ተነግሯል። በዚህ ጊዜ በክፍሉ ውስጥ የነበረው ሁኔታ ከፍተኛ ስጋት ነበር ተብሏል።
ቾዋሜኒንም በድርጊቶ ደንግጦ የነበር ሲሆን ቫልቬርዴም ጉዳት ከደረሰበት በኋላ በፍጥነት ወደ ሆስፒታል የተወሰደው ፌዴ ቫልቨርዴ ትላንት ምሽት ከሆስፒታል ወደ ቫልዴቤባስ መመለሱ ታውቋል።

ፌዴሪኮ ቫልቬርዴ ከሆስፒታል ከወጣ በኋላም ትላንት ምሽት ባጋራው መልዕክት ጭንቅላቱን የተጎዳው በቡድን አጋሩ ተመቶ አለመሆኑን እና ጠቡ የቃላት ልውውጥ ብቻ እንደነበር ገልጿል። 

ተጨዋቹ በማህበራዊ ገጹ ላይ ባጋራው መልዕክትም “የቡድን አጋሬ እኔን አልመታኝም እኔም አልመታሁትም “ ሲል አስፍሯል።

ነገር ግን ተጫዋቹ ያጋራው ይህ ፖስት መነጋገሪያ የሆነውን ጉዳይ ለማርገብ እንጂ ፍፁም ከእውነት ያራቀ መሆኑ ግልፅ ነው።

በዚህም ተጨዋቹ በኤልክላሲኮ ላይ እንደማይሳተፍ ተገልጿል። ዶክተሮች በጭንቅላቱ ላይ ከደረሰው ከባድ ጉዳት በኋላ ቢያንስ ለ1 ሳምንት ከስልጠና እና ከጨዋታዎች እንዲያርፍ ነግረውታል ተብሏል።

በተጨማሪም ይህንን የተፈጠረውን አስደንጋጭ ክስተት  ተከትሎ
ሪያል ማድሪድ በቹአሜኒ እና ቫልቬርዴ ላይ ክፉኛ ተቆጥቷል። ተጫዋቾቹ በዚሁ የሚቀጥሉ ከሆነ ክለቡ ተጫዋቾችን እስከ መሸጥ የሚያደርስ እርምጃ ሊወስድ ይችላልም ተብሏል።

በርግጥ በተለየ መልኩ የቹአሚኒን እና የባልቬርዴን ጉዳይ አለም አወቀው እንጂ የሎስ ብላንኮቹ ሙሉ የቡድን መንፈስ ኃይለኛ ንፋስ እንደገባበት ታውቋል።

አሁን ላይ ቡድኑ በከፍተኛ ውጥረት ተከፋፍሏል። ሁሉም ተጫዋቾች ከሀገራቸው ዜጋ እና ተመሳሳይ ቋንቋ ከሚያወሩ አጋሮቻቸው ጋር ብቻ ነው ዕርስ በዕርስ እየተነጋገሩ ያሉት ተብሏል።

ማንኛቸውም ተጨዋች አሰልጣኝ አልቪሮኣን እየሰማ እንዳልሆነና
ከአሰልጣኙ ጋርም ንግግር ያቆሙ ተጫዋቾች ቁጥር 8 መድረሱን ታውቋል።
በተጨማሪም "በቀጣይ የቪኒሺየስ እና የምባፔ ፀብ ይጠበቃል" የሚሉ መረጃዎች ከቅርብ ምንጮች እየወጡ ነው። ነገር ግን ምንምኳ እኒህ ወሬዎች ቢኖሩም ኪሊያን ምባፔ ከቪኒ ጁኒየር ጋር ያለው ግንኙነት ጠንካራ እንደሆነ እና እዛ የሚያደርስ ጥል እንደማይፈጠር ገልፀዋል።

ይባስ ብሎ ከ ሰሞኑ በክለቡ አይነኬ በሚመስለው ኬሊያን ሜባፔ ላይ የተጀመረው ዘመቻ ሌላው የሪያል ማድረድ መልበሻ ከፍል ፈተና ሆኗል።

ከሰሞኑኑ አንድ የ ሪያል ማድሪድ ደጋፊ " ሜቫፔ ከሪያል ማድሪድ ይውጣ" የሚል መፈክርን ይዞ 200,000  ድምፆችን ለማግኘት የጀመረው ዘመቻ አሁን ላይ ቁጥሩ ከ40 ሚልየን አልፏል።

ይህም በእግር ኳስ ታሪክ ለአንድ ተጨዋች የተሰበሰበ ከፍተኛው ፊርማ ሲሆን በአንድ ወቅት "አለም ላይ ለሚገኙ ለደሀ ሀገራቶች ተሰጥቶ የነበረው ያልተከፈለ ብድር ይቁም" ተብሎ ተጀምሮ ከነበረው የ ኦንላይን ድምፅ ማሰባሰብ በላይ በልጦ ተቀምጧል። 
በዚህም ምክንያት ይህ የሪያል ማድሪድ ደጋፊዎች ፊርማ የማሰባሰብ ሪከርድ በጊነስ ቡክ ላይ ጭምር መስፈር ችሏል። በጊነስ ታሪክ በኦንላይን ፊርማ ማሰባሰብ ከዚህ ቀደም የተያዘው ሪከርድ 20 ሚልየን ነበር። አሁን የማድሪድ ደጋፊዎች በ24 ሰአታት ውስጥ ብቻ 40 ሚልየን ደርሰው ሪከርዱን ሰብረውታል።

ሆኖም ይህ ሜባፔ ከማድሪድ ይልቀቅ የሚለው ፊርማ በሪያል ማድሪድ ደጋፊዎች ብቻ የተፈረመ መሆኑ ያጠራጥራል። 
ምክንያቱም ሪያል ማድሪድን የሚጠሉ ደጋፊዎች በዋነኝነት ባርሴሎና እና አትሌቲኮ ማድሪድ እንዲሁም ሰብሯቸው የሄደው የፒኤስጂ ደጋፊዎች ሊሳተፉበት ይችላሉ ተብሎ ይታሰባል።

ይሔንን ተከትሎ በርካቶች ሜባፔ በዚህ ደረጃ የተዘመተበት ከደጋፊው ጋር ምን አቃቅሮት ነው? ሲሉ ይጠይቃሉ።
ትልቁ ችግር ደግሞ ሜባፔ ከደጋፊው ጋር ብቻ ሳይሆን ከተጫዋቾችም ጋር ያለው ልዩነት ነው።

የሪያል ማድሪድ ተጨዋቾች በበኩላቸው ከምባፔ ይልቅ ቪኒሺየስ ጁኒየርን እንደ መሪያቸው እንደሚመለከቱት እና ሜባፔን ማግለል መጀመራቸው ታውቋል።

ይህ እንዲሆን ካነሳሱት ምክንያቶች አንዱ ሪያል ማድሪድ ምባፔ በጉዳት ምክንያት ባልነበረባቸው 5 ጨዋታዎች ተከታታይ ማሸነፉ እና ምባፔ ከጉዳት ሲመለስ 6 ጨዋታ አድርገው አንድ ግጥሚያ ብቻ ድል ማድረጋቸውን ተከትሎ በክለቡ ተጫዋቾች እና ደጋፊዎች ዘንድ የምባፔ መኖር እየጎዳቸው እንደሆነ እንዲያምኑ አድርጓቸዋል።

በተጨማሪም ፈረንሳያዊው ኮከብ ኪልያን ሜባፔ ከሰሞኑ ካጋጠመው ጉዳት ቡሀላ የአካል ብቃቱ እስኪመለስ ድረስ በ ማድሪድ ቆይቶ ክትትል ያደርጋል ተብሎ ቢታሰብም እሱ ግን ቀዳሚ ምርጫው ያደረገው ከፍቅረኛው ጋር ሌላ ሀገር ሔዶ አሸሸገዳሜ ማለትን ነበር።

ሜቫፔ በደጋፊው ዘንድ ከጉዳት ለመመለስ ጠንክሮ ይሰራል ተብሎ ሲጠበቅ ከስፔናዊቷ አዲስ የከንፈር ወዳጁ ኤስተር ኤክስፖሲቶ ጋር በመሆን ወደ ጣልያኗ ከተማ ሳርዲንያ አቅንቶ መዝናናትን መምረጡ ደጋፊውን ክፉኛ አበሳጭቶታል።
ያለፉትን አመታት በተቀናቃኛቸው ባርሴሎና ሙሉ ለሙሉ የተበለጡትና ያለምንም ዋንጫ አመቱን እያጠናቀቁ ላሉት ሎስ ብላንኮቹ በዚህ በክለቡ ውስጥ ውጥረት በነገሰበት ጊዜ ይህንን ተግባር መፈፀሙ በርካታ ማድሪዲስታዎችን አስከፍቷቸዋል።

በዛ ላይ ደግሞ ሜባፔ ከሰሞኑ በ ልምምድ ወቅት ከ አርቤሎአ የ ስታፍ አባል ጋር ኦፍሳይድ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዳለ ከነገረው ቡሀላ ቅር ተሰኝቶ አላስፈላጊ ክርክርን መፍጠሩ ሌላ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ መቃቃሩን አባብሶታል። 

በዚህም ደጋፊው በፒኤስጂ ቤት ሳይቀር የነበረውን ባህሪ በማጣቀስ "ቀድሞውኑ በሜዳ ላይ እኔ ብቻ ልታይ የሚል የግለኝነት ባህሪ አለበት" ብለው የሚያስቡት የሎስብላንኮቹ ቤተሰቦች በተጫዋቹ ላይ እንዲዘምቱ አስገድዷቸዋል።

ሜባፔ በሀገሩ ሊግ ፈረንሳይ በቱጃሩ ክለብ ፒኤስጂ ዘንድ ሁሉንም ማድረግ እንዲችል የተፈቀደለት "ሁሉ በእጅህ ሁሉ በደጅህ ፣ ፈረሱም ይሔው ሜዳውም ይሄው" ተብሎ 
እንደስለት ልጅ በስስት የሚታይ የነበረ ቢሆንም አምላክ "እሳቱም ይሄው ፣ ውኃውም ይሔው ፤ እጅህን ወደፈለክበት ስደድ" ተብሎ የተፈቀደለትን መብት ተጠቅሞ
ሜባፔ እጁን ወደእሳት ሰደደ።

ያን ለማንም ባልተፈቀደ ደረጃ እንካ እንዳሻህ የተባለበትን ክለብ ሽራፊ ሳንቲምኳ በሽያጭ ሳያስገኘው ወደ 200 ሚሊዬን ዩሮ የሚጠጋ ገንዘብ አክስሮት በነፃ ወደ ስፔን ማድሪድ ኮበለለ።

ታዲያ ሜባፔን ሁለቴ የጎዳው ነገር ሳይዘገይ መጣ። በዋናነት ወደማድሪድ ሔዶ ማግኘት የፈለገውን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ የቀድሞ ክለቡ በሔደበት ቅፅበት ማሳካት የቻለ ሲሶን ዘንድሮም ለፍፃሜው ደርሷል።

ሜባፔ ግን አምናም ዘንድሮም በሩብ ፍፃሜው ከውድድሩ መድረክ ለመሰናበት ተገዷል። ይባስ ብሎ እናት ክለቡ የሰጠውን ገነት የመሰለ ምቾት እርግፍ አድርጎ የሔደበት ክለብ በሚሊየን የሚቆጠሩ ደጋፊዎች "ልቀቅልን" ብለው ፊርማ እያሰባሰቡ ነው።

ይሕ ለሜባፔ እጅግ ከባድ ስሜት መፍጠሩን ለማወቅ የግድ በሱ ቦታ መሆን ሚጠይቅ አይደለም።

ሆኖም ምንም እንኳን በማድሪድ ሰዎች እና ደጋፊዎች እንዲሁም በፈረንሳያዊው ኮከብ መካከል ከባድ ውጥረት ቢኖርም ክለቡ ግን ተጫዋቹን የመሸጥ ምንም አይነት እቅድ እስካሁን የላቸውም። 
ነገር ግን ክለቡ ከገባበት ውጥቅጥ እንዲዎጣ ፔሬዝን ትልቅ ስራ ይጠብቃቸዋል።

የክለቡ ፕረዚዳንት ፔሬዝ ለዚህ ትልቅ ችግርም ሆነ ለዋንጫ እጦቱ ችግር  ዋና መፍትሄ አድርገው የሚቆጥሩት ፣ ከዚህ ቀድም በዚሁ በሪያል ማድሪድ አሰልጣኝ ሆኖ የሰራውን ፖርቱጋላዊውን አንጋፋ አሰልጣኝ ጆዜ ሞሪኒዮን ዳግም ወደ ቤርናባው መመለስን ነው።

በርግጥ በሁለቱ አካላት መካከል ንግግሮች መደረጋቸው ታውቋል።

ነገር ግን the special one ወደ ማድሪድ ቤት የሚመጡ ከሆነ ዲስፕሊናዊ ውሳኔዎችን የማስተላለፍ ሙሉ መብት ማለትም የተጫዋቾችን ቋሚ አሰለፍ የመምረጥ እና የማሥቀመጥ ጉዳይ ላይ የማንንም ጣልቃ ገብነት እንደማይፈልጉ አሳውቀዋል።

ጆዜ ሞሪኖ ወደክለቡ ከማምራታቸው በፊት የፈለጉትን ሁሉ ማድረግ እንዲችሉ ሙሉ ስልጣን እንዲሰጣቸው ሲጠይቁ በተለዬ  ያቀረቡት መስፈርትም "የፈለግሁትን ተጫዋች ማሰልፍ እችላለሁ ፣ ያልፈለኩትን ተቀያሪ ማስቀመጥ እችላለሁ ፣ ይሄ ተጫዋች ተቀያሪ አይሆንም ፣ ይሄ ተጫዋች መነካት አይችልም ማትሉኝ ከሆነ ብቻ ነው ወደ ማድሪድ የምመለሰው።" ሲሉ በምላሻቸው ማሳወቃቸው ተሰምቷል።

ማድሪድ እስካሁን ባለው ሁኔታ ለሞሪኖ የሰጡት ምላሽ በይፋ ባይገለፅም
ነገር ግን አሰልጣኙ ወደቀድሞ ቤታቸው መመለሳቸው የሚቀር አይመሥልም።

በተለይ ደግሞ ቀጣይ እሁድ ከምን ጊዜም ተቀናቃኛቸው ባርሴሎና ጋር በሚያደርጉት የአሌ'ክላሲኮ ጨዋታ ላይ በዚህ መንፈስ መግጠማቸው ለቡድኑ እንደ መጥፎ አጋጣሚ እየተቆጠረ ሲሆን ፤ ይባስ ብሎ ከተሸነፉ ወይም አቻ ከወጡ ፣ ባርሴሎና የ2025/26 የላሊጋው ሻምፒዮናነቱን ያረጋግጣል።
ይህ ደግሞ ለሪያል ማድሪድ ሌላ ውጥረትን የሚያመጣባቸውና ለውሳኔ እንዲቸኩሉ የሚያደርጋቸው ይመሥላል።

ይህንን ተከትሎ የክለቡ ፕረዚዳንት ፔሬዝ ለሁሉም አመራሮች ፣ የአሰልጣኝ ቡድን አባላት እና ተጫዋቾች በሙሉ ዛሬ ቀን 8:00 ሰዓት ላይ ስብሰባ ጠርተው በክለቡ አዳራሽ ማነጋገራቸው ታውቋል።

በዚህ ስብሰባም ሁሉም ተሰታፊዎች ስልካቸውን ይዘው እንዳይገቡ የተደረገ ሲሆን ፣ ለሚዲያዎችም በሩ ዝግ እንደነበር ታውቋል።

እነሆ በከፍተኛ የቀውስ ማዕበል እየተናወጠ ያለው የሪያል ማድሪድ ግዙፍ መርከብ በምን መፍትሔ መቼስ ይረጋጋ ይሆን?

 

A
ስለ ጸሐፊው

Administrator

12 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።