Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
አለም አቀፍ ትንታኔ

ኢራን በኩዌት እና ባህሬን ላይ የድሮን ጥቃት ፈፀመች

SM Samuel Mulgeta Jun 3, 2026 Updated 3h ago 2 ደቂቃ ንባብ 270 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
ኢራን በኩዌት እና ባህሬን ላይ የድሮን ጥቃት ፈፀመች

የአሜሪካ ጦርም ለዚሁ ጥቃት በሰጠው ምላሽ በሆርሙዝ ሰርጥ አቅራቢያ በምትገኘው የኢራኗ ቃሺም ደሴት ላይ የአጸፋ እርምጃ መውሰዱ ተሰምቷል፡፡

የአሜሪካና የኢራን ወታደራዊ ውጥረት ማገርሸቱን ተከትሎ በሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥና በኩዌት አውሮፕላን ማረፊያ ላይ አዳዲስ የድሮንና ሚሳዔል ጥቃቶች እንደተፈጸሙ በዛሬው እለት ይፋ ሆኗል።


በዚህ በኢራን  የድሮን እና ሚሳኤል ጥቃት ሳቢያ የኩዌት ዋና ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት ለአጭር ጊዜ አገልግሎት ያቋረጠ ሲሆን በጥቃቱ የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉና በርካታ ሰዎች መቁሰላቸው ተረጋግጧል።



በጥቃቱ በሰው ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ በህንፃው ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን የኩዌት መከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጄኔራል ሳኡድ አብዱልአዚዝ አል-ኦታይቢ አረጋግጠው አየር መንገዱ በረራዎችን አቋርጦ ወደ ሌላ አቅጣጫ ለመቀየር መገደዱን ገልጸዋል።

Advertisement
Your ad could be here — contact us



ትናንት ምሽት የተጀመረውን የሚሳኤል ልውውጥ ተከትሎ የአሜሪካ እና የባህሬን መከላከያ ኃይሎች የአሜሪካ ባህር ኃይል አምስተኛ መርከቦች ዋና መሥሪያ ቤት የሚገኝባትን ባህሬንን ኢላማ ያደረጉ ሦስት የሚሳኤል እና የድሮን ጥቃቶችን በስኬት ማክሸፋቸውን የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ አስታውቋል።


አሜሪካ በሰጠችው ራስን የመከላከል ምላሽ በሆርሙዝ ሰርጥ አቅራቢያ በምትገኘው የኢራኗ ቃሺም ደሴት ላይ በሚገኝ ወታደራዊ ጣቢያ እና የኮሙኒኬሽን ታወር ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሟም ተገልጿል።


በተጨማሪም አሜሪካ በሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ ላይ በጣለችው የባሕር እገዳ ሳቢያ ወደ ኢራን ስታመራ በነበረች መርከብ ላይ የሚሳዔል ጥቃት መሰንዘሯ ተገልጿል።


ይህንን ተከትሎ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከፍተኛ ዲፕሎማት አንዋር ጋርጋሽ በኤክስ  ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ይህ የኢራን ጥቃት በአንድ ሀገር ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ላይ የተሰነዘረ ነው በማለት የባሕረ ሰላጤው ሀገራትጽኑ እና የተባበረ አቋምእንዲወስዱ አሳስበዋል።



የኢራን ፋርስ እና ታስኒም የዜና ወኪሎች እንደዘገቡት በሊባኖስ ከሄዝቦላህ ጋር ያለው ውጥረት በመጨመሩ ኢራን ከአደራዳሪዎች ጋር ያላትን ግንኙነት ያቆመች ሲሆን የኢራን ባለሥልጣናት የተኩስ አቁም ድርድሩ እንዲቀጥል መጀመሪያ በሊባኖስ ያለው ውጊያ መቆም አለበት የሚል ጽኑ አቋም ይዘዋል።


ይሁን እንጂ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ድርድሩ መቋረጡን አስተባብለው "ንግግሩ ቀጥሏል፤ ለኢራን እንደነገርኳት ስምምነት የምታደርግበት ጊዜ አሁን ነው" ብለዋል።



በአሁኑ ወቅት የእስራኤል ጦር ከተኩስ አቁም ስምምነቱ ውጭ ወደ ሊባኖስ በረዥም ዘመን ታሪኩ ያልገባበትን ያህል እየገባ ሲሆን ይህ የሊባኖስ ጉዳይ በትራምፕ እና በኢራን መካከል ለሚደረገው ሰፊ ስምምነት ዋና ማነቆ ሆኗል።


ይህ በእንዲህ እንዳለ የፖለቲካ ውጥረቱ በዲፕሎማሲው መድረክም የቀጠለ ሲሆን የአሜሪካ የውጭ ሁኔታ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ለኮንግረስ በሰጡት ማብራሪያ አሜሪካ በኢራን ላይ የጣለችውን ማዕቀብ ማቃለል የምትችለው ሀገሪቱ ሙሉ በሙሉ የኑክሌር መርሃ ግብሯን ስታቆም ብቻ መሆኑን በይፋ አስታውቀዋል።

 

SM
ስለ ጸሐፊው

Samuel Mulgeta

41 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።