በመኮንን አልማው
ከሰሞኑኑ የኢትዮጵያ ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች ተደርገው ነበር።
ሰኞ በተደረገ የትግራይ ደርቢ ጨዋታ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ መቐለ 70 እንደርታን በፍፁም ቅጣት ምት አሸንፈው ማለፍ ችለዋል።
ቀጥሎ ማክሰኞ በተደረገ የኢትዮጵያ ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ሲዳማ ቡና ኢትዮጵያ መድንን በመለያ ምት 4ለ3 ማሸነፍ ችሏል።
ውጤቱን ተከትሎ ሲዳማ ቡና እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ዋንጫ ፍፃሜ ተፋላሚ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
የፍፃሜው አሸናፊ ክለብም ኢትዮጵያን ወክሎ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ውድድር ላይ የሚሳተፍ ይሆናል።
ታዲያ በዚህ የኢትዮጵያ ጨዋታ መድረክ ማክሰኞ ዕለት በተካሔደው የመድን እና የሲዳማ ቡና ጨዋታ ላይ አንድ አነጋጋሪ ሁነት ተፈጥሮ ነበር።
ከጨዋታው በላይ ትኩረት የሳበው እና የስፖርቱን ቤተሰቡ ያስቆጣው ይህ ጉዳይም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የኢትዮጵያ መድን የግራ መስመር ተከላካይ የሆነው ያሬድ ካሳየ ያሳየው የስነ-ምግባር ግድፈት ነበር።
በጨዋታው ወቅት የኢትዮጵያ መድን አሰልጣኝ ገብረመድህን ሀይሌ የክለቡ የግራ መስመር ተከላካይ የሆነውን ያሬድ ካሳዬን 33ኛ ደቂቃ ላይ ቀይረው ያስወጡታል።
ተጨዋቹም ተቀይሮ ሲወጣ አሰልጣኙን እና የቡድን አባላቱን ክብር በሚነካ መልኩ የለበሰውን ማልያ ወርውሮ በመጣል እና የስድብ ቃላት በመሰንዘር ከስፖርታዊ ጨዋነት ፍፁም የራቀ ድርጊት ፈፅሟል።
በመቀየሩ ፍፁም ደስተኛ ያልነበረው ያሬድ በአሰልጣኙ ፊት ወርውሮ የጣለውን ማልያ ለማንሳት ሳይሞክር በቀጥታ ተቀያሪ ተጨዋቾች ወደሚቀመጡበት ቦታ ይሔዳል።
ተቀያሪ ወንበር ላይ ተቀምጦም አሰልጣኙን መሳደብ እና ከቡድኑ መሪው መስፍን አህመድ ጋር እሰጣገባ ውስጥ ይገባል።
ይህ ያልተጠበቀ የተጨዋቹ ድርጊትም በበርካቶች ዘንድ ቁጣ ለማስነሳት እና መነጋገሪያ ለመሆን በቅቷል።
ብዙዎቹ በማህበራዊ መገናኛ ላይ በመውጣት "የሃገራችን እግር ኳስ በሚፈለገው ልክ የማያድገው እንደዚህ ያሉ ስርዓት የጎደላቸው እብሪተኛ ተጨዋቾች መኖራቸው እና ለጥፋታቸው አስተማሪ እርምጃ አለማግኘታቸው ነው" በማለት ጠንካራ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።
በጣም አስገራሚው ነገር ደግሞ ይህን ፈፅሞ ተገቢ ያልሆነ ተግባር የፈፀመው ያሬድ ካሳየ እዚህ ደረጃ እንዲደርስ ብዙ እድል እየሰጠ ያሳደገው የሙያ አባቱ አሰልጣኝ ገብረ መድህን ሃይሌ ላይ መሆኑ ነው።
ነገር ግን አሰልጣኙ በዚህ ለፍፃሜ ለመብቃት በሚያደርጉት ወሳኝ ጨዋታ እንደቡድን ድል ለማድረግ የራሣቸውን ታክቲክ በሚጠቀሙበት ጊዜ አንድ ግለሰብ ለምን ተቀየርኩ በማለት ያሳየው ተግባር በብዙዎች ዘንድ አስፈርዶበታል።
"የበላበትን ወጭት ሰባሪ"ም አስብሎታል።
እውነት ነው የመጫዎት ፍላጎት እና ኳስ ላይ ስሜታዊነት ሁሌም አለ!
ነገር ግን የአንዲት ሀገር የብሔራዊ ቡድን አባል የሆነ ፣ በጣም ውለታ በዋለለት አሰልጣኝ እየሠለጠነ ፣ በሀገሪቱ የጨዋታ አስተላላፊ ቴሌቭዥን ጣቢያ ለህዝብ በቀጥታ እየታየ 'ተከታዩቼ ከእኔ ምን ይማራሉ' ሳይል በፀሐይ በጉባይ ያንን በማድረጉ ማንንም አላስደሰተም።
ይልቅስ የሀገሪቱ ከፍተኛ የእግር ኳስ መድረክ ላይ እንደመጫወቱ እና የብሔራዊ ቡድኑ አባል እንደመሆኑ ስሜቱን ተቆጣጥሮ አርዓያነቱን ለማሳየት ባለመቻሉ በርካታ ትችቶች እንዲሰነዘሩበት እና ጫናዎች እንዲበረቱበት በር ከፍቷል።
በርግጥ ተጫዋቹ ያሬድ ካሳዬ ጥፋቱን አምኖ በድርጊቱ ተፀፅቶ የተተፈጠረውን ክስተት በመግለፅ ይቅርታ ጠይቋል።
“ስሜታዊ ሆኜ ላደረኩት ነገር በጣም ይቅርታ እጠይቃለሁ። ይህ ከእኔ የማይጠበቅ ነገር ነው። ለዚህም አሰልጣኜን ገብረመድኅንን ፣ ተጫዋቾችን ፣ ክለቡን እና መላውን የስፖርት ቤተሰቡን ይቅርታ ማለት እፈልጋለሁ። ባደረኩት ነገር በጣም ተፀፅቻለሁ።" በማለት ሀሳቡን ገልጿል።
ሆኖም ግን ጉዳዩ በሰፈር ጨዋታዎች ላይ የተፈፀመ ባለመሆኑ እና በሀገሪቱ ትልቅ መድረክ ላይ የተከሰተ መሆኑን ተከትሎ በቀላሉ ከመታለፍ ይልቅ አፋጣኝ ርምጃ እንዲወሰድበት ተደርጓል።

በዚህም ክለቡ ኢትዮጵያ መድን ተጫዋቹን በፍጥነት ከካንፕ ሲያሰናብት ፣ ፌዴሬሽኑ በበኩሉ የገንዘብ ቅጣት ጥሎበታል።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ያሬድ ካሳዬ ማልያውን አውልቆ በመጣሉ ላሳየው የስነምግባር ጥሰት በሚል 10 ሺ ብር ቅጣት እንደጣለበት አውቀናል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በቀጣይ ግንቦት 29 እና ሰኔ 2 ለሚያደርገው የወዳጅነት ጨዋታ አሰልጣኝ ዩሐንስ ሳህሌ ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ ሲያደርጉ ያሬድ ካሳየን ከስብስቡ ውጪ አድርገውታል።
የዋልያዎቹ አለቃ ዮሐንስ ሳህሌ ተጫዋቹን በስብሰባቸው ውስጥ ማካተት ያልቻሉትም በዚሁ የማክሰኞው ተግባሩ ምክንያት ስለመሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በዛች ቅጽበት ስሜቱን ባለመቆጣጠሩ ምክንያት ይህ ሁሉ የትችት ናዳ የደረሰበት እና ቅጣት የተጣለበት ተጫዋቹ ምናልባት በቀጣይ ተጨማሪ ቅጣቶች ሊጣሉበት እንደሚችሉ ይጠበቃል።
ሆኖም ጉዳዩ የስፖርቱን ቤተሰብ ከሁለት የከፈለ ሆኗል።
ገሚሱ "ክለቡም ሆነ ፌደሬሽኑ ይህንን መሰል እብሪተኛ ተጫዋች ድጋሜ ወደ ሜዳ እንዳይመለስ አድርጎ መቅጣት አለበት" በማለት ጠንካራ ተቃውሞ ይሰነዝራሉ።
ገሚሶቹ ደግሞ "አዎ ተጫዋቹ ከእረፍት በፊት በረመዳን ዩሱፍ ሲቀየር ለምን ተቀየርኩ በሚል ማሊያውን አውልቆ በመጣልና አሰልጣኙን በመሳደብ ነውር ሲፈጽም በቀጥታ ስርጭት ላይ ታይቷል! ይህ ፈፅሞ ተገቢ አይደለም!" በማለት ድርጊቱን ይቃዎሙና "ነገር ግን ልጁ ወጣት እና ተስፈኛ በመሆኑ ትምህርት እንዲሆነው ተደርጎ በይቅርታ ቢታለፍ" ሲሉ የምህረት ድምጽ ያሰማሉ።
የሆነው ሆኖ የስፖርቱን ቤተሰብ ለሁለት የከፈለው ይህ ክስተት የወቅቱ መነጋገሪያ ሆኗል። እናም የሚመለከተው አካል የልጁን ተስፈኛነት ተመልክቶ ፣ የሰው ልጅ ከስህተት እንደማይድን ተረድቶ ፣ በይቅርታ አስተምሮ ወደ ስራው ይመልሰዋል? ወይስ ለእግር ኳሱ የዲሲፒሊን ጥራት እና ለሌሎች ማስተማሪያነት በማድረክ በከፋ መራር እርምጃው ይፀናል? ከሚለው በተጨማሪ የተጫዋቹ የወደፊት እጣ ፋንታ ትኩረት የሚይዝ ተጠባቂ ጉዳይ ነው።
መጨረሻው በምን ይቋጫል? የሚለውን ጥያቄ ጊዜ እስኪመልስልን በቸር ያቆየን።