በመኮንን አልማው!
በ10 አመታት ውስጥ 20 ዋንጫዎችን የሰበሰቡት የክለቡ ታሪካዊ እና የአለም እግር ኳስ አይረሴ አሰልጣኝ የሆኑት ፔፕ ጋርዲዮላ እንግሊዝን የመሰናበታቸው ጉዳይ እርግጥ ሆኗል።
ክለቡ ማንችስተር ሲቲም የታሪካዊ አሰልጣኛቸውን መልቀቅ አሰመልክቶ በተዘጋጀ የስንብት ቪድዮ ጉዳዩ እውነት መሆኑን አረጋግጧል።
ፔፕ ጋርዲዮላ በበኩላቸው ከክለቡ ጋር መለያየታቸውን ለማሳወቅ የተዘጋጀውን የስንብት ቪዲዮ ስክሪፕቱን ራሳቸው እንደፃፉት ታውቋል።
ስፓኒያርዱ ታክቲሽያን ሶስት ደቂቃ ከሰላሳ ሰከንድ በወሰደው የስንብት ቪዲዮ በክለቡ የነበራቸውን ቆይታ ኪነ-ጥበባዊ ለዛ በተሞላባቸው ቃላቶች ከሽነው ገልጸውታል።
ይህ የፔፕ ጋርዲዮላ ስንብት ቪዲዮም በዚህ ሰዓት በማንችስተር ሲቲ የማህበራዊ ትስስር ገፆች ላይ ለእይታ ቀርቧል።
የአውሮፓ እግር ኳስ ፈላጭ ቆራጭ የሆኑት አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ በማንችስተር ሲቲ ቤት የ10 አመት ቆይታቸው 20 ዋንጫዎችን በማሳካት ስኬታማ ጊዜ አሳልፈዋል።
በዚህም አሰልጣኙ በማንችስተር ሲቲ ታሪክ በርካታ ዋንጫዎችን ያሳካ አሰልጣኝ ሆነው በእሁዱ የአስቶን ቪላ ጨዋታ ክለቡን የሚሰናበቱ ይሆናል።
በርግጥ ምንም'ኳ አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ከማንችስተር ሲቲ የአሰልጣኝነት ስራ ቢለቁም አዲስ ሀላፊነት እንደተሰጣቸው ተሰምቷል።
ፔፕ ጋርዲዮላ በቀጣይ የሲቲ ፉትቦል ግሩፕ ግሎባል አምባሳደር በመሆን መሾማቸው ነው ይፋ የተደረገው።
በቀጣይም ፔፕ በሲቲ ፉትቦል ጎሩፕ ስር ላሉ ክለቦች ቴክኒካል ምክሮችን በመለገስ በጋራ እንደሚሰሩ ተነግሯል።
በተጨማሪም ማንችስተር ሲቲ የኢትሀድ ስታዲየምን አንድ ክፍል በአሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ስም መሰየሙን እወቁልኝ ብሏል።
ክለቡ እያስፋፋ የሚገኘው የስታዲየሙ የሰሜን ክፍል "The Pep Guardiola Stand" ተብሎ መሰየሙ ተገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም ሀውልት እንደሚገነባላቸው ማንችስተር ሲቲ ይፋ አድርጓል።
ሀውልቱም "The Pep Guardiola Stand" ተብሎ በተሰየመው የስታዲየሙ ክፍል አቅራቢያ እንደሚቆም ተገልጿል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ንግግር ያደረጉት የማንችስተር ሲቲው ሊቀመንበር አል ሙባረክ በሰጡት አስተያየት “ ጋርዲዮላ ማንችስተር ሲቲን ብቻ አይደለም ያቀናው እግርኳስን ጭምር ነው“ ሲሉ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ በበኩላቸው በማንችስተር ሲቲ አሰልጣኝነታቸው የመጨረሻ እንደሆነ የሚገመተውን አስተያየታቸውን ለጋዜጠኞች ሰጠዋል።
ስፔናዊው አሰልጣኝ ማንችስተር ሲቲን እንደሚለቁ ይፋ ባደረጉበት በዚህ ወቅት በሰጡት አስተያዬት “ ለምን እንደምለቅ አትጠይቁኝ! ምክንያቱም የተለየ ምክንያት የለኝም! ነገር ግን ለመልቀቅ ጊዜው አሁን መሆኑን አውቃለሁ ” ሲሉ ተናግረዋል።
''ምንም ነገር ዘላለማዊ አይደለም። ዘላለማዊ ቢሆን ኖሮ እዚህ እሆን ነበር" ያሉት ጋርዲዮላ "ዘላለማዊ የሆነ ምንም ነገር የለም ሁሉም ነገር አላቂ ነው'' ሲሉ ተናግረዋል።
ፔፕ ጨምረው በሰጡት ቃል “በቀጣይ የውድድር አመት እረፍት አደርጋለሁ! ላልተወሰነ ጊዜ ክለቦችን አላሰለጥንም" ያሉ ሲሆን “በማንችስተር ሲቲ በነበረኝ ቆይታ እኮራለሁ ፤ ክለቡን የምለቀው ትክክለኛው ጊዜ እንደሆነ ስለተሰማኝ ነው" ሲሉ አክለዋል።
ክለቡ አዲስ አሰልጣኝ እና አዲስ ጉልበት እንደሚያስፈልገው የተናገሩት ፔፕ ቀጣዩ አሰልጣኝ (ኢንዞ ማሬስካ) አስደናቂ ተጨዋቾች እንደሚኖሩት ገልጸዋል።
"አሁን ምንም ጉልበት የለኝም የነበረኝ አቅም ከአስር አመት ስራ በኋላ ጥሎኝ ሄዷል" የሚሉት አሰልጣኙ ስራቸው በጣም አድካሚ መሆኑን በመግለጽ እረፍት እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁመዋል።
እሁድ ደጋፊዎቹን በደንብ እንደሚሰናበቱ እና ሜዳ ላይ ሁሉንም ማቀፍ እንደሚፈልጉ የገለጹት ፔፕ "በማንችስተር ሲቲ ቤት 20 ዋንጫ አሸንፊያለሁ ነገር ግን ትላንት ከዴብሩይን የደረሰኝ የስልክ ጥሪ ለእኔ ትልቅ ትርጉም አለው" ብለዋል።
አክለውም "በእንግሊዝ እግርኳስ ታሪክ ታላቁ አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ናቸው” ያሉት አሰልጣኙ “ትላንት ከሰር አሌክስ ፈርጉሰን መልእክት ደርሶኛል! ይህም በጣም አስደስቶኛል” ሲሉ ተደምጠዋል።
በቀጣይ አሰልጣኝ ኢንዞ ማሬስካ ጋርዲዮላን ተክተው ማንችስተር ሲቲን የሚረከቡ ይሆናል።
ሌላው ፔፕ ጋርዲዮላ ማንችስተር ሲቲን መሰናበታቸውን ተከትሎ የሻምፒዮኖቹ አሰልጣኝ ሚካኤል አርቴታ በፕሪሚየር ሊጉ በአንድ ክለብ ለረጅም ግዜ መቆየት የቻለው አሰልጣኝ ሆነዋል።