በመኮነን አልማው
የ2025/26 የውድድር ዘመን የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ አሸናፊ መሆኑን ያረጋገጠው የአርሰናል ተጫዋቾች እና ደጋፊው ምድርን እያስጨነቀ ነው።
ከ22 አመታት በኋላ ሻምፒዮን ለሆኑት መድፈኞቹ ከእየአቅጣጫው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክቶች እየጎረፉላቸው ነው።
የአርሰናል ብቸኛው የዋንጫ ተፎካካሪ የነበረውና ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንችስተር ሲቲ ትላንት ምሽት ከበርንማውዝ ጋር ያደረገውን ጨዋታ 1አቻ ማጠናቀቁን ተከትሎ አርሰናል ሻምፒዮን መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ አለም ተጨንቃለች ተጠባለች።
የምሽቱ የጨዋታው ማብቂያ ፊሽካ ከተነፋ ጀምሮ በመላው አለም የተነቃነቀው የአርሰናል ደጋፊዎች የደስታ ማዕበል ሌሊቱን "ንጋ አልነጋም" በሚል ሙግት ፍጥጥ ብለው አድረዋል።
በዚያ ቅጽበት ከአዲስ አበባ ቦሌ እስከ ለንደን ሶብሃ ሪያሊቲ (የመድፈኞቹ የልምምድ ማዕከል) የተሰራጨው በምስል የተደገፈ የደጋፊው እና የተጫዋቾችን ደስታ አገላለጽ የአለም የመገናኛ መረቦች ሁሉ በሚገርም ፍጥነት እየተቀባበሉት ነው።
ከአራቱም አቅጣጫ እንደአውሎ ንፋስ የተዛመተው እና እንደ ሰደድ እሳት መቆሚያ የሌለው የሚመስለው የደጋፊው ንቅናቄ ሲታይ አለም ሁሉ የአርሰናል ደጋፊ ብቻ ይመስላል።
ከሀገራችን ኢትዮጵያ ጀምሮ በመላው አለም ያሉ ከዚህ በፊት የአርሰናል ደጋፊ እንደነበሩ የማይታዎቁ ጭምር የአርት ፣ የስፖርት ፣ የፖለቲካ ፣ የንግድ እና የተለያዬ ዘርፍ ላይ ያሉ አለም አቀፍ ዝነኛ ሰዎች ከያሉበት ሆነው ደስታቸውን ገልጸዋል።
ደጋፊዎች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች በርካታ አካላትም ለመድፈኞቹ "እንኳን ደስ አላችሁ ፣ ይገባችኋል" የሚሉ መልካም ምኞቶች ማህበራዊ መገናኛ መረቡን አጨናንቀውታል።
አርሰናል አንድ ጨዋታ እየቀረው ከተከታዩ ማንችስተር ሲት በ4 ነጥቦች እርቆ በ82 ነጥቦች ዋንጫውን እንዳሸነፈ ከተረጋገጠ በኋላ ሲቪያ ፣ ናፖሊ እና ሌቨርኩሰን ለመድፈኞቹ እንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት ልከዋል።
የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪው አላን ሺረር " አርሰናሎች እንኳን ደስ ያላችሁ" የሚል መልዕክቱን ልኳል።
ሪያል ሶሲዳድ በበኩሉ ለአሰልጣኝ ሚካኤል አርቴታ ፣ ለካፒቴን ኦዴጋርድ ፣ ለሜሪኖ እና ለዙቢሜንዲ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።
ሌቨርኩሰን ለቀድሞ ልጃቸው ፒዬሮ ሂንካፔ "እንኳን ደስ ያለህ" ብለውታል።
የፈረንሳይ ሊግ ዋን በበኩሉ ለቀድሞ ተጨዋቾቹ እና ለአሁኑ የአለማችን ምርጥ የመሃል ተከላካይ ጥምረቶች ለማጋሌሽ እና ለሳሊባ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክቱን ልኳል።
የቀድሞው መድፈኛ የአሁኑ የሪያል ማድሪድ ተጫዋች ዳኔ ሴባዮስም እንዲሁ ለቀድሞ ክለቡ መልካም ምኞቱን ገልጿል።
ትላንት ማንችስተር ሲቲን ነጥብ አስጥለው አርሰናል ሻምፒዮን ያደረጉት እና ለራሳቸውም የአውሮፓ መድረክ ተሳታፊነታቸውን ያረጋገጡት በርንማውዞች በበኩላቸው በገፃቸው ላይ ግቧን ያስቆጠረውን የክሩፒን ፎቶ ተጠቅመው አብሮነታቸውን ገልፀዋል።
ስለ ወጣት ተጫዋች ካነሳን ደግሞ አንድ አስገራሚ ብላቴና ጠቅሰን ማለፍ ግድ ይለናል። እሱም የመድፈኞቹ እና የወደፊት የእግር ኳሱ አለም ተስፋ የሆነው ማክስ ዶውማን ነው። ይህ ሰው ገና በ16 አመት የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ በማንሳት አዲሥ ሪከርድ አስመዝግቧል።
ቬክቶር ዮክሬሽ በበኩሉ በተከታታይ 3 አመታት የሊግ ዋንጫዎች ማሸነፍ ችሏል። ሁለቱ በፖርቹጋል ሊግ በስፖርቲንግ ሊዝበን የተመዘገበ መሆኑ አይዘነጋም።
ካይ ሃቨርትዝ ፣ ኬፓ እና ኖኒ ማዱኬ ቼልሲን ለቀው ወደ አርሰናል ከተቀላቀሉ በኋላ የፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ሆነዋል።
ሌላው በመድፈኞቹ ቤት አሁን የተሰማው ሰበር ዜና ደግሞ ግብ ጠባቂው ኬፓ አርዛባላጋ ሙሉ መስፈረቱን ባለማሟላቱ ምክንያት የሊጉ የአሸናፊነት ሜዳሊያ እንደማይሰጠው ይፋ ተደርጓል።
የሆነው ሆኖ አሁን ላይ በአሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ የሚመራው አርሰናል ከ22 አመታት በኋላ ለ14ኛ ጊዜ የእንግሊዝ የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ አንስቷል።
የዋንጫው ብቸኛ ተፎካካሪ የነበረው ማንችስተር ሲቲ 2ኛ እንዲሁም ማንችስተር ዩናይትድ 3ኛ ደረጃ በመያዝ የውድድር አመቱን ማጠናቀቃቸው ተረጋግጧል።
ተወዳጁ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የዘንድሮው የውድድር ዘመን የፊታችን እሁድ ይጠናቀቃል።