የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የቻይናው መሪ ዢ ጂንፒንግ አዲስ ዓይነት የባለብዙ-ፅንፍ ዓለም ለመገንባት የሚያስችለውን የጋራ መግለጫ በዛሬው እለት በቤጂንግ ከተማ ተፈራርመዋል።
ይህ ስምምነት ይፋ የተደረገው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቻይና ያደረጉትን ጉብኝት ምንም ዓይነት ዋና ስምምነት ሳይቋጩ ካጠናቀቁ ከጥቂት ቀናት በኋላ መሆኑ ለዋሽንግተን የተላከ ጠንካራ የፖለቲካ መልዕክት ተደርጎ ተወስዷል።
ከቀናት በፊት በተደረገው በዚህ ጉባኤ በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እና የኃይል አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያለው የሆርሙዝ ሰርጥ ጥበቃን ጨምሮ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ዋይት ሀውስ አስታውቆ ነበር።
በዚህም ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ቻይና በባህር ሰርጡ ላይ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚደረገውን ማንኛውንም ጥረት እንደምትቃወም ገልጸው በተለይም ቻይና በቀጣይ በሆርሙዝ ላይ ያላትን ጥገኝነት ለመቀነስ ተጨማሪ የአሜሪካን ዘይት ለመግዛት ፍላጎት እንዳላት ተናግረዋል።
የታይዋን ጥያቄ በቻይና እና በአሜሪካ ግንኙነት ውስጥ በጣም አስፈላጊው ጉዳይ ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ጉዳዩ በአግባቡ ካልተያዘ አጠቃላይ የሁለትዮሽ ግንኙነቱ አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል ማሳሰባቸውን በወቅቱ በስፋት ሲዘገብ ነበር።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በበኩላቸው ከፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ጋር ያደረጉትን ውይይት እጅግ አዎንታዊ እና ውጤታማ ሲሉ የገለጹት ሲሆን በሁለቱ ሀገራት መካከል በጣም ልዩ ግንኙነት እየተፈጠረ ነው ብለው ነበር።
ነገር ግን በዛሬው የሩሲያ እና ቻይና ውይይት ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ የቻይና እና ሩሲያን ግንኙነት ለታላላቅ ኃያላን አገራት ግንኙነት እንደ አርአያ የጠቀሱት ሲሆን አሜሪካን በግልጽ ባልጠቆመ መልኩ “አንድ ወገንተኝነት እና የበላይነትን የመፈለግ አዝማሚያዎች በዓለም ላይ እየተስፋፉ መሆናቸውን” አስጠንቅቀዋል።
ሁለቱ መሪዎች በጉባኤው ወቅት እ.ኤ.አ በሐምሌ 2001 የተፈረመውን የሩሲያ-ቻይና የበጎ ጎረቤትማማችነት የወዳጅነት እና የትብብር ስምምነት ውል ያደሱ ሲሆን ስትራቴጂካዊ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ተስማምተዋል።
ይሁን እንጂ ሁለቱ ወገኖች ከምዕራባውያን የሚሰነዘርባቸውን ጫና ለመመከት የጋራ አቋም ቢያሳዩም ሩሲያ ለዓመታት ስትወተዉት የነበረውንና ፓወር ኦፍ ሳይቤሪያ 2 የተሰኘውን ግዙፍ የጋዝ ማስተላለፊያ መስመር ግንባታን በተመለከተ አሁንም ቢሆን ስምምነት ላይ መድረስ አልቻሉም።

በሌላ በኩል በመካከለኛው ምስራቅ የተከሰተውን የኢራን ጦርነት አስመልክቶ ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር ባደረጉት ውይይት በአካባቢው ተጨማሪ ግጭቶች መፈጠራቸው የማይመከርና አደገኛ መሆኑን ገልጸው በአስቸኳይ አጠቃላይ የተኩስ አቁም ስምምነት መደረግ እንዳለበት አጽንኦት መስጠታቸውን ዘ ሞስኮ ታይምስ ዘግቧል።
ሁለቱ ሀገራት ይሄንን ቢሉም በኢራን ላይ የሚሰነዘር ማንኛውም አዲስ ወታደራዊ ጥቃት አሁን ያለውን ግጭት ከመካከለኛው ምስራቅ ቀጣና ባሻገር በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያስፋፋው የኢራን አብዮታዊ ዘብ አስጠንቅቋል።
አብዮታዊ ዘቡ በዛሬው እለት ባወጣው ይፋዊ መግለጫ አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ከደረሰባቸው ተደጋጋሚ ስትራቴጂካዊ ሽንፈቶች ትምህርት አለመውሰዳቸውን ገልጿል።
ጠላቶቻችን በዓለም ላይ ከፍተኛ ወጪ ከሚወጣባቸው የሁለት አገራት ጥምር ጦር ኃይሎች ጋር በመሆን ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው ጥቃት ቢሰነዝሩብንም እኛ ግን በአንጻሩ የአብዮቱን ሙሉ አቅም ገና ጥቅም ላይ አላዋልንም ሲል መግለጫው ጠቁሟል።
በተጨማሪም አሁን ላይ በኢራን ላይ የሚሰነዘር ማንኛውም ዓይነት ወታደራዊ ትንኮሳ የሚደገም ከሆነ ከዚህ ቀደም ይደረጋል ተብሎ የተዛተበት የቀጣናው ጦርነት በዚህ ጊዜ ከቀጣናው ወሰን ውጭ እንደሚገነፍል ጥበቃ ጦሩ አስገንዝቧል።
በመጨረሻም መግለጫው እኛ የጦርነት ሰዎች ነን በመሆኑም ኃይላችንና አቅማችን የሚታየው በጦር ሜዳ ላይ እንጂ በባዶ መግለጫዎች እና በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ አይደለም ሲል ለአሜሪካ እና ለእስራኤል ጥምረት የመጨረሻ ማስጠንቀቂያውን አስተላልፏል።