Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ስፖርት

ማይክል ካሪክ የጠፋውን የማንችስተር ዩናይትድ የስኬት ቁልፍ ፈልገው ያገኙ ይሆን?

A Administrator May 14, 2026 Updated 3h ago 4 ደቂቃ ንባብ 33 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
ማይክል ካሪክ የጠፋውን የማንችስተር ዩናይትድ የስኬት ቁልፍ ፈልገው ያገኙ ይሆን?

ማንችስተር ዩናይትድ 13 የፕሪሚየር ሊግ እና ሁለት የሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫዎችን ጨምሮ በበርካታ ዋንጫ ያንበሸበሻቸውን ሰር አሌክስ ፈርጉሰንን በክብር ከተሸኘ በኋላ አሰልጣኝ አልወጣልህ ብሎት ቆይቷል፡፡ 

በቀያይ ሰይጣናቱ ቤት 26 ስኬታማ ዓመታትን ያሳለፉት ስኮትላንዳዊው አሌክስ ፈርጉሰን አሰልጣኝነትን በቃኝ ብለው ኦልትራፎርድን በክብር ከተሰናበቱ ወዲህ ክለቡ የነገሰበትን የሊጉን ዋንጫ ሳያገኝ 12 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

ሰር አሌክስ ፈርጉሰን እኤአ በ2012/13 የውድድር ዓመት ነበር የሊጉን ዋንጫ በማንሳት ራሳቸውን ከአሰልጣኝነት ያገለሉት። ማንችስተር ዩናይትድም ከእሳቸው በኋላ ስድስት ቋሚ አሰልጣኞችን ቢያፈራርቅም ነገር ግን ክለቡን ወደኃያልነቱ የሚመልስ ሊገኝ አልቻለም፡፡ 

Advertisement
Your ad could be here — contact us

የዩናይትድን ታላቅነት እንደሚያስቀጥሉ ታምኖባቸው ኦልትራፎርድ የደረሱት የመጀመሪያው ሰው ሌላኛው ስኮትላንዳዊ ዴቪድ ሞይስ ነበሩ፡፡

ሞይስ በወቅቱ የመርሲሳይዱን ክለብ ኤቨርተንን ተሰናብተው የታላቁ አሰልጣኝ ምትክ በመሆን ኦልድትራፎርድን ሲረግጡ የዩናይትድ ደጋፊዎች 'ተመራጩ ሰው' በማለት ነበር የተቀበሏቸው። ሆኖም ግን ከኃላፊነታቸው ሲሰናበቱ ሙሉ የውድድር ዓመቱን እንኳን አልጨረሱም ነበር።

የሞይስን ስንብት ተከትሎ ክለቡ የውድድር አመቱን የመጨረሻ አራት ጨዋታዎች በታሪካዊው ተጨዋች ሪያን ጊግስ ከተመራ በኋላ ሊውስ ቫን ሀልን ሾመ።

photo_2_2026-05-14_10-01-59

ባርሴሎናን ፣ ባየርን ሙኒክን እና አያክስን አምስተርዳምን ከመሳሰሉ ቡድኖች ጋር ዋንጫዎችን ማሳካት የቻሉት ቫን ሀል ዩናይትድን ወደ ውጤማነት እንደሚመልሱት ቢታመንባቸውም ነገር ግን በተቃራኒው ለስንብት ተዳርገዋል።

ሁለት ደካማ የውድድር ዓመት ካሳለፉ በኋላም ቫን ሀል ተሰናብተው ፖርቹጋላዊው እውቅ አሰልጣኝ ጆዜ ሞሪኒሆን ተሾሙ።

ከቸልሲ ጋር የሊጉን ዋንጫ ማሳካታቸው የሚታወቅላቸው እና ራሳቸውን "ልዩ ሰው" በማለት የሚጠሩት ፖርቹጋላዊ አሰልጣኝ ጆዜ ሊጉን ጠንቅቀው ያውቃሉ በሚል ነበር ከበርካቶች ድጋፍ አግኝተው ወደ ካሪንግተን ያመሩት።

በስፔን እና በጣሊያን ጭምር ክለቦችን በመምራት ስኬታማ የአሰልጣኝነት ጊዜያትን ማሳለፋቸው ደግሞ ቀያይ ሰይጣናቱን እንዲረከቡ ተመራጭ አድርጓቸው ነበር።

ሆኖም በኦልድትራፎርድ ነገሮች እንዳሰቡት ያልሆነላቸው ሞሪኒሆ ከሁለት ዓመት ከመንፈቅ ቆይታ በኋላ የቀደሙት አሰልጣኞች እጣ ደርሷቸው ተሰናበቱ።

ጆዜ ሞሪኒሆ ዩናይትድን የዩሮፓ ሊግ፣ የካራባኦ እና የኮሙኒቲ ሺልድ ዋንጫ አሸናፊ ማድረጋቸውና በፕሪሚየር ሊጉ ክለቡ 2ኛ ደረጃን ይዞ እንዲያጠናቅቅ ቢያደርጉም ነገር ግን የቀያይ ሰይጣኖቹ ኃላፊዎች ተጨማሪ እድል አልሰጧቸውም።

ከሞሪንሆ መባረር በኋላ በጊዜያዊነት የተመደቡትና በኋላም በቋሚነት የተሾሙት የክለቡ የቀድሞ ተጫዋች ኦሌጉናር ሶልሻየር ሦስት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ክለቡን መምራት ችለው ነበር።

ሶልሻየር በ2020/21 ማንችስተር ዩናይትድ በሊጉ 2ኛ ሆኖ እንዲያጠናቅቅ ያስቻሉ ሰሆን በዩሮፓ ሊግም ለፍጻሜ ደርሰው ነበር። ነገር ግን ያ ውጤት በኃላፊነታቸው ለመቀጠል ዋስትና አልሆናቸውም።

ክለቡ ሶልሻየርን ካሰናበተ በኋላ ለማይክል ካሪክ ጊዜያዊ ኃላፊነት ሰጥተው የሰር አሌክስ ፈርጉሰን ሁነኛ ምትክ ሲያፈላልጉ ከቆዩ በኋላ ራልፍ ራኚክን እንዲሁ በጊዜያዊነት መሾማቸው አይዘነጋም።

በመቀጠል ኦልድትራፎርድ የደረሱት ሌላኛው ኔዘርላንዳዊ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግ ነበሩ።
ገና ከመምጣታቸው 'የሊቨርፑል እና የማንቼስተር ሲቲ ዘመን በቅርቡ ያከትማል' በሚለው ንግግራቸው ራሳቸውን ያስተዋወቁት ኤሪክ ቴን ሀግ በአሰልጣኝነት ቆይታቸው ተቃራኒ የሆነውን እና በክለቡ ታሪክ መጥፎ የሚባሉ ክብረወሰኖችን በመጻፍ ደካማ ጊዜ አሳልፈዋል።

ኤሪክ ቴን ሀግ በቆይታቸው ምንምኳ አንድ የኤፍ ኤ እና አንድ የካራባኦ ካፕ ዋንጫ ማሳካት ቢችሉም ነገር ግን ክለቡ በሊጉ ባሳየው የሚዋዥቅ አቋም ምክንያት ለስንብት ተዳርገዋል።

ከዚያም ለምክትላቸው ሩድ ቫኒስትሮይ ጊዜያዊ ኃላፊነት የሰጠው ክለቡ ከአራት ጨዋታዎች በኋላ እሱን አሰናብቶ ሩበን አሞሪምን ወደ ኦልድትራፎርድ አመጣ።

በተለይም የጨዋታ ስልታቸውን አልቀይርም በሚለው አቋማቸው "ግትር ናቸው" በሚል የሚተቹት ሩበን አሞሪም ከ14 ወራት በኋላ ራሳቸውም እንደሌሎቹ ከካሪንግተን ተሰናበቱ።

በእሳቸው ምትክ ደግሞ የቀድሞው የክለቡ የመሐል ሜዳ ኮከብ ማይክል ካሪክ ተተክተው ጥሩ የሚባል ጊዜ ማሳለፍ ችለዋል።

እግር ኳስን ለትውልድ ከተማው ዎልሴንድ በመጫዎት "ሀ" ብሎ የጀመረው ማይክል ካሪክ ገና በ15 ዓመቱ ወደ ለንደን ተጉዞ የዌስትሃም ዩናይትድን የታዳጊዎች ቡድንን በመቀላቀል ራሱን ከእግር ኳስ ጋር እያሥተዋወቀ መጣ።

ከሁለት ዓመታት ቆይታ በኋላም ከወጣት ቡድኑ ጋር የእንግሊዝ ወጣቶች ዋንጫን በማሸነፍ ወደ ዋናው ቡድን የማደግ እድል አግኝቷል።

ቀጥሎም በስዊንደን ታውን እና በርሚንግሃም ሲቲ በውሰት በመጫዎት ከእግር ኳስ ጋር በደንብ ከተወዳጀ በኋላ ወደ ዌስትሃም ዋናው ቡድን በመመለስ ለአራት ዓመታት ያህል የተጫወተ ሲሆን እኤአ 2004 ላይ ቶተንሃምን ሆትስፐርን ተቀላቀለ።

ለሁለት አመታት በቶተናም ሆትስፐር ከቆየ በኋላ እኤአ 2006 ላይ በሰር አሌክስ ፈርጉሰን ፍላጎት መሰረት ከሰሜን ለንደኑ ክለብ ወደ ማንቼስተር ዩናይትድ በማቅናት ደማቅ በቀያይ ሰይጣናቱ ቤት ደማቅ 12 ዓመታትን አሳልፏል።

በ12 ዓመታት የማንችስተር ዩናይትድ ቤት ቆይታው 464 ጨዋታዎችን አድርጎ 5 ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮን መሆን የቻለ ሲሆን አንድ የሻምፒየንስ ሊግ እና ሌሎች የአውሮፓ ዋንጫዎችን አሳክቷል።

በተጫዋችነት ዘመኑ በነበረው አቅም በርካቶች የሚያደንቁት እና "በብቃቱ ልክ ያልተዘመረለት ኮከብ" ሲሉ የሚገልፁት የቀድሞው የማንችስተር ዩናይትድ አማካይ ማይክል ካሪክ አሁን ደግሞ ቀያይ ሰይጣናቱን በጊዜያዊ አሰልጣኝነት እየመራ ይገኛል።

ከወራቶች በፊት ብዙ የተባለለትን ግን የተጣለበት ተስፋ ሁሉ የመከነበትን አሰልጣኝ ሩበን አሞሪምን ያሰናበተው ማንችስተር ዩናይትድ በሱ ምትክ የቀድሞ ኮከቡን ማይክል ካሪክን እስከ ውድድር ዓመቱ መጨረሻ እንዲያሰለጥን ሹሞት የነበር ሲሆን አሁን ደግሞ ያስመዘገበውን አስደናቂ ውጤት ተከትሎ ለቋሚነት አጭቶታል።

ዛሬ በተሰማ አዲስ ዜና የማንችስተር ዩናይትድ የበላይ ሀላፊዎች አሰልጣኝ ማይክል ካሪክን በቋሚነት እንዲቀጥል ድጋፋቸውን ሰጥተዋል። 

የክለቡ ዋና ስራ አስፈፃሚ ኦማር ቤራዳ እና የእግርኳስ ዳይሬክተሩ ጄሰን ዊሎክስ ካሪክን በሀላፊነት ለመሾም እየተዘጋጁ መሆኑ ተሰምቷል። 

ሀላፊዎቹ ማይክል ካሪክ ቀጣይ አመት ቡድኑን ለመምራት ትክክለኛው ሰው ነው የሚል እምነት እንዳላቸው ተነግሯል። 

ይህንንም ተከትሎ ሀላፊዎቹ በቀጣይ ቀናት ማይክል ካሪክ እንዲቀጥል የክለቡን ባለቤት ሰር ጂም ራትክሊፍን እንደሚጠይቁ ተገልጿል። 

ይህንን ተከትሎ አሰልጣኝ ማይክል ካሪክ ክለቡን ለመምራት የቋሚነት ቦታውን የሚያገኝበት እድል ከፍተኛ ነው።

በዚህም ባለፉት ዓመታት መፍትሔ ፍለጋ ጊዜያዊዎችን ጨምሮ 10 አሰልጣኞች የቀያዬረው ማንችስተር ዩናይትድ በፈርጉሰን ዘመን የጠፋውን የስኬት ቁልፍ በአሰልጣኝ ማይክል ካሪክ ያገኘው ይሆን?
ወይስ "ጉልቻ ቢቀያዬር..." እንዲሉ  እሳቸውም የሌሎች አሰልጣኞች እጣ ይደርሳቸው ይሆን የሚለውን ጥያቄ ጊዜ መልሱን ይሰጥበታል።

A
ስለ ጸሐፊው

Administrator

12 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።