Home / ዜና / ኢራን የአሜሪካን የየብስ ወረራ ለመመከት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ወታደሮች አሰለፈች

ኢራን የአሜሪካን የየብስ ወረራ ለመመከት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ወታደሮች አሰለፈች

መጋቢት 18/2018 (ገበያ ሚዲያ) የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ላይ ሙሉ በሙሉ የየብስ ወረራ የሚጀምሩ ከሆነ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የኢራን ወታደሮች አጸፋዊ እርምጃ ለመውሰድ በተጠንቀቅ ላይ መሆናቸው ተገልጿል።

በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ወታደራዊ ውጥረት ወደ ከፋ ደረጃ መሸጋገሩን ተከትሎ ኢራን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተዋጊዎችን በተጠንቀቅ ማሰለፏን በቴህራን የሚገኙ ወታደራዊ ምንጮችን ጠቅሶ ዘሰን የዜና አገልግሎት ዘግቧል።

ሀገሪቱ ይህን ግዙፍ ሰራዊት ያሰለፈችው ደግሞ ከአሜሪካ ሊሰነዘርባት ይችላል ላለችው የምድር ወረራ ምላሽ ለመስጠት መሆኑ ተገልጿል።

በሌላ በኩል የኢራኑ ታስኒም የዜና ወኪል አንድን ወታደራዊ ከፍተኛ መኮንን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ዋሽንግተን በየብስ ጦር ጥቃት ለመሰንዘር የምታደርገው ማንኛውም ሙከራ ለኃይሎቿ “ታሪካዊ ሲኦል” የሚሆን ምላሽ ያስከትልባታል ብሏል።

እንደ ወታደራዊ ምንጩ ገለጻ የአሜሪካ የየብስ ጦር ወረራ ሊፈጽም ይችላል የሚለው ስጋት በኢራናውያን ዘንድ ከፍተኛ የሀገር ፍቅር ስሜትን የቀሰቀሰ ሲሆን በዚህም ሳቢያ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የጦር ኃይል አባላትና ታጣቂዎች ጥቃቱን ለመመከት አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቀዋል ነው የተባለው።

ይህ መግለጫ የወጣው ደግሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን እንድትከፍት ካስተላለፉት ጥብቅ ትእዛዝ ጋር ተያይዞ ሲሆን ፕሬዝዳንቱ ኢራን ትእዛዙን የማታከብር ከሆነ በሀገሪቱ የኃይል መሰረተ ልማቶች ላይ ጥቃት እንደሚሰነዘርና የየብስ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።

በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የኢራን የምድር ጦር አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል አሊ ጃሃንሻሂ በበኩላቸው የየብስ ጦርነት ለጠላት እጅግ አደገኛና ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍል እንደሚሆን አጽንኦት ሰጥተዋል።

ጄኔራሉ አክለውም በድንበር አካባቢ ያሉ ማናቸውም የጠላት እንቅስቃሴዎች በቅርብ ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑንና ማንኛውንም አይነት ትንኮሳ ለመቀልበስ ጦሩ በሙሉ ዝግጁነት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *