Home / ዜና / ትራምፕ ኢራንን ወደ “ድንጋይ ዘመን” እንደሚመልሱ በመዛት አስጠነቀቁ

ትራምፕ ኢራንን ወደ “ድንጋይ ዘመን” እንደሚመልሱ በመዛት አስጠነቀቁ

መጋቢት 24/2018 (ገበያ ሚዲያ) የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትላንት ምሽት በዋይት ሀውስ በሰጡት መግለጫ፤ አሜሪካ በኢራን ላይ የነደፈቻቸው ወታደራዊ ግቦች በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቁ አስታውቀዋል።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ኢራን ላይ እጅግ ከባድ ጥቃት እንደሚሰነዘር በግልጽ ዝተዋል።

“አሜሪካ በኢራን ላይ የነደፈቻቸው ወታደራዊ ግቦች በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃሉ” ያሉት ትራምፕ፤ በቀጣዮቹ ሁለት እና ሶስት ሳምንታት ውስጥ የሚፈጸመው ጥቃት ሀገሪቱን ወደ “ድንጋይ ዘመን” የሚመልስ እንደሚሆን ተናግረዋል።

ይህ የፕሬዝዳንቱ ንግግር አሜሪካ እስከ አሁን ከወሰደችው እርምጃ በበለጠ የኢራንን መሠረተ ልማቶች ሙሉ በሙሉ ለማውደም መዘጋጀቷን የሚያመላክት ሆኗል።

ትራምፕ ይህንን የኃይል ዛቻ የሰነዘሩት የኢራን መሪዎች ለአሜሪካ የድርድር ጥያቄ እጃቸውን ካልሰጡ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም እስካሁን ያልተነኩ የኢራን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች እና የነዳጅ መሠረተ ልማቶች በቀጣዩ የጥቃት ዙር ዋና ኢላማ እንደሚሆኑ አስጠንቅቀዋል።

“በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ እጅግ በኃይለኛው እንመታቸዋለን” ሲሉ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ ይህም ጦርነቱን በፍጥነት የማጠናቀቂያ ስልታቸው እንደሆነ ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የትራምፕን ንግግር ተከትሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ ዳግም ያሻቀበ ሲሆን፤ ጦርነቱ ከማለቅ ይልቅ ይበልጥ ወደ ከፋ ደረጃ ሊሸጋገር እንደሚችል ስጋት ፈጥሯል።

የኢራን ወታደራዊ አመራሮች በበኩላቸው ለትራምፕ ዛቻ ምላሽ ሲሰጡ አሜሪካ ጥቃት የምትሰነዝር ከሆነ “የማይገመት እና የከፋ” አጸፋዊ እርምጃ እንደሚጠብቃት አስታውቀዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *