Home / ዜና / የዕለት ዜና / በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ሳቢያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሳምንት እስከ 137 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ሊያጣ እንደሚችል ገለጸ

በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ሳቢያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሳምንት እስከ 137 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ሊያጣ እንደሚችል ገለጸ

ካቲት 26/2018 (ገበያ ሚዲያ) በአሜሪካ፣ እስራኤል እና ኢራን መካከል የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቀጠናው የሚያደርጋቸውን በርካታ በረራዎች ለመሰረዝ መገደዱንና በዚህም ሳቢያ በሳምንት እስከ 137 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ገቢ ሊያጣ እንደሚችል አስታውቋል።

የአየር መንገዱ የንግድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ለማ ያዴቻ ስድስተኛ ቀኑን በያዘው አሜሪካ እና እስራኤል ከኢራን ጋር የሚያደርጉት ጦርነት በአየር መንገዱ ላይ ትልቅ ጉዳት እንደሚያስከትል ተናግረዋል።

ጦርነቱ ከመቀስቀሱ በፊት አየር መንገዱ ወደ ተለያዩ የመካከለኛው ምስራቅ ከተሞች ከፍተኛ የደንበኞች ፍሰት የነበረው ሲሆን፤ አሁን ላይ ግን በቀን በአማካኝ 15 በረራዎች እየተሰረዙ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በሳምንት ከ101 በላይ የመንገደኞች በረራዎች እየተሰረዙ መሆኑን ዋናው ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።

“የጭነት (Cargo) በረራዎችን ጨምሮ በሳምንት በአጠቃላይ 160 በረራዎች ተሰርዘዋል” ያሉት አቶ ለማ፤ በዚህም ምክንያት በሳምንት ይጓጓዙ የነበሩ ከ45 እስከ 50 ሺሕ መንገደኞች ጉዟቸው ተስተጓጉሏል።

አቶ ለማ እንደገለጹት ጦርነቱ በዚህ ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ አየር መንገዱ ከመንገደኞች አገልግሎት 135 ሚሊዮን ዶላር ከጭነት አገልግሎት ደግሞ 2 ሚሊዮን ዶላር በድምሩ እስከ 137 ሚሊዮን ዶላር በሳምንት ሊያጣ ይችላል።

“ይህ ከፍተኛ የገቢ መቀነስ ቢኖርም አየር መንገዱ በከፍተኛ ሁኔታ አይከሰርም” ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ለዚህም በመካከለኛው ምስራቅ መስመር ላይ ይሰሩ የነበሩ አውሮፕላኖችን ለጊዜው ወደ ሌሎች አማራጭ መስመሮች በማሰማራት የገቢ ምንጩን ለማመጣጠን ጥረት እየተደረገ ነው ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

በአሁኑ ወቅት በመካከለኛው ምስራቅ ያለው የሰማይ ላይ በረራ ሁኔታ እርግጠኛ ባልሆነ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ ግጭቱ የሚሰፋ ከሆነ የዓለም አቀፍ የበረራ መስተጓጎሉ ተባብሶ ሊቀጥል እንደሚችል ባለሙያዎች እየገለጹ ይገኛሉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *