በመኮንን አልማው!
የኢትዮጵያ ህዝብ በእግር ኳስ ላይ የቆረጠውን ተሥፋ መልሰው ለመቀጠል ቆርጠው የተነሱት እና በሀገረ ሞሮኮ እየተፋለሙ ያሉት የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ምሽትም ወደ ዓለም አቀፍ መድረክ የሚወስዳቸውን አህጉራዊ ጨዋታ ያደርጋሉ።
ኢትዮጵያ በበርካታ ዘርፎች ከአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ከአለምም ቀዳሚት እንደነበረች አበውም ሆነ የታሪክ መዛግብት ያወሱልናል።
ተነግሮም ተዝቆም የማያልቅ በርካታ ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ በስፖርቱ በኩልም እንዲሁ የሚያኮራ ታሪክ ነበራት።
ነገር ግን ያ ውብ ታሪኳ እንዳይቀጥልም ሆነ እንዳይደገም ተረግማ ይመሥል ከጉያዋ ከራቀ ቆይቷል።
በተለይ ባለፉት አስር አመታት ውስጥ ከሀገራችን ሊግ የዘለለ በአህጉርም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ ይሔ ነው የሚባል አንገትን ቀና ፣ ደረትን ነፋ የሚያሥደርግ አንዳች ጥሩ ነገር ብልጭ ብሎ አልታየም።
አህጉራዊ ጨዋታዎቹን በውሰት እና በኪራይ ሜዳ በስደት ሲጫወት የቆየው ብሔራዊ ቡድኑም ከህዝቡ እና ከደጋፊው እቅርቆ እንዲጫዎት ተፈርዶበት ፣ ዜጋውም አይኖቹን በአውሮፓ ክለቦች ላይ ጥሏል።
ታዲያ ይሔንን ደስ የማይል ታሪክ የሚሽር እና እንደ አንድ ወቅት ዋልያዎቹ ኳስ ወዳዱን ህዝብ የሚያገማሽር ትውልድ እየመጣ ይመሥላል።
ይህ ተስፋ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው ባለፈው ሕዳር 6 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ሲካሄድ በቆየው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ማጣሪያ ውድድር ላይ ነበር።
በአህጉራዊ እና አለም አቀፍ መድረኮች ላይ መሳተፍ ብርቋ የሆነባት ኢትዮጵያ ያኔ በውድ ብላቴና ልጆቿ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ የቻለችበት ቅፅበት በህዝቡ ልብ ውስጥ የሻማ ብርሃን መለኮስ ችሏል።
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ማጣሪያ ጨዋታውን ከኬንያ አቻው ጋር ባደረገው የደረጃ ጨዋታ 3 ለ 0 በማሸነፍ ለአህጉራዊው መድረክ ማለፉን ማረጋገጥ የቻለበት አጋጣሚ ነበር ተስፋ ያሰነቀው።
በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በተካሄደው በዚህ ጨዋታ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ገና ከአሁኑ ተስፋ የተጣለበት ዳዊት ካሳው በ66ኛው ደቂቃ ላይ የኬንያን መረብ አሐዱ ብሎ ባረከው። ቀጠለና አምበሉ ቢነያም አብርሃ በ79ኛው ደቂቃ ቶናውን ደገመ። ሶስተኛዋን ግብ ደግሞ ብሩክ እይላቸው ተቀይሮ በገባበት ቅፅበት በ93ኛው ደቂቃ ላይ በቴስታ አበረከላቸው።
ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ከሰሞኑኑ በሞሮኮ አስተናጋጅነት እየተካሔደ በሚገኘው እና በ16ኛው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ በማለፍ አሁን እየተሳተፈች ያለች ሀገር ሆናለች።
በወቅቱ አንደኛ እና ሁለተኛ በመሆን ኢትዮጵያን ቀድመው ማለፍ የቻሉት ደግሞ ዮጋንዳ እና ታንዛኒያ ነበሩ።
በዚህ ኢትዮጵያ ባስተናገደችው የካፍ ውድድር ሶስተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችው ኢትዮጵያ ለመጨረሻ ጊዜ ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የተሳተፈችው እ.አ.አ በ2003 ስዊዚላንድ ባዘጋጀችው ውድድር ላይ ነበር።
ከዛም ከ22 ዓመታት ጥበቃ በኋላ እንደገና በውድድሩ ላይ ኬንያን አሸንፋ በማለፍ ዛሬ እየተሳተፈች ትገኛለች።
በዚያ ጨዋታ ትልቅ የታሪክ ግጥምጥሞሽም ተከስቶ ነበር።
የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን የዛሬ 22 አመት ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈው ኬንያን በማሸነፍ ነበር። ታዲያ በዘንድሮው ውድድርም ታሪክ ራሡን ደግሟል።
በዚያ ውድድር ኢትዮጵያ በከዋከብት ልጆቿ አማካኝነት እጅግ በጣም ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ማስመልከት ችላለች።
ብላቴናዎች ምናልባትም በቀጣይ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ታሪክ በደማቁ የሚፅፉበትን የታሪክ አሻራ እንደሚያሳርፉ ከወዲሁ እምነት የተጣለባቸው ያኔ ህዳር ላይ ነበር።
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን አጥቂ የሆነው ዳዊት ካሳው እና የቡድኑ አምበል የአማካኝ ስፍራ ተጫዋቹ ቢኒያም አብርሃ በአውሮፓ ክለቦች ዘንድ እንደምናያቸው የሚጠበቁ ተስፈኛ ኮከቦች መሆናቸውን በሚገባ አሳይተዋል።
ዳዊት ካሳው በውድድሩ ላይ 8 ግቦችን በማስቆጠር ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ማጠናቀቁም ይታወሳል።
በእነዚህ ወሳኝ ብላቴናዎች የተሰራው ቡድኑ "ቀይ ቀበሮዎቹ" በሚል ስያሜ እየተጠራ ያልተደናቀፈ ጉዞውን ቀጥሏል።
በህዳር ወር ያስመዘገበውን ውጤት ተከትሎ ለአፍሪካ ዋንጫ መሳተፍ የቻለው ቡድኑ ከሳምንት በፊት ወደሞሮኮ አሥርቶ ጨዋታውን እያደረገ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ስትሳተፍ ይሕ የሞሮኮው ዝግጅት ለአራተኛ ጊዜዋ ሲሆን በመድረኩም የምድብ ጨዋታዎችን በተመጣጣኝ ውጤት መፈፀም ችላለች።
በመጀመሪያው የምድብ ጨዋታ ከግብፅ ጋር አቻ የወጡት ቀይ ቀበሮዎቹ በአዘጋጇ ሞሮኳ 2-1 ተሸንፈው እና ታንዛኒያን 1-0 ድል አድርገው በ4 ነጥብ ከምድብ ሶስተኛ ደረጃን መያዝ ችለዋል።
በዚህም ቡድኑ ምርጥ ሶስተኛ በመባልና ከሌላ ተመሳሳይ እድል ካገኘ ብሔራዊ ቡድን ጋር ጥሎ ማለፍ በመጫዎት ለኳታሪ የአለም ዋንጫ የማለፍ ጥሩ አጋጣሚ አግኝቷል።
ቀይ ቀበሮዎቹ ለዚህ እድል ከሞዛምቢክ ጋር የተመደቡ ሲሆን ፣ የጥሎ ማለፍ ጨዋታውም ዛሬ ቅዳሜ ምሽት 1:00 ሰዓት ላይ ይደረጋል።
ቀይ ቀበሮዎቹ ዛሬ ሞዛምቢክን የሚያሸንፉ ከሆነ በአለም ዋንጫው በቀጥታ የሚያልፉ ይሆናል።
ታዲያ የኳታር አለም ዋንጫ ምድብ ድልድልም ከትላንት በስቲያ የወጣ ሲሆን የኢትዮጵያ እና የሞዛምቢክ አሸናፊ
በአለም ዋንጫው ምድብ 2 ላይ እንደሚገባ እና ከደቡብ ኮርያ ፣ ኢኳዶር እና ካሌዶንያ ጋር እንደሚገጥም ይፋ ሁኗል።
ከ17ዓመት በታች አለም ዋንጫ ውድድርም በሚቀጥለው አመት ህዳር ወር ውስጥ በኳታር አዘጋጅነት ይደረጋል።
ታዲያ ኢትዮጵያ ታይታ በማይታወቅበት በዚህ መድረክ መገኘት ትችል ዬሆን?
ለዋልያዎቹ ያልተቻለውን ይህንን የአለም መድረክ ቀይ ቀበሮዎቹ ይሳካላቸው ይሆን?
የእግር ኳስ ወዳዱ የኢትዮጵያ ህዝብስ የራሰን ተወካዮች ፣ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ለባሽ ብላቴናዎቹን በአለም መድረክ ላይ ለመመልከት ይታደል ይሆን?
ተስፈኞቹ ኢትዮጵያ የጠፋችበት መድረክ ላይ ደምቀው በመታየት የሀገሪቱ የጨለመ እግር ኳስ ላይ ብርሃን ይፈነጥቁ ይሆን?
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ31 ዓመታት ጥበቃ በኃላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የተመለሰበት ዕለት ጥቅምት 4 ቀን 2005 ዓመተ ምህረትን ያስታውሱን ይሆን?
አሰልጣኝ ቤንጃሚን ዚመር እንደ ክብር ለኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው አይረሴ ታሪክ ሰርተው በአሁጉራዊ እና በአለም አቀፍ መድረክ ላይ የጠፋችውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፀሃይ ያበሯት ይሆን?
መልሱን የምሽቱ ጨዋታ ውጤት ሹክ አስኪለን በቸር ያቆየን!