ኢራን 1,200 የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ዜጎች በሳምንት ውስጥ ከአገር እንዲወጡ አዘዘች
መጋቢት 21/2018 (ገበያ ሚዲያ) የኢራን የፍትህ አካል በአገሪቱ የሚኖሩ 1,200 የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች (UAE) ዜጎች የመኖሪያ ፈቃዳቸው መሰረዙንና በሰባት ቀናት ውስጥ አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ማዘዙን በዛሬው እለት አስታውቋል።
ይህ ውሳኔ የተላለፈው በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ፍጥጫ እጅግ በከረረበት ወቅት ነው።
የኢራን የፍትህ አካል ባወጣው ይፋዊ መግለጫ እነዚህ ዜጎች በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ከአገር መውጣት እንዳለባቸው ያሳሰበ ሲሆን እርምጃው የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ቀደም ሲል በኢራን ዜጎች ላይ ለወሰደችው ተመሳሳይ የቪዛ ስረዛ የተሰጠ “አጸፋዊ ምላሽ” መሆኑን አመልክቷል።
ይህ ዲፕሎማሲያዊ ቀውስ የተቀሰቀሰው ባለፈው የካቲት ወር መገባደጃ ላይ አሜሪካና እስራኤል በኢራን ላይ የጋራ ወታደራዊ ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ ነው።
ኢራን ለጥቃቱ ምላሽ ለመስጠት በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ውስጥ የሚገኙ ኢላማዎችን ጨምሮ በተለያዩ የቀጠናው ስፍራዎች ላይ መጠነ ሰፊ የሚሳኤልና የድሮን ጥቃቶችን ሰንዝራለች።
ባለፉት ጥቂት ቀናት የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በአገሯ የሚኖሩ ኢራናውያንን ቪዛ በመሰረዝ ከአገር እንዲወጡ ማድረጓና በርካታ ኢራናውያን በየኤርፖርቱ እንዲንገላቱ ማድረጓ ይታወሳል።
የዛሬው የቴህራን ውሳኔ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ወደ ከፋ ደረጃ የሚያሸጋግረው ሲሆን በቀጠናው ላይ ያለውን የጸጥታ ስጋትም ከፍ አድርጎታል።
እስካሁን ድረስ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች መንግስት ለዚህ የኢራን ውሳኔ የሰጠው ይፋዊ ምላሽ የለም።






