Home / ዜና / የዕለት ዜና / ኢራን ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጋር ምንም ዓይነት የተኩስ አቁም ስምምነት እንደማትፈልግ አስታወቀች

ኢራን ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጋር ምንም ዓይነት የተኩስ አቁም ስምምነት እንደማትፈልግ አስታወቀች

የአሜሪካ የጦር መርከብ “ዩኤስኤስ አብርሃም ሊንከን” የድሮን ጥቃት እንደደረሰበት ተገልጿል

የካቲት 27/2018 (ገበያ ሚዲያ) የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰይድ አባስ አራግቺ ሀገራቸው ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጋር ምንም ዓይነት የተኩስ አቁም ስምምነት እንደማትፈልግና ከዋሽንግተን ጋር ለመደራደርም ምክንያት እንደሌላት ገለጹ።

ሚኒስትሩ ከኤንቢሲ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ቀደም ሲል በነበሩ የድርድር ሂደቶች አሜሪካ በንግግር መካከል ጥቃት መፈጸሟን በማስታወስ፣ አሁን ላይ ድርድር እንደማያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።

“እኛ የተኩስ አቁም ጥያቄ አላቀረብንም፤ ቀደም ሲል ሁለት ጊዜ ከእነሱ ጋር ተደራድረን በንግግር መካከል ጥቃት ስለፈጸሙብን አሁን ከአሜሪካ ጋር የምንደራደርበት ምንም ምክንያት አይታየንም” ብለዋል።

“አሜሪካ በኢራን ላይ የምድር ወረራ ልታካሂድ ትችላለች” ስለሚባለው ግምት ሚኒስትሩ ሲመልሱ፤ የሀገሪቱ የጦር ኃይሎች ለማንኛውም ዓይነት ወረራ ሙሉ በሙሉ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

አክለውም “እየጠበቅናቸው ነው፤ እኛ እነሱን ለመጋፈጥ ሙሉ አቅም አለን፣ ይህም ለእነሱ ትልቅ ጥፋት ይሆናል” ሲሉ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል፣ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ (IRGC) የባህር ኃይል ከኢራን የባህር ክልል 340 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በኦማን ባህረ ሰላጤ ላይ የሚገኘውንና፤ “ዩኤስኤስ አብርሃም ሊንከን” የተባለውን የአሜሪካ የአውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ በድሮን መምታቱን አስታውቋል።

እንደ ኢራን መንግሥታዊ ሚዲያ አይአርአይቢ ዘገባ ከሆነ፤ መርከቧ ጥቃት ከደረሰባት በኋላ ከአጃቢዎቿ ጋር በመሆን ቀጠናውን ለቃ ከአንድ ሺሕ ኪሎ ሜትር በላይ ርቃ ለመሸሽ ተገዳለች።

ይህ ውጥረት ከፍ ሊል የቻለው አሜሪካ እና እስራኤል በጋራ በቴህራን እና በሌሎች የኢራን ከተሞች ላይ ቅዳሜ ጠዋት የፈጸሙትን የአየር ጥቃት ተከትሎ ሲሆን፤ በጥቃቱም የኢራን የበላይ መሪ አሊ ኻሜኒ፣ የቤተሰባቸው አባላት፣ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች እና ሲቪሎች መገደላቸው ይታወሳል።

ኢራንም ለዚህ ጥቃት ምላሽ ለመስጠት በእስራኤል እና በቀጠናው ባሉ የአሜሪካ ይዞታዎች ላይ ሰፊ የሚሳኤል እና የድሮን ጥቃቶችን እየሰነዘረች ትገኛለች።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *