Home / ፖለቲካ / ሻዕቢያን አሳምረን ስለምናውቀው ዳግም ሕዝባችንን እንዲበድል እድል አንሰጥም” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ሻዕቢያን አሳምረን ስለምናውቀው ዳግም ሕዝባችንን እንዲበድል እድል አንሰጥም” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

የካቲት 25/2018 (ገበያ ሚዲያ) የኤርትራን መንግሥት ሻዕቢያን አሳምረን ስለምናውቀው ዳግም ህዝባችንን እንዲበድል እድል አንሰጥም፤ ምናልባት ከሞከረ ደግሞ የመጨረሻ ሙከራው ነው የሚሆነው ብዬ ነው እኔ የማምነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ጋር በትግርኛ ቋንቋ ባደረጉት ቆይታ፤ የሰሜን እዝ ጥቃት ከደረሰበት በኋላ የኤርትራ ሕዝብና ሠራዊት ላደረጉት ድጋፍ እውቅና የሰጡ ቢሆንም፣ የኤርትራ ጦር በኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት ውስጥ በመግባት በንጹሐን ላይ የፈጸመውን ግፍ አውግዘዋል።

በዚህም “የኤርትራ ጦር ትግራይ ውስጥ ገብቶ ከባድ ወንጀል በመፈፀም ንጹሐንን ገድሏል፣ ተቋማትን ዘርፏል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በተለይም በአክሱም ከተማ በሁለት ቀናት ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች መጨፍጨፋቸውን አንስተዋል።

በተጨማሪም በዓድዋ፣ ዓዲግራት እና ሽሬ ቤቶች መፍረሳቸውንና የኢንዱስትሪ ማሽነሪዎች መዘረፋቸውን ገልጸዋል።

መንግሥት በወቅቱ ከህወሓት ጋር ጦርነት ላይ በመሆኑ የውጭ ኃይልን ለመከላከል የሚያስችል አቅም እንዳልነበረው ጠቁመው፤ ሠራዊቱ ወደ መቐለ እንዳይገባ ግን ታክቲካዊ በሆነ መንገድ ተገትቶ እንደነበር አስረድተዋል።

“አሁንም ቢሆን አቅም ካገኘ ሀገርን ከመበጥበጥ ወደ ኋላ አይልም” ያሉ ዶ/ር ዐቢይ፤ ይሁን እንጂ አሳምረን ስለምናውቀው ዳግም ሕዝባችንን እንዲበድል እድል አንሰጥም ምናልባት ከሞከረ ደግሞ የመጨረሻ ሙከራው ነው የሚሆነው ብዬ ነው እኔ የማምነው በማለት ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በቃለ ምልልላቸው ከነሷቸው ጉዳዮች መካካል የሻዕቢያ ሥርዓት በልማት የማያምን፣ በሥልጣን ሽግግር የማያምንና ልጆቹን፣ የልጅ ልጆቹን ሳይቀር የማያምን ስረዓት ተከታይ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

“እንደሚታወቀው የኤርትራ ሕዝብ የሥራ ፍቅር ያለውና ሥራ ፈጣሪ ቢሆንም ግን የሚሆነውን መንግሥት ማግኘት አልቻለም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሻዕቢያ ሥልጣን ሲይዝ ከ300 በላይ ፋብሪካዎች በኤርትራ የነበሩ ሲሆን ዛሬ ግን ሁሉም በሚባል ደረጃ የሉም ብለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *