የካቲት 25/2018 (ገበያ ሚዲያ) የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በመካከለኛው ምስራቅ በኢራን እና በአሜሪካ-እስራኤል ጥምረት መካከል እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ተከትሎ፤ የዓለም የነዳጅ አቅርቦት እንዳይስተጓጎል አዲስ መመሪያ አስተላልፈዋል።
ፕሬዝዳንቱ በመመሪያቸው የአሜሪካ የባህር ሃይል አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ፤ በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ በሚያልፉ የነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ ወታደራዊ አጃቢነት እና ጥበቃ እንዲያደርግ አዘዋል።
ይህ ውሳኔ የተላለፈው የኢራን አብዮታዊ ዘብ (IRGC) የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ “ተዘግቷል” ሲል ካወጀና የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት እንደሚሰነዝር ካስጠነቀቀ በኋላ ነው።
በአሁኑ ወቅት ከ150 በላይ መርከቦች በመንገዱ ላይ ተዘግተው የሚገኙ ሲሆን፤ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ቢያንስ አምስት መርከቦች ጥቃት ደርሶባቸዋል ተብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም ፕሬዝዳንት ትራምፕ በ”ትሩዝ ሶሻል” ገጻቸው ላይ እንደገለጹት፤ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን ለንግድ መርከቦች “በጣም በተመጣጣኝ ዋጋ” የፖለቲካ ስጋት የመድን ዋስትና እንዲሰጥም ትዕዛዝ ሰጥተዋል።
በዚህም የግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በከፍተኛ ስጋት ምክንያት ዋስትና ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው፤ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት የነዳጅ ዋጋ ንረትን ለመቀነስ ወሳኝ እንደሆነ ታምኖበታል።
“ምንም ይሁን ምን አሜሪካ የኢነርጂ ፍሰት ወደ ዓለም እንዲቀጥል ታደርጋለች” ያሉት ትራምፕ፤ የአሜሪካ ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥንካሬ በዓለም ላይ ተወዳዳሪ የሌለው መሆኑን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ በኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉ ባለሙያዎች የባህር ሃይል አጃቢነት በቶሎ ተግባራዊ ለማድረግ ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል ስጋታቸውን እየገለጹ ነው ተብሏል።
ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ የነዳጅ ዋጋ ከ12 በመቶ በላይ ሲጨምር፤ የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በአንድ በርሜል ከ81 ዶላር በላይ መድረሱን የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በተጨማሪም ይህ ሁኔታ በዓለም አቀፍ የገበያ መረጋጋት ላይ ከፍተኛ ስጋት የፈጠረ ሲሆን፤ የአሜሪካ መንግሥት አዳዲስ እርምጃዎች ገበያውን ያረጋጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።








