የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት በይፋዊ መግለጫው ባስታወቀው መሰረት በግንቦት ወር 2018 ዓ.ም የተመዘገበው አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 13.4 በመቶ ሆኗል።
ይህ አኃዝ ካለፈው ዓመት ግንቦት ወር ጋር ሲነጻጸር መጠነኛ ቅናሽ ያሳየ ቢሆንም የምግብ ነክ ምርቶች ላይ የታየው የ14.6 በመቶ የዋጋ ጭማሪ በዜጎች የመግዛት አቅም ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ ይገኛል።
የዋጋ ንረቱ በዋናነት የተከሰተው በአትክልት፣ በስጋ፣ በወተት ተዋፅኦዎች፣ በእንቁላል፣ በፍራፍሬ፣ በዘይትና ስኳር የመሳሰሉ መሰረታዊ የምግብ ሸቀጦች ዋጋ በተከታታይ በመጨመሩ ነው።
የኢኮኖሚው አዝማሚያ እንደሚያሳየው በሚያዝያ ወር 11.7 በመቶ የነበረው አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ወደ 13.4 በመቶ ማሻቀቡ፤ የኑሮ ውድነቱ ለዜጎች በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች እጅግ ፈታኝ መሆኑን ያሳያል።
ምግብ ነክ ባልሆኑ ምርቶችና አገልግሎቶች ዘርፍ ደግሞ የዋጋ ግሽበቱ 11.1 በመቶ ተመዝግቧል።
በዚህ ዘርፍ ስር የሚመደቡ አገልግሎቶችና ሸቀጦች በየዘርፉ ሲከፋፈሉ ትራንስፖርት 12.1 በመቶ፣ አልኮል መጠጦችና ትምባሆ 14.6 በመቶ ጭማሪ አሳይተዋል።
በተመሳሳይ መልኩ የቤት፣ ውሃ፣ ኤሌክትሪክና ነዳጅ አገልግሎቶች 9.1 በመቶ እንዲሁም ምግብ ቤቶችና ሆቴሎች 10.5 በመቶ የዋጋ ጭማሪ አስመዝግበዋል።
በተጨማሪም ሌሎች ዕቃዎችና አገልግሎቶች በዚሁ ወር 17.9 በመቶ የዋጋ ጭማሪ ማሳየታቸው ተገልጿል።
የአገልግሎቱ መረጃ እንደሚያመላክተው ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ የዋጋ ግሽበቱ ተለዋዋጭነት አሳይቷል።
ምንም እንኳን አጠቃላይ የግሽበት መጠኑ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንጻር ቅናሽ ቢኖረውም የምግብ ነክ ምርቶች ዋጋ መናር የዕለት ተዕለት የፍጆታ ዕቃዎችን ዋጋ ወደ ላይ በመግፋት የኑሮ ውድነቱን አባብሶታል።
ይህ በዕለት ተዕለት ሕይወት ብዙዎችን እያሳሰበ የመጣው ነገር ግን ለረጅም ዓመታት መፍትሔ ያልተገኘለት የዋጋ ንረት ጉዳይ በተለይም ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ እና ቋሚ ገቢ የማያገኙትን የኅብረተሰብ ክፍሎችበከፍተኛ ደረጃ አማርሯል።
ባለሙያዎች እንደሚጠቁሙት የገበያ መረጋጋትን ለመፍጠር እና የምግብ ዋጋን ለመቆጣጠር የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በቁርጠኝነት መስራት ይጠበቅባቸዋል።
በሌላ በኩል መንግስት የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር በዋናነት የገንዘብ ዝውውርን በመገደብና የብድር አቅርቦትን በማጥበቅ፣ የገንዘብ ህትመትን በመቆጣጠር እንዲሁም የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የአቅርቦት እጥረትን ለመቅረፍ ጥረት እያደረግኩ ነው ሲል ይሰማል።
በተጨማሪም የምርት ግብይት ሰንሰለትን በማሳጠር በደላሎች አማካኝነት የሚፈጠረውን ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ለመግታትና ህገ-ወጥ ክምችትን ለመቆጣጠር ጥብቅ ክትትልና የገበያ መረጋጋት ስራዎችን እየሰራ መሆኑን በመግለጫዎቹ ያሳውቃል።
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት በየወሩ የሚያወጣው ይህ መረጃ በመንግሥት ዘንድ የኑሮ ውድነትን ለማርገብና ኢኮኖሚያዊ ውሳኔዎችን ለመወሰን እንደ ወሳኝ ግብዓት የሚያገለግል ይሆናል።