ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ከተማ እና በአካባቢው የሽንኩርት ዋጋ ካሳየው ያልተጠበቀ ከፍተኛ ጭማሪ ጋር ተያይዞ በገበያው ላይ አለመረጋጋት መፈጠሩ ይታወቃል።
በአሁኑ ወቅት አንድ ኪሎ ሽንኩርት በችርቻሮ መደበኛ ገበያ ከ130 እስከ 170 ብር እየተሸጠ የሚገኝ ሲሆን ከከተማ ውጪ ባሉ ቦታዎች ደግሞ ዋጋው እስከ 200 ብር እየደረሰ መሆኑ ተሰምቷል።
ይህ ዋጋ በተለይም ከወራት በፊት ከ60 እስከ 70 ብር ይሸጥ ከነበረው የገበያ ዋጋ ጋር ሲነጻጸር ከሁለት እጥፍ በላይ ጭማሪ ያሳየ መሆኑ በበርካቶች ዘንድ ጥያቄን ፈጥሯል።
የዋጋ ጭማሪው በዋናነት የመነጨው ከምርት እጥረት እንደሆነ የሽንኩርት አስመጪ ነጋዴዎች የገለጹ ሲሆን የመካከለኛው ምስራቅ ግጭትን ተከትሎ የተከሰተው የነዳጅ አቅርቦት እጥረት በአርሶ አደሮች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ማሳደሩም ሌላኛው የሚጠቅሱት ምክንያት ነው።
በተለይም መስኖን ተጠቅመው ሽንኩርት የሚያመርቱ ገበሬዎች ለፓምፕ እና ለትራንስፖርት የሚሆን ነዳጅ አለማግኘታቸው ምርታቸው እንዲቀንስ እና እንዲደርቅ አድርጓል።
ባለፈው አመት የሽንኩርት ዋጋ በጣም ርካሽ ስለነበረ አርሶ አደሮች የገበያ መረጃን መሰረት በማድረግ ዘንድሮ ሽንኩርት ከመትከል ይልቅ ወደ ስንዴ ቲማቲም እና ሌሎች ሰብሎች ለመቀየር መገደዳቸው ለአቅርቦት ማነስ ምክንያት ሆኖ በአስመጭዎች ተጠቅሷል።
በተጨማሪም ወቅቱ አትክልት በበሽታ የሚጠቁበት መሆኑን እንዲሁም የፋሲካ በአልን ተከትሎ ጾም በመፈታቱ የሽንኩርት ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ለዋጋ ንረቱ አስተዋጽኦ ማድረጉን ነጋዴዎቹ ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በበኩሉ በቂ ምርት ወደ ከተማዋ እየገባ እንደሆነ እና ችግሩ ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረት መሆኑን በመግለጽየነጋዴዎችን ሃሳብ ውድቅ አድርጎታል።
በዚህም ዋጋው በገበያ ውስጥ እየተጋነነ ያለው አላግባብ ዋጋ በሚጨምሩ እና የትራንስፖርት ወጪን ሰበብ በሚያደርጉ ነጋዴዎች የኢኮኖሚ አሻጥር የተከሰተ ነው ተብሏል።
ቢሮው ላለፉት ሳምንታት ባደረገው ኦፕሬሽን ብቻ ከ34 በላይ ምርት የጫኑ መኪናዎችን በመያዝ ሽንኩርቱን በሕገ-ወጥ መንገድ የደበቁ ነጋዴዎችን ለይቶ እርምጃ መውሰዱም ተጠቁሟል።
ነጻ ገበያ ላይ በ170 ብር የሚሸጠው ሽንኩርት በመንግስት በተመረጡ የገበያ ማዕከላት ከ85 እስከ 100 ብር በሚደርስ ዋጋ እየቀረበ በመሆኑ ህብረተሰቡ አማራጭ ቦታዎችን እንምዲጠቀምም ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።
በሌላ በኩል ቢሮው የቁጥጥር ስርአቱን በማጠናከር እና ህገ-ወጥ የዋጋ ጭማሪን በመቆጣጠር በቅርብ ጊዜ ውስጥ የሽንኩርት ዋጋ ከነበረበት ደረጃ ዝቅ እንደሚል ተስፋ ሰጥቷል።
በአጠቃላይ የሽንኩርት ዋጋ መናር በአንድ በኩል የአቅርቦት ሰንሰለት ችግር፤ በሌላ በኩል ደግሞ የግብይት ቁጥጥር እና የነጋዴዎች ታማኝነት ጥያቄዎች አብረው የተነሱበ ሆኖ ቀጥሏል።