የኪራይ ውል ማለቁን እንደ ሰበብ በመጠቀም አከራዮች ተከራዮችን ማስለቀቅም ሆነ፤ ካስለቀቁ በኋላ የቀድሞውን ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምረው ለሌላ ሰው ማከራየት በሕግ የተከለከለ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ አስታወቋል።
የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ቅድስት ወልደጊዮርጊስ አጽንኦት ሰጥተው እንደተናገሩት “ተከራይን አስወጥቼ ሌላ ሰው አስገባለሁ ብሎ ማሰብ ይቻል ይሆናል፤ ነገር ግን ዋጋ ጨምሮ ማከራየት በአዲሱ አሰራር ፈጽሞ አይፈቀድም” ብለዋል።
አያይዘውም ይህ ተግባር በሕግ እንደሚያስጠይቅና በጥቆማ በሚደርስበት ወቅትም አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድ ኃላፊዋ አስገንዝበዋል።
በከተማዋ በተተገበረው የዲጂታል ምዝገባ ሂደት እስካሁን ወደ አምስት መቶ ሺህ የሚጠጉ የኪራይ ቤቶች ወደ ሲስተሙ መግባታቸውን የገለጹት ወይዘሮ ቅድስት ይህ አሰራር አከራዮች መረጃ በመደበቅ በዘፈቀደ ዋጋ እንዲጨምሩ የሚያደርጉትን ኢ-ፍትሃዊ ድርጊት ሙሉ በሙሉ ማስቀረቱን አስታውቀዋል።
የቤቶቹ ዝርዝር መረጃ በየትኛው ክፍለ ከተማ ወረዳና ብሎክ እንደሚገኝ በሲስተሙ ውስጥ በግልጽ በመታወቁ አከራዮች የቤት ኪራይ ዋጋን በራሳቸው ፍላጎት መጨመር እንደማይችሉ አረጋግጠዋል።
ማንኛውም የዋጋ ጭማሪ በየዓመቱ ሰኔ 30 ቀን በመንግሥት በሚወጣው ይፋዊ የገበያ ጥናት ውጤትና መመሪያ መሰረት ብቻ የሚወሰን መሆኑን ኃላፊዋ ጠቅሰዋል።
በምሳሌነትም የአንድ ቤት ኪራይ 1 ሺህ ብር ቢሆንና መንግሥት በሰኔ ወር በሚያወጣው የዋጋ ጥናት መሠረት የፈቀደው ጭማሪ በፐርሰንት የተወሰነ ከሆነ አከራዩ ማሳደግ የሚችለው በዚያው ሕጋዊ ስሌት ብቻ ሲሆን ከዚህ ውጭ በግል ስምምነት የሚደረግ ማንኛውም የተጋነነ ጭማሪ ሕገ-ወጥ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም ሲሉ አብራርተዋል።
የአከራይና ተከራይ ውል ምዝገባ ከተጀመረ ሁለት ዓመት መሙላቱን የጠቀሱት ወይዘሮ ቅድስት አሁን ላይ የውል ማደስ ሥራውን በአካል ሳይንገላቱ በኢንተርኔት ለማከናወን የሚያስችል ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት ቴክኖሎጂው ቤቶችን ወደ ቋት ያስገባ በመሆኑ አከራዮች ውል አያድስም በሚል ተከራይን ለማስወጣት የሚሄዱበትን አሰራር አዳጋች አድርጎታል።
በሌላ በኩል ቢሮው ተከራዮች መብታቸውን በደንብ እንዲያውቁና እንዲጠቀሙበት እንደሚያሳስብ እና አከራዮች “ዋጋ ጨምሩ” ስላሉ ብቻ ተከራዮች ያለ ምንም ሕጋዊ መነሻ ክፍያ መጨመር እንደሌለባቸው የተናገሩት ኃላፊዋ አብዛኞቹ ውሎች ጊዜያቸው የሚያበቃው ከሰኔ 30 በኋላ በመሆኑ በውል ስምምነት ውስጥ እያሉ ዋጋ መጨመር ፈጽሞ እንደማይፈቀድ አስረድተዋል።
ችግር የሚያጋጥማቸው ተከራዮች በየደረጃው በሚገኙ የወረዳና የክፍለ ከተማ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴዎች እንዲሁም በቢሮው በአካል በመቅረብ ቅሬታቸውን ማቅረብ ይችላሉ ተብሏል።
በመጨረሻም መንግሥት ተከራዮች ቢያንስ ለሁለት ዓመት በአንድ ቦታ በሰላም እንዲቀመጡና ከአከራዮች የሚደርስባቸውን ኢ-ፍትሃዊ ጫና ለመቅረፍ የቴክኖሎጂ ማሻሻያውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልበት የተገለጸ ሲሆን በተለይም በሕገ-ወጥ መንገድ ተከራይን ለማስለቀቅና ዋጋ ለመጨመር የሚሞክሩ አከራዮች ላይ ጥቆማ ሲቀርብ በየአካባቢው ባለው መዋቅር በኩል ፈጣን እርምጃ እንደሚወሰድ ተጠቁሟል።