Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ዜና

ከሰኔ ወር መጨረሻ ጀምሮ ታክሲዎች ላይ አዲስ አሰራር ይጀመራል ተባለ!

SM Samuel Mulgeta Jun 10, 2026 Updated 3h ago 2 ደቂቃ ንባብ 112 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
ከሰኔ ወር መጨረሻ ጀምሮ ታክሲዎች ላይ አዲስ አሰራር ይጀመራል ተባለ!

እንደ ትራንስፖርት ቢሮ መረጃ ባለፈው ግንቦት ወር ብቻ ከታሪፍ በላይ በማስከፈልና የታሪፍ ዝርዝር ባለመስቀላቸው ከ3 ሺህ 300 በላይ አሽከርካሪዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዷል።

ከአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሶስት ጊዜ በላይ ጥቆማ የሚቀርብባቸው አሽከርካሪዎች አገልግሎት እንዳይሰጡ ሊደረግ ነው።



በመዲናዋ ከታሪፍ በላይ የሚያስከፍሉ እና ከተሰጣቸው ስምሪት ውጪ የሚያሽከረክሩ የሕዝብ ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር ተጠናክሮ ሊቀጥል መሆኑን ያስታወቀው ቢሮው ከሦስት ጊዜ በላይ ጥቆማ የሚቀርብባቸው ታክሲዎች ከአገልግሎት እንደሚታገዱ ገልጿል።



ቁጥጥሩን ይበልጥ ለማሳለጥና ቀደም ሲል በኪሎ ሜትር ይገለጽ በነበረው ታሪፍ ሳቢያ በትራፊክ ፖሊሶች፣ በተቆጣጣሪዎችና በተሳፋሪዎች መካከል የሚፈጠረውን መወዛገብ ለመፍታት በመጪው ሰኔ ወር በመነሻና መዳረሻ ላይ ያለውን የጉዞ ታሪፍ በግልጽ የሚያሳይ ዝርዝር በየተሽከርካሪዎቹ ላይ እንደሚለጠፍ ተገልጿል።

Advertisement
Your ad could be here — contact us



ይህ እርምጃ የተወሰደው በዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ መዋዠቅ ሳቢያ የተደረገውን ይፋዊ የዋጋ ማሻሻያ ተገን በማድረግ በርካታ አሽከርካሪዎች ከተቀመጠው ታሪፍ ውጪ እያስከፈሉ መሆኑ በጥናት መረጋገጡን ተከትሎ ነው።


እንደ ትራንስፖርት ቢሮ መረጃ ባለፈው ግንቦት ወር ብቻ ከታሪፍ በላይ በማስከፈልና የታሪፍ ዝርዝር ባለመስቀላቸው 3 ሺህ 300 በላይ አሽከርካሪዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዷል።


ከዚህ በተጨማሪም በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው 9417 አጭር የነጻ ስልክ መስመር በድጋሚ ስራ መጀመሩን ተከትሎ ባለፈው ወር ብቻ 400 የሚጠጉ ጥቆማዎች የደረሱ ሲሆን 300ዎቹ ላይ እርምጃ ተወስዷል።



በመካከለኛው ምስራቅ ከተቀሰቀሰው ጦርነትና የነዳጅ አቅርቦት መስተጓጎል ጋር ተያይዞ መንግስት ከመጋቢት 7 ቀን 2018 . ጀምሮ የትራንስፖርት ታሪፍ ማሻሻያ ማድረጉ ይታወሳል።



ይሁን እንጂ የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከሚያዚያ 23 ቀን 2018 . ጀምሮ ለሁለተኛ ጊዜ ያደረገውን የነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ጭማሪ በመጥቀስ በርካታ አሽከርካሪዎችና ረዳቶች ያለ ቢሮው ዕውቅና በዘፈቀደ ዋጋ በመጨመር ከተሳፋሪዎች ጋር ወደ ጸብና እንግልት ሲያመሩ በተለያዩ የመዲናዋ አካባቢዎች ይስተዋላል።



ይህንንም ተከትሎ ቢሮው ቀደም ሲል የተደረገው የታሪፍ ማሻሻያ ወደፊት ሊደረግ የሚችለውን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ጭምር ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ጠቅሶ በአሁኑ ወቅት ወቅታዊውን ሁኔታ መሠረት ያደረገ ጥናት እየተከናወነ ቢሆንም ጥናቱ ተጠናቆ ይፋዊ መመሪያ እስካልወጣ ድረስ ነባሩ ታሪፍ ብቻ ተፈጻሚ መሆን እንዳለበት አሳስቦ ነበር።


ከታሪፍ ውጪ የሚደረግ ማንኛውም የዋጋ ጭማሪ ሕገ-ወጥ መሆኑን የገለጸው ቢሮው የቁጥጥር ሂደቱ የተሳፋሪዎችን መብት ሙሉ በሙሉ ማስከበር እንዲችል በአቅራቢያው ያሉ የትራፊክ ፖሊሶችና ተቆጣጣሪዎች ፈጥነው የሚደርሱበት የቅንጅት አሠራር እንደሚጠናከር አስታውቋል።



ይህ የሕግ አስከባሪነት ሚና በአሽከርካሪዎች ላይ ብቻ ሳይወሰን አባሎቻቸውን የመቆጣጠርና የስነ-ምግባር ኃላፊነት ባለባቸው የትራንስፖርት ማኅበራትና ባለንብረቶች ላይም ጭምር አስተማሪ አስተዳደራዊ ቅጣቶችን እንደሚጥልም ተጠቁሟል።



የከተማዋ ነዋሪዎች ከተቀመጠው ሕጋዊ ታሪፍ በላይ እንዲከፍሉ መገደዳቸውን፣ ከልክ በላይ ትርፍ መጫንና የተሳፋሪዎች መጉላላትን፣ በጉዞ መካከል መንገድ ላይ በድንገት ማውረድና የሥነ-ምግባር ጉድለቶችን፣ እንዲሁም ያለ ታርጋ ማሽከርከርና በተሽከርካሪዎች ላይ የሚፈጸሙ ስርቆቶችን በመጥቀስ ቅሬታ እንደሚያቀርቡ ይታወቃል።

SM
ስለ ጸሐፊው

Samuel Mulgeta

53 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።