የታክስ ማጭበርበርን ለመከላከል 10 ዓመታት ወደኋላ በመሄድ ሂሳብን በመመርመር ወይም ሂሳብ ኦዲት በማድረግ ተጨማሪ ግብር ማስከፈልን ለገቢ ሰብሳቢው የሚፈቅድ አዋጅ ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ቀረበ፡፡
ትናንት ግንቦት 27 ቀን 2018 ዓ.ም ለምክር ቤቱ የቀረበው ረቂቅ አዋጁ የታክስ ማጭበርበርን በዘላቂነት ለመከላከል ሲባል የገቢ ሰብሳቢው ባለሥልጣን የታክስ ስወራ መፈጸሙን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ካገኘ የግብር ከፋዮችን የሒሳብ ሰነድ እስከ 10 ዓመታት ወደኋላ በመሄድ በድጋሚ የመመርመር (ኦዲት የማድረግ) እና ተጨማሪ ግብር የማስከፈል ሰፊ ሥልጣን የሚሰጥ ነው።
በዚህ የፌዴራል ታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 ማሻሻያ ረቂቅ “አንቀጽ 28” ላይ እንደተደነገገው ባለሥልጣኑ የማጭበርበር ድርጊት መፈጸሙን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ካገኘ የታክስ ስሌት ማስታወቂያውን ካቀረበበት ቀን ጀምሮ በሚቆጠር የ10 (አስር) ዓመት የይርጋ ጊዜ ውስጥ የታክስ ስሌቱን በድጋሚ ኦዲት በማድረግ ሊያሻሽል ይችላል።

ይህ የ10 ዓመት ገደብ ሊቀመጥ የቻለው በኢትዮጵያ የንግድ ሕግና የሒሳብ አያያዝ ሕጎች መሠረት የሒሳብ ሰነዶች ተጠብቀው መቆየት ያለባቸው ለ10 ዓመታት ብቻ በመሆኑ ሲሆን ተራ ስህተቶች ባሉበት መደበኛ ሁኔታ ግን የይርጋ ጊዜው 5 (አምስት) ዓመት ብቻ ሆኖ እንዲቀጥል ተደንግጓል።
ረቂቅ አዋጁ የሀገሪቱን የታክስ ስወራ ለመግታት ጥብቅ የቁጥጥር ሥርዓት የዘረጋ ሲሆን በተለይም ደረሰኝ ባለመቁረጥ በሚፈጸሙ ግብይቶች ላይ ከባድ አስተዳደራዊና የወንጀል ቅጣቶችን ጥሏል።
ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ለኢትዮጵያ በሰጠው ማሳሰቢያ "የሀገር ውስጥ የታክስ እና ታክስ ያልሆኑ ገቢዎችን የመሰብሰብ አቅምን በከፍተኛ ደረጃ ማጠናከር ያስፈልጋል" ማለቱ መንግሥት አዋጁን ይዞ ለመቅረቡ ትልቅ ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረ ይታመናል።
በሌላ በኩል ረቂቅ አዋጁ በዚህ የቁጥጥርና የኦዲት ሂደት ውስጥ በታክስ ባለሥልጣኑ እና በታክስ ከፋዩ መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችን በአጭር ጊዜ ለመፍታት የሚያስችል አዲስ "የመስማማት ሥርዓት" በገለልተኛ አስማሚ አማካኝነት ስራ ላይ እንዲውል ይፈቅዳል።
ቀደም ሲል በነበረው ሕግ ግብር ከፋዮች የተጣለባቸውን ተጨማሪ ግብር ለመቃወም ቅድሚያ ከተወሰነባቸው የገንዘብ መጠን ከ50 እስከ 75 በመቶ የሚሆነውን ከፍለው ለቅሬታ ሰሚ ለግብር ይግባኝ ኮሚሽን እና በየደረጃው ላሉ ፍርድ ቤቶች ማቅረብ የሚችሉ ቢሆንም ሂደቱ ግን መፍትሔ ለመስጠት ረጅም ጊዜ የሚወስድ ነበር።
አዲሱ አሠራር ግን የቀደመው መደበኛ ሂደት እንዳለ ሆኖ አለመግባባቶችን በሚስጥራዊነት መርህ ላይ በመመስረት በገለልተኛ አስማሚ አማካኝነት በፍጥነትና በአጭር ጊዜ ለመፍታት ትልቅ ዕድል እንደሚሰጥ በረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ ላይ ተመላክቷል።