Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ዜና

አይ ኤም ኤፍ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ባደረገው ስምምነት ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ሊለቅ ነው

SM Samuel Mulgeta Jun 4, 2026 Updated 3h ago 2 ደቂቃ ንባብ 251 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
አይ ኤም ኤፍ  ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ባደረገው ስምምነት ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ሊለቅ ነው

ይህ አዲስ የገንዘብ ድጋፍ የተፈቀደው ኢትዮጵያ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳዋን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን እያሳየች ባለችበት ወቅት መሆኑን የአይ ኤም ኤፍ መግለጫ ጠቅሷል፡፡

ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ባደረገው ስምምነት መሰረት ለኢትዮጵያ ወደ 468 ሚሊዮን የሚጠጋ የአሜሪካ ዶላር ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ሊለቅ መሆኑን አስታውቋል።



ይህ ተጨማሪ ድጋፍ የሚለቀቀው ሁለቱ ወገኖች አምስተኛው ዙር ግምገማ ላይ በባለሙያዎች ደረጃ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተከትሎ ሲሆን ይፋዊ አፈጻጸሙም በድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ እስኪጸድቅ እየተጠበቀ ነው።


የአይ ኤም ኤፍ የባለሙያዎች ቡድን መሪ የሆኑት አቶ አልቫሮ ፒሪስ በትናንትናው እለት በሰጡት መግለጫ አዲሱ ስምምነት በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ ለድርጅቱ ማናጅመንት እና ለሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ቀርቦ እንደሚጸድቅ ገልጸዋል።

Advertisement
Your ad could be here — contact us


ይህ 468 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ የፋይናንስ ድጋፍ ሲፈቀድ ኢትዮጵያ በማሻሻያ ፕሮግራሙ ስር እስካሁን ያገኘችው አጠቃላይ የገንዘብ ድጋፍ መጠን ወደ 2.65 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከፍ ይላል።



ይህ አዲስ የገንዘብ ድጋፍ የተፈቀደው ኢትዮጵያ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳዋን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን እያሳየች ባለችበት ወቅት መሆኑን የጠቀሰው የአይ ኤም ኤፍ መግለጫ በተለይም የወጪ ንግድ፣ የውጭ ምንዛሬ ክምችት እና የመንግሥት ገቢ መሻሻል ማሳየታቸውን እንዲሁም የዋጋ ግሽበት መቀነሱን ገልጿል።



ሆኖም አሁን ላይ በመካከለኛው ምስራቅ የተቀሰቀሰው ጦርነት በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ገጽታ ላይ አዲስ የውጭ ተጽዕኖ መፍጠሩ የገለጸው መግለጫው ጦርነቱ በዓለም አቀፍ የንግድ መስመር ላይ በፈጠረው መስተጓጎል ምክንያት በገቢ ነዳጅና ማዳበሪያ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ማስከተሉንና ጊዜያዊ የነዳጅ እጥረት መፍጠሩን ጠቁሟል።


ይህ ቢሆንም የኢትዮጵያ  የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አሁንም ጠንካራ መሆኑንና በምርት ዕድገትና በዋጋ ግሽበት ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ መጠነኛ መሆኑ ተመላክቷል።


ድርጅቱ አክሎም ይህንን ከባድ የውጭ ተጽዕኖ ለመቋቋም እና አዎንታዊ የኢኮኖሚ መነቃቃቱን ዘላቂ ለማድረግ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲማስቀጠል፣ የውጭ ምንዛሬ ገበያውን አሠራር ማሻሻል እንዲሁም ጥንቃቄ የተሞላበት የወጪ አስተዳደር መከተል እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።



ከዚህ በተጨማሪ የግል ዘርፉን ዕድገት ለማገዝ የንግድ ሁኔታን ማሻሻልና በፋይናንስ ዘርፍ ላይ መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች መሆናቸውን አስታውቋል።



በሌላ በኩል የኢትዮጵያን የዕዳ ዘላቂነት አስተማማኝ ለማድረግ ከኦፊሴላዊ አበዳሪዎች ጋር የሚደረገው የዕዳ መልሶ ማዋቀር ውይይት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝና ከቦንድ ባለቤቶች ጋር የሚደረገው ውይይትም መቀጠሉ ተገልጿል።



ከግንቦት 6 እስከ 20 ቀን 2026 ... በአዲስ አበባ በአካልና ከዚያ በኋላ በበይነመረብ ሲደረግ የቆየውን ይሄንኑ ውይይት ያጠናቀቀው የአይ ኤም ኤፍ ልዑክ በቆይታው ከገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፣ ከከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ከግል ዘርፍ እና ከልማት አጋሮች ተወካዮች ጋር ምክክር ማድረጉን አስታውቋል።

 

SM
ስለ ጸሐፊው

Samuel Mulgeta

43 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።