በሀገር አቀፍ ደረጃ በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ያሉ ሁሉም አሽከርካሪዎች እንደገና ተመዝግበው አስገዳጅ ስልጠና እና የብቃት ማረጋገጫ ምዘና እንዲወስዱ የሚያዝ አዲስ የዲጂታል ቁጥጥር ሥርዓት ሊዘረጋ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የቀረጸው ይህ አዲስ አሠራር በየዓመቱ የሰዎችን ሕይወት የሚቀጥፈውን፣ የአካል ጉዳት የሚያስከትለውንና ከፍተኛ የኢኮኖሚ ኪሳራ የሚያመጣውን የመንገድ ትራፊክ አደጋ ለመግታት ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
ይህ አዲስ አሠራር ከተለመደው የቁጥጥር ሥርዓት በተለየ መልኩ ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ሲሆን ከአሽከርካሪዎች የመጀመሪያ ምዝገባ ጀምሮ እስከ ስልጠና፣ ምዘና እና የሰርተፊኬት አሰጣጥ ድረስ ያለው አጠቃላይ ሂደት በዲጂታል ሲስተም እንዲመራ ተደርጎ የተቀረጸ ነው።
ይህም በአሠራሩ ላይ ግልጽነትን ለማስፈንና የምዘና ሂደቱን ከእጅ ንክኪ ወይም ከሰው ጣልቃገብነት ሙሉ በሙሉ ነፃ ለማድረግ እንደሚረዳ ሚኒስቴሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ አመላክቷል።
በአዲሱ መመሪያ መሠረት ማንኛውም አሽከርካሪ ፈተና ከመውሰዱ በፊት ቅድሚያ ስልጠና መውሰድ ያለበት ሲሆን በተቀመጠው መስፈርት መሠረት አሽከርካሪዎች ብቃታቸውን በማረጋገጥ ብቻ እንዲያሽከረክሩ ይደረጋል።
ይህንን ብሔራዊ ፕሮጀክት በይፋ ወደ ትግበራ ለማስገባት የሚያስችሉ አጠቃላይ የሰነድ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውም የተገለጸ ሲሆን ለዚሁ ሀገር አቀፍ ፕሮጀክት መሳካት የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር ኤስ ዲ ኤስ ሴፍቲ ኤንድ ድራይቪንግ ከተባለ የሥልጠና ተቋም ጋር የምዝገባ፣ የሥልጠና እና የምዘና አገልግሎቶችን በጋራ ለመስጠት የሚያስችል የሥራ ውል ስምምነት ተፈራርሟል።
ማንኛውም አሽከርካሪ በዚህ የብቃት ማረጋገጫ ሂደት ውስጥ ማለፍ ያለበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በቅድሚያ ግን ማንኛውም የሕዝብና የጭነት ተሽከርካሪ የሚያሽከረክሩ አሽከርካሪዎች ምዝገባ፣ ሥልጠና እና ምዘና በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚጀመር ታውቋል።
በመሆኑም የንግድ ተሽከርካሪ አሽከርካሪዎች አስፈላጊውን ቅድመ-ዝግጅት እንዲያደርጉ ሚኒስቴሩ ያሳሰበ ሲሆን አሽከርካሪዎች በበኩላቸው ምዘናው አግባብነት የለውም እያሉ ይገኛሉ።
አሽከርካሪዎች ሚኒስቴሩ ቀድሞ ማስተካከል የነበረበት አዲስ መንጃ ፈቃድ የሚሰጥበትን የታችኛውን ሥርዓት ነበር ያሉ ሲሆን ለመመዘኛው የሚወጣው ክፍያን የተመለከቱ ጥያቄዎችንም አንስተዋል።
በተጨማሪም መንግሥት ራሱ ፈትኖ የሰጠውን መንጃ ፈቃድ “እንደገና ካልመዘንኩህ አትሠራም” ማለት ሕጋዊ መሠረት የለውም ያሉ ሲሆን ከ10 እስከ 30 ዓመት የሥራ ልምድ ያላቸውን አሽከርካሪዎች ሥራ አስፈትቶ ማሰልጠን አግባብነት የለውም ባይ ናቸው።
በሌላ በኩል አሁንም ቢሆን የጽሑፍ ፈተና በኮምፒውተር፣ የተግባር ፈተና በካሜራ እየተሰጠ ባለበት ሁኔታ አዲሱ ሥርዓት ከሰው ንክኪ ነፃ ነው መባሉ ግልጽ እንዳልሆነ አንስተዋል።
ክህሎትን የሚያጎለብት ደጋፊ ስልጠና መስጠት መልካም መሆኑን ያልካዱት አሽከርካሪዎች ይህ መሆን ያለበት አሽከርካሪዎች መንጃ ፈቃድ ሊያድሱ በሚመጡበት ወቅት የግማሽ ወይም የሙሉ ቀን ስልጠና በመስጠት መሆን እንዳለበት ይናገራሉ፡፡