በተለያዩ ሀገራት እጅግ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ከ432 ሺህ በላይ ዜጎችን ወደ ሀገር መመለስ መቻሉን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በዛሬው እለት ይፋ አድርጓል።
ነገር ግን ከእነዚህ ተመላሾች መካከል የተወሰኑት በማቋቋሚያ ማዕከላት ውስጥ የሚጠብቁትን ያህል ድጋፍ ባለማግኘታቸውና ቀድሞ የነበሩበት ቦታ የተሻለ ገቢ ስለሚኖረው በድጋሚ በህገ-ወጥ መንገድ እየተሰደዱ እንደሚገኙ ቀደም ብሎ ተቋሙ አስታውቋል።
እንደሚታወቀው ዜጎች ህይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው ለስደት የሚዳረጉበት ዋነኛው ምክንያት በሀገር ውስጥ ያለው ከፍተኛ የስራ አጥነት ቁጥር፣ ዝቅተኛ ገቢና የኑሮ ውድነት ነው።
በየዓመቱ ከትምህርት ተቋማት የሚመረቁ ወጣቶች ቁጥር፤ ከሚፈጠረው የስራ እድል ጋር ባለመመጣጠኑ እና በውጭ ሀገር በአጭር ጊዜ መበልጸግ ይቻላል በሚለው እሳቤ ሳቢያ ወጣቶች ስደትን ብቸኛ አማራጭ አድርገው እንዲመለከቱት ያደርጋቸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ቀድመው ተሰደው የተለወጡ ሰዎችን በማየት ወጣቶችን ይበልጥ ለስደት ያነሳሳቸዋል።
ይህንን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ደግሞ ህገ-ወጥ ደላሎች የስደቱን አስከፊ አደጋ በመደበቅ እና ሀሰተኛ መረጃዎችን በመስበክ ወጣቶችን በቀላሉ ያታልላሉ።
ነገር ግን መንግስት ዜጎች ሰብዓዊ ክብራቸውና መብታቸው ሙሉ በሙሉ በተጠበቀ አግባብ በህጋዊ መንገድ ተሰማርተው የሚለወጡበትን ስርአት ዘርግቶ ወደ ስራ ማስገባቱን ገልጿል።
በዚህም በዛሬው እለት ይፋ በተደረገው መረጃ መሰረት 432 ሺህ 691 ዜጎችን በጊዜያዊ መጠለያና ማቆያ ማዕከላት ውስጥ በመቀበል የስነ-ልቦና፣ የማህበራዊና የኢኮኖሚ ድጋፍ አገልግሎቶችን በመስጠት ወደ ማህበረሰቡ የማቀላቀል ስራ ተከናውኗል ተብሏል።
ከተመለሱት ዜጎች መካከል 308 ሺህ 155 ወንዶች፣ 101 ሺህ 636 ሴቶች እንዲሁም 22 ሺህ 900 እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊ ህጻናት እንደሚገኙበት ሚኒስቴሩ ገልጿል።

እነዚህ ግለሰቦች በዋናነት ከሳዑዲ ዓረቢያ፣ የመን፣ ኦማን፣ ኳታር፣ ቤሩትና ማይናማር የተመለሱ ሲሆን፤ አንዳንዶቹ ደግሞ በሞያሌ፣ ጋላፊ፣ መተማና ቶጎጫሌ ኬላዎች በድንበር አካባቢ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመውጣት ሲሞክሩ የተያዙ ናቸው።
ይሁን እንጂ የተመላሾችን ዘላቂ ተጠቃሚነትና ሁለንተናዊ ደህንነት ማረጋገጥ አሁንም ትልቅ ፈተና ሆኖ የቀጠለ ሲሆን ቁጥራቸው የበዛ ባይሆንም ወደ ሀገር ቤት ከተመለሱ በኋላ በድጋሚ በህገ-ወጥ መንገድ ከሀገር የሚወጡ ዜጎች እንዳሉ ተሰምቷል።
ይህ የሚሆነው ዜጎቹ ወደ ሀገር ሲመጡ በማቋቋሚያ ሂደቱ ላይ የጠበቁትን ያህል ድጋፍና ፈጣን ማገገሚያ ባለማግኘታቸውና ቀድሞ በነበሩበት ስደት የተሻለ ገቢ ያገኙ ስለነበር ድጋሚ መሄድን በመምረጣቸው ነው።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይህንን ስር የሰደደ ችግር በዘላቂነት ለመፍታትና ዜጎች በሀገራቸው የመስራት እሴት እንዲያዳብሩ ለማድረግ ፍልሰቱን ከጀርባ ሆነው በሚያፋጥኑና ህዝብን በሚያታልሉ ህገ-ወጥ ደላሎች ላይ በትኩረትና በህግ ተጠያቂነት ላይ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።