የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም ታሪክ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ ተደርጎ የተወሰደው የኢትዮ ቴሌኮም አክስዮን ሽያጭ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ሂደቱ ምን ደረጃ ላይ ደረሰ? የሚሉ በርካታ ጥያቄዎች በስፋት ሲሰነዘሩ ቆይተዋል።
ተቋሙ ዛሬ በሰጠው ይፋዊ መግለጫ ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጠ ሲሆን አክስዮን ከገዙት 47 ሺህ 377 ኢትዮጵያውያን ኢንቨስተሮች መካከል 45 ሺህ የሚሆኑት ባለአክስዮኖች መሟላት ያለበትን መረጃ በማሟላት የኢትዮ ቴሌኮም የተረጋገጠ ባለድርሻ መሆን መቻላቸውን አብስሯል።
ይህም አጠቃላይ አክስዮን ከገዙት ኢንቨስተሮች ውስጥ 96 በመቶ የሚሆኑት የተረጋገጠ ባለድርሻ መሆን መቻላቸውን ያሳያል።
ኢትዮ ቴሌኮም ቀደም ብሎ 100 ሚሊዮን መደበኛ አክሲዮኖቹን ለሽያጭ ገበያ አውጥቶ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን ለአራት ወራት ያህል ክፍት ሆኖ በቆየው በዚህ የሽያጭ ሂደት ለሽያጭ ካቀረበው የ10 በመቶ የኩባንያው ድርሻ ውስጥ 10.7 ሚሊዮን መደበኛ አክሲዮኖች ብቻ ሲሸጡ ቀሪዎቹ 89.3 ሚሊዮን አክሲዮኖች ግን ሳይሸጡ መቅረታቸው ይታወቃል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በጉዳዩ ላይ በሰጡት ማብራሪያ ኩባንያው በኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ላይ በይፋ መመዝገቡን ገልጸው አክስዮኑ በኩባንያው በኩል የመደልደል እና የማጸደቅ ስራ ከሰራ በኋላ በካፒታል ገበያ ባለሥልጣን የጸደቀና ሊስት የተደረገ በመሆኑ የተረጋገጡት ባለአክስዮኖች ድርሻቸውን በገበያው ላይ የመሸጥ፣ የመግዛትና የማዘዋወር ሙሉ ህጋዊ መብት ማግኘታቸውን አስረድተዋል።
በርካታ ባለአክስዮኖች መጀመሪያ ላይ ያላሟሏቸው መረጃዎች ስለነበሩ እነዛን መረጃዎች የመመርመር እና የማሟላት ስራ ጊዜ ተወስዶ ሲሰራ መቆየቱንም ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ከዛሬ ጀምሮ አሁን ላይ መረጃቸውን የያዙት 45 ሺህ ባለአክሲዮኖች የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ፈቃድ ከሰጣቸው የኢንቨስትመንት ባንኮች፣ ዲለሮች ወይም ብሮከሮች ዘንድ በመሄድ አካውንት መክፈትና ለመገበያየት የሚያበቃቸውን ደረጃዎች መፈጸም እንደሚኖርባቸው በመግለጫው ተነስቷል።
በሌላ በኩል የተወሰኑ ገዢዎች ግን ከባለድርሻነት ዝርዝር ውጭ መሆናቸውን የገለጹት ስራ አስፈጻሚዋ የቀሩት 3.4 በመቶ ወይም 1 ሺህ 646 የሚሆኑት አክስዮን ገዢዎች የብሔራዊ መታወቂያ (ፋይዳ) ቁጥር ማቅረብ ባለመቻላቸው ምክንያት እስካሁን ወደ ቀጣዩ ሂደት ሳይሸጋገሩ ቀርተዋል ብለዋል።
ሆኖም እነዚህ ዜጎች በቀጣይ የብሔራዊ መታወቂያ ቁጥራቸውን ካቀረቡ ባለድርሻ መሆን የሚችሉ ሲሆን አክስዮን ከገዙት ውስጥ 248 የሚሆኑት ገዢዎች ኢትዮጵያውያን ባለመሆናቸው ምክንያት ተቀባይነት ባለማግኘታቸው የከፈሉት ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ተመላሽ እንደሚደረግላቸው ታውቋል።
የትርፍ ድርሻ ክፍፍልን በሚመለከት በቦርድ እና በአጠቃላይ ጉባኤው በሚሰጠው አቅጣጫ እና ውሳኔ መሰረት የሚወሰን ሲሆን የኩባንያው የቢዝነስ ካላንደር ከሐምሌ እስከ ሰኔ የሚመራ በመሆኑ የዚህ በጀት አመት እንደተጠናቀቀ አጠቃላይ አፈጻጸሙን ለባለአክሲዮኖች ይፋ ይደረጋል ተብሏል።
የኩባንያው የፋይናንስ አፈጻጸም በውጭ ኦዲተር ተመርምሮ ሲጠናቀቅ በዌብሳይት ላይ ይፋ የሚደረግ ሲሆን በጀት ዓመቱ በተጠናቀቀ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ የሚጠራበትንና 45 ሺህ ባለአክሲዮኖች የሚሰበሰቡበትን ስነ-ስርዓት ኢትዮ ቴሌኮም ከካፒታል ገበያ ባለስልጣን ጋር በመመካከር በቀጣይ ያሳውቃል ተብሏል።