Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ዜና

የዳቦ ዋጋ ጭማሪ፡ ምክንያቶች እና የሸማቾች ስጋት

SM Samuel Mulgeta May 24, 2026 Updated 3h ago 2 ደቂቃ ንባብ 121 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
የዳቦ ዋጋ ጭማሪ፡ ምክንያቶች እና የሸማቾች ስጋት

በአዲስ አበባ ከተማ በዳቦ ላይ የታየው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ከመንግስት የዋጋ ቁጥጥር መነሳት ጋር ተያይዞ በተጣለው አዲስ የ2.5 በመቶ የሽያጭ ግብር እና በዱቄት ግብዓት መናር ምክንያት የመጣ መሆኑ ይፋ ተደርጓል።

 


እንደሚታወቀው በመዲናዋ ቀደም ሲል 10 ብር ይሸጥ የነበረው ባለ 90 ግራሙ ዳቦ አሁን ላይ እስከ 15 ብር፣ ባለ 130 ግራሙ ደግሞ እስከ 25 ብር ከፍ ያለ ሲሆን፤ ከፍተኛ መጠን ያለው ባለ 250 ግራሙ ዳቦ ደግሞ ዋጋው እጥፍ በመጨመር እስከ 50 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ ሸማቾች በምሬት እየገለጹ ይገኛሉ።



ይህ ማለት ደግሞ መሠረታዊ የሆነውን የዕለት ጉርስ ለመሸፈን የሚታገሉ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰፊ ማኅበረሰቦችና ቁጥራቸው የበዛ ቤተሰቦች፤ የዳቦ ዋጋ በዚህ ፍጥነት በመናሩ ምክንያት የዕለት የምግብ ፍላጎታቸውን ማሟላት የማይችሉበት እና ዳቦ መግዛት ራሱ እንደ ቅንጦት የሚታይበት እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ መፈጠሩን ያሳያል።

Advertisement
Your ad could be here — contact us



በሌላ በኩል ዋጋ ባልጨመሩ የተወሰኑ አካባቢዎች ላይ ደግሞ የዳቦ ቤቶች የዳቦውን መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ማለትም ባለ 90 ግራሙን ወደ 70 ግራም በመቀነስ እየሸጡት መሆኑ በመሬት ላይ ያለው ኑሮ እየከበደ መምጣቱን ጠቋሚ ነው።



ይህ አሠራርና የዋጋ መናር የኅብረተሰቡን የመግዛት አቅም ያላገናዘበ በመሆኑ ከፍተኛ ቅሬታ እየቀረበበት ቢሆንም የዳቦ አምራቾችና ነጋዴዎች ግን ለዚህ ጥብቅ እርምጃ የራሳቸውን ምክንያቶች ያቀርባሉ።



በዋናነት ከሚያነሷቸው ምክንያቶች አንዱ የዱቄት ዋጋ በአንድ ኪሎ ላይ እስከ 24 ብር መናሩ ሲሆን የምግብ ዘይት ላይ የተደረገው ጭማሪ እንዲሁም የስኳር እና የቤት ኪራይ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ተጠቃሽ ናቸው።



በመሆኑም ይህንን የግብዓት ዋጋ ግሽበት መቋቋም ባለመቻላቸው ከቢዝነሱ ሙሉ በሙሉ ላለመውጣት ሲሉ ዋጋ ለመጨመር ወይም ግራም ለመቀነስ መገደዳቸውን ይገልጻሉ።



ይሁን እንጂ ከዚህ የዱቄትና የዳቦ ዋጋ መናር በስተጀርባ እንደ ዋና ምክንያት የሚጠቀሰው መንግስት ተግባራዊ ያደረገው አዲሱ የታክስና የገበያ መመሪያ ነው።



መንግሥት ቀደም ሲል በዳቦና ዱቄት ላይ ይደረግ የነበረውን የዋጋ ተመን ቁጥጥር ሙሉ በሙሉ አንስቶ ገበያውን ነጻ ማድረጉ ይታወቃል።



በዚህም ከዚህ ነጻ ገበያ ጎን ለጎን አምራቾች ከጠቅላላ ሽያጫቸው ላይ 2.5 በመቶ የሽያጭ ግብር እንዲከፍሉ በመወሰኑ ግብሩን ለመሸፈንና ትርፋቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ የዱቄት ዋጋን ለመጨመር ተገደዋል።



በዚህ እና በሌሎች የግብይት ሂደቶች ላይ የቁጥጥር ስራ የሚያከናውነው የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በበኩሉ የዳቦን ዋጋ በቀጥታ እንደማይቆጣጠርና ገበያው ነጻ መሆኑን ቢያረጋግጥም የትርፍ ጣሪያው ግን ሕጋዊ ገደብ እንዳለው አስታውቋል።



ይሁን እንጂ አንድ ነጋዴ ከግብዓት ወጪው በላይ ማግኘት የሚችለው ከፍተኛው የትርፍ መጠን 20 በመቶ ብቻ ሲሆን ከዚህ በላይ ማትረፍ ግን ያለአግባብ መበልጸግ በመሆኑ በሕግ የሚያስተይቅ እንደሆነ ተነግሯል

 

SM
ስለ ጸሐፊው

Samuel Mulgeta

27 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።