በቤተልሄም ሰለሞን!
ለረጅም ዓመታት በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘንድ በአሉታዊና በአንድ ወገን ገፅታ ብቻ ስትሳል የነበረችው ኢትዮጵያ አሁን ላይ ግን ታሪኳንና እውነታዋን በራሷ ልጆች፣ በአፍሪካውያንና በዓለም አቀፍ የዲጂታል ታሪክ ነጋሪዎች አማካኝነት በመቀየር ላይ ትገኛለች።
በተለይም የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ የዓለም አቀፍ ዩቲዩበሮች፣ ቲክቶከሮች፣ ታዋቂ አርቲስቶች፣ የስፖርት ባለሙያዎች፣ የሀገራት መሪዎችና ቱሪስቶች ቀዳሚ የጉዞ መዳረሻ እየሆነች ትገኛለች።
በቅርቡ የመጀመሪያውን የአፍሪካ ሶሻል ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤን (ASMIS 2026) በደመቀ ሁኔታ ላስተናገደችው አዲስ አበባ ይህ እድል የኢትዮጵያን ቅርስ፣ ባህል እና የቱሪዝም ሀብት ለዓለም ገበያ ለማስተዋወቅ ታላቅ እድል ሆኖ ተገኝቷል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሀገሪቱን የቱሪዝም መስህብነት እና ቀልብ ሳቢነት በተግባር ካሳዩት ታላላቅ ክስተቶች መካከል በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ጉልበቱና አስቂኝ ድርጊቶቹ የሚታወቀው አሜሪካዊው ወጣት ዩቲዩበሪ "አይሾው ስፒድ" በአዲስ አበባ ያደረገው ጉብኝት አንዱ ነበር።

ይህም ቆይታ በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች ስለ ኢትዮጵያ ቱሪዝም እና ታሪክ እንዲያውቁና ወደ ኢትዮጵያ መምጣት እንዲፈልጉ ትልቅ መነቃቃትን ፈጥሮ አልፏል።
ይህንኑ የተጀመረውን ጉብኝት በመቀጠል በአሁኑ ወቅት ከ19 ሚሊዮን በላይ የቲክቶክ ተከታዮች ያሉትና በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ የሚታወቀው የይዘት አዘጋጅ ዲላን ፔጅ በአዲስ አበባ በመገኘት ሰፊ የባህልና የቅርስ ጉብኝት መርሃ ግብር ጀምሯል።
የእነዚህ ታዋቂ ግለሰቦች መጉረፍና የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ቀልብ መሳብ የሀገሪቱን የቱሪዝም ገፅታ በከፍተኛ ደረጃ እየቀየረው የሚገኝ ሲሆን በተለይም በቅርቡ የቱርክ ፕሬዝዳንት ኤርዶሃን ወደ አዲስ አበባ በመጡበት ወቅት አዲስ በተገነቡት የአዲስ አበባ ሰፋፊ ጎዳናዎች፣ ዘመናዊ መብራቶችና ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች መካከል ሲጓዙ የሚያሳየው ቪዲዮ በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ "ቫይራል" መውጣቱ የዚህ ትልቅ ማሳያ ነው።
የአርሰናል የቀድሞ እግር ኳስ ተጨዋች የሆነው ባካሪ ሳኛን ጨምሮ በርካታ የውጭ ሀገር ዜጎች በከተማዋ ሁለንተናዊ ለውጥና ውበት ላይ ያላቸውን ታላቅ አድናቆት መግለጻቸው የሚታወስ ሲሆን ይዘት ፈጣሪዎቹ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዓለም አቀፍ ተከታዮቻቸው የኢትዮጵያን ባህላዊ እሴቶች በማጋራት ሀገሪቱ ያላትን ጥንታዊ ማንነት ከዘመናዊነት ጋር እንዴት አዋህዳ እንደያዘች ያስተጋባሉ።
በአጠቃላይ የእነዚህ ግህለሰቦች ጉብኝት ዋነኛ ፋይዳው ኢትዮጵያ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ መድባ ልታከናውነው የማይችለውን ሰፊ የቱሪዝም ማስተዋወቅ በማከናወን የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደጋቸው ነው።
ከዚህም ባሻገር ለዘመናት ስለ ሀገሪቱ የተገነቡትን የተዛባና አሉታዊ ትረካ በአንድ ጀንበር በመስበር አዲስ አበባ ምን ያህል ዘመናዊ፣ ውብና ሰላማዊ የቱሪስት መዳረሻ መሆኗን በተግባር ያሳያሉ።
ይህ ሂደት የሀገር በቀል ባህላዊ እሴቶችን፣ ምግቦችንና የቡና ሥነ-ሥርዓትን ለዓለም በማስተዋወቅ የባህል ቱሪዝምን ከማሳደጉም በላይ መዲናዋን ለአፍሪካ የዲጂታል ፈጠራ ዋነኛ ማዕከል በማድረግ አህጉራዊ ተፅዕኖዋን በከፍተኛ ደረጃ ያጠናክረዋል።