Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
አስተያየት

የሜትር ታክሲ አሽከርካሪዎች ከመተግበሪያ የሚመጣ ጥሪን አለመቀበል ጉዳይ!

SM Samuel Mulgeta May 21, 2026 Updated 4h ago 3 ደቂቃ ንባብ 504 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
የሜትር ታክሲ አሽከርካሪዎች ከመተግበሪያ የሚመጣ ጥሪን አለመቀበል ጉዳይ!

በአፕሊኬሽኑ 250 ብር ያሳይ የነበረውን መንገድ አሽከርካሪዎች እስከ 390 ብር በመጠየቅ እያስከፈሉ መሆኑም ተሰምቷል፡፡

 

 በቤተልሄም ሰለሞን!

 

Advertisement
Your ad could be here — contact us

በአዲስ አበባ ከተማ ከሰሞኑ በአንዳንድ የሜትር ታክሲ አሽከርካሪዎች እና ድርጅቶች ላይ ከፍተኛ ቅሬታ እየቀረበ ይገኛል፡፡ የዚህ ቅሬታ መነሻ አሽከርካሪዎች በመተግበሪያ በኩል የሚመጣውን ጥሪ ለማንሳት አለመፈለግ ሲሆን ይህም መንገድ ላይ ከደንበኞች ጋር በመደራደር እየሰሩ ነው የሚል ነው፡፡



የሜትር ታክሲ መጀመር በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንዳመጣ የሚታመን ሲሆን ይህ አሰራር ከተለምዶው የታክሲ ስርዓት በተሻለ በርካታ ችግሮችን የቀረፈ እና የጉዞ ዋጋው በርቀትና በሰዓት የሚሰላ በመሆኑ አሽከርካሪና ተጓዥ ዋጋ ለመደራደር የሚያደርጉትን ጭቅጭቅና አለመግባባት ሙሉ በሙሉ ያስቀረ ነበር።



በተለይም ቀደም ሲል የሚደርሱ ስርቆቶች፣ እቃ መጥፋት ወይም የደህንነት ስጋቶች ከፍተኛ የነበሩ ሲሆን አሁን ግን የአሽከርካሪው፣ የባለቤቱ እና የመኪናው መረጃ በሲስተም ውስጥ ስለሚመዘገብና ጉዞው በጂፒኤስ ክትትል ስለሚደረግበት የደህንነት ስጋት በእጅጉ ቀንሷል፤ የጠፋ እቃን በቀላሉ መፈለግም አስችሏል።



ለብዙ ወጣቶች እና የግል መኪና ላላቸው አሽከርካሪዎች ሰፊ የስራ እድል የፈጠረው አገልግሎቱ በስራ ምክንያት አስቸኳይ ስብሰባ ወይም ጉዳይ ኖሯቸው በሰልፍ መዘግየት የማይፈልጉ፣ ከተማዋን በደንብ የማያውቁ፣ የከተማዋን የታክሲ ዋጋ ተደራድረው ለመክፈል የሚቸገሩ ግለሰቦች፣ መደበኛ ትራንስፖርት በብዛት በማይገኝበት የምሽት ሰዓት የሚንቀሳቀሱ እንዲሁም ከኤርፖርት የሚመጡ ወይም ድንገተኛ የህክምና ጉዳይ የገጠማቸው ሰዎች ቀዳሚ ምርጫቸው አድርገው ሲጠቀሙት ይስተዋላል።



ነገር ግን ከሰሞኑ የሜትር ታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች አሽከርካሪዎች አገልግሎቱ ለማግኘት የሚረዳውን መተግበሪያ ባለመጠቀም ጥሪዎችን ባለመቀበል፣ ትዕዛዞችን በራሳቸው በመሰረዝ እና መንገድ ላይ ከደንበኞች ጋር በመደራደር ላይ መሆናቸው ቅሬታ እያስነሳ ይገኛል።



ይህ የአሽከርካሪዎች አዲስ አካሄድ አንዳንድ ድርጅቶቹ ሳያሻሽሉት ለረጅም ጊዜ በቆየ የታሪፍ ማሻሻያ እና በወቅታዊው የነዳጅ ዋጋ መጨመር መሀል የመጣ አለመግባባት የፈጠረው ሲሆን በዚህ ሳቢያ የከተማዋ የቴክኖሎጂ ታክሲ ተጠቃሚዎች ለከፍተኛ የገንዘብ ብዝበዛና ለደህንነት ስጋት መጋለጣቸውን በምሬት እየገለጹ ይገኛሉ።

 



ደንበኞቹ በአሁኑ ወቅት በፌርማታም ሆነ በመኖሪያ አካባቢዎች በአፕሊኬሽን የሚታዘዙ መኪኖች ጥሪን በፍጹም የማይቀበሉበት ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን በአንጻሩ ግን መኪኖቹን መንገድ ላይ በራሳቸው አስቁመው ሲሳፈሩ አሽከርካሪዎች ያለ ምንም ችግር አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ መሆናቸውን ይናገራሉ።



ይሁን እንጂ ይህ ከመተግበሪያ ውጪ የሚደረግ ጉዞ የድርጅቱን የዋጋ ተመን ስለማይከተል ቀደም ሲል በአፕሊኬሽኑ 250 ብር ያሳይ የነበረውን መንገድ አሽከርካሪዎች እስከ 390 ብር በመጠየቅ እያስከፈሉ መሆኑን ቅሬታ አቅራቢዎች ይናገራሉ።



በተጨማሪም የደንበኞች ቅሬታ የሚያሳየው አንዳንድ አሽከርካሪዎች ጥሪ ተቀብለው ደንበኛው ጋር ከደረሱ በኋላ አያዋጣኝም ስለዚህ አቋርጠው እና በውጭ እንደራደር የሚሉ ግፊቶችን እንደሚያደርጉ ነው።



አሽከርካሪዎች በበኩላቸው ለዚህ ተግባራቸው ዋነኛ ምክንያት አድርገው የሚያቀርቡት የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩንና ከዚህ በፊት ድርጅቶቹ ያደረጉት የታሪፍ ማሻሻያ ከወቅታዊው የገበያ ሁኔታ ጋር የማይመጣጠን መሆኑን ነው።



አሽከርካሪዎች እንደሚሉት ድርጅቶቹ ደንበኞችን ላለማጣት ሲሉ የታሪፍ ጭማሪውን ዝቅተኛ በማድረጋቸው፣ የነዳጅና የኑሮ ጫናው ሙሉ በሙሉ በእነሱ ላይ አርፏል። በዚህም በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች ቅሬታቸው እያሰሙ የቆዩ ሲሆን በድርድር የሚሰሩ መተግበሪያዎችን በማዘጋጀት ወይም ዋጋውን ለደንበኛው በማሳየት እና እነሱ ደግሞ የሚያዋጣቸውን በመጥራት ለመጓዝ መምረጣቸውን ይናገራሉ።



ይህንን ጥያቄ የማይቀበሉ ደንበኞች ደግሞ ጉዟቸው የሚሰረዝ ሲሆን፣ ወደ ድርጅቶቹ የጥሪ ማዕከል በመደወል አቤቱታ ለማቅረብ በሚሞክሩበት ወቅትም የኦፕሬተሮች ስልክ አለማንሳት፣ ረጅም ሰዓት ማስጠበቅና መኪና አለመገኘት ሌላው የእንግልት ምንጭ ሆኗል።



በመሆኑም ችግሩ አሽከርካሪውን ብቻ በመውቀስ ወይም ድርጅቶቹን ብቻ በመጫን መፍትሄ የማይቀረፍ በመሆኑ የዋጋ ድርድርን የሚያስተናግዱ መተግበሪያዎች፣ ደንበኛ ጋር ሄደው ትዕዛዝ የሚሰርዙ ወይም ተደጋጋሚ ጥሪዎችን ያለምክንያት የማይቀበሉ አሽከርካሪዎችን መለየት፣ ድርጅቶቹ ከአሽከርካሪዎች የሚወስዱትን ኮሚሽን ማስተካከል እንዲሁም ድርጅቶች ደንበኛ እንዳይጠፋ በሚል ዋጋን ማርከስ ብቻ ሳይሆን አሽከርካሪውም አትርፎ በስራው ላይ እንዲቆይ እንዲያደርጉ ይመከራል።

 

SM
ስለ ጸሐፊው

Samuel Mulgeta

27 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።