Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ዜና

አነጋጋሪው አዲሱ የታክስ አዋጅ

SM Samuel Mulgeta May 21, 2026 Updated 3h ago 3 ደቂቃ ንባብ 442 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
አነጋጋሪው አዲሱ የታክስ አዋጅ

ታክስ ከፋዮች በይግባኝ ሒደት ላይ አዲስ ማስረጃ ማቅረብ አይችሉም ተብሏል፡፡

ከገንዘብ ሚኒስቴር የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ በአዲሱ የታክስ አስተዳደር አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ ላይ ታክስ ከፋዮች በኦዲት ወቅት ካቀረቡት ውጭ በይግባኝ ሒደት ላይ አዲስ ማስረጃ እንዳያቀርቡ የሚከለክል ጥብቅ ድንጋጌ ተካቷል።

 

ይህ ማለት ደግሞ፣ አንድ የንግድ ድርጅት ወይም ነጋዴ በኦዲት ወቅት ሳይገኝ ቀርቶ ወይም ተደብቆ የነበረን ወሳኝ የወጪ ሰነድ፣ የባንክ መግለጫ (Bank Statement) አሊያም የደረሰኝ ኮፒ በኋላ ላይ ፈልጎ ቢያገኘው እንኳ፣ የተጣለበትን ከፍተኛ ግብር ለማስቀነስ እንደ አዲስ ማስረጃ አቅርቦ የመከራከር መብቱ ሙሉ በሙሉ ይገደባል ማለት ነው።

Advertisement
Your ad could be here — contact us

 

ይህ አሠራር በመሬት ላይ ካለው ተጨባጭ የንግድ እንቅስቃሴ እውነታ ጋር የሚጋጭ ሲሆን፣ በተለይም በአራትና በአምስት ዓመታት የቆዩ የሒሳብ ሰነዶች ድንገት በሚፈተሹበት ወቅት በሠራተኛ መለዋወጥ፣ በቢሮ ዝውውር፣ ወይም ከአቅም በላይ በሆኑ ተፈጥሯዊ አደጋዎችና ስርቆት ምክንያት ሰነዶች ሊዘነጉ ወይም ሊጠፉ እንደሚችሉ ከግምት ያላስገባ ነው በመባል ወቀሳ እየቀረበበት ይገኛል።

 

ሰነዱ ራሱ በገቢዎች ባለሥልጣን እጅ የሚገኝበት አጋጣሚ እንኳ ቢኖር፣ በወቅቱ አልቀረበም በሚል ብቻ በኋላ ላይ "አዲስ መረጃ ነው" ተብሎ ውድቅ መደረጉ፣ ታክስ ከፋዩ ራሱን በሕግ ፊት በአግባቡ የመከላከል መብቱን የሚነፍግና ፍጹም ሚዛናዊነት የጎደለው አሠራር እንደሆነ ተነግሯል፡፡

 

ይሁን እንጂ መንግሥት ለዚህ ጥብቅ አቋም የሚሰጠው ማብራሪያ እንደሚያሳየው፣ ሕጉ አዳዲስ ማስረጃዎችን ሙሉ በሙሉ ከመከልከል ይልቅ ታክስ ከፋዮች ያለምንም በቂ ምክንያት የክርክር ጊዜን እንዳያባክኑና የታክስ ማስተዳደር ጫናን ለመቀነስ ታስቦ የተዘጋጀ ነው።

 

በመሆኑም አዲሱ ረቂቅ አዋጅ አዲስ ማስረጃዎችን በልዩ ሁኔታ ለማስተናገድ ሦስት ዋና ዋና መመዘኛዎችን አስቀምጧል።

 

የመጀመሪያው፣ ሰነዱ ባለመታየቱ ምክንያት በግብር ከፋዩ ላይ ሊሸከሙት የማይችሉት ከፍተኛ የታክስ ዕዳ ጫና የሚፈጥር መሆኑ ሲረጋገጥ ሲሆን፤ ሁለተኛው፣ ታክስ ከፋዩ አዲሱን ሰነድ ሊያገኝ የቻለው የታክስ ውሳኔው ሙሉ በሙሉ ከተሰጠ በኋላ መሆኑ ሲታመን፤ እና ሦስተኛው፣ ሰነዱ በኦዲት ወቅት ሳይቀርብ የቀረው ከአቅም በላይ በሆነ ተጨባጭ ምክንያት መሆኑ ሲረጋገጥ ብቻ ነው። እነዚህ ሦስት መመዘኛዎች ተሟልተው አዲሱ ማስረጃ ተቀባይነት ካገኘም፣ ታክስ ከፋዩ ሰነዱን አስቀድሞ በወቅቱ ባለማቅረቡ ምክንያት ሊከፈል ከሚገባው የታክስ ዕዳ ላይ ተጨማሪ 20 በመቶ ቅጣት እንዲከፍል ይገደዳል። ይህ አካሄድ ግብር ከፋዮች የፈተና ውጤት ሲመጣ ደብተር እንደሚፈልግ ተማሪ ሳይሆኑ፣ ገና ከጅምሩ ሒሳባቸውንና መረጃዎቻቸውን በጥንቃቄና በሥርዓት እንዲይዙ ለማስገደድ የወጣ የቁጥጥር ሥርዓት ነው ተብሏል።

 

በሌላ በኩል ደግሞ፣ በረቂቅ አዋጁ ላይ የተካተተውና ከፍተኛ መደናገጥን የፈጠረው ሌላው ድንጋጌ ደረሰኝ የመቁረጥ ግዴታን ባልተወጡ ታክስ ከፋዮች ላይ የሚጣለውን የገንዘብ ቅጣት መጠን በእጥፍ በማሳደግ በእያንዳንዱ ባልተቆረጠ ደረሰኝ 100 ሺህ ብር እንዲቀጣ መደንገጉ ነው።

 

ይህ ማለት ደግሞ፣ አንድ ነጋዴ በቸልተኝነት፣ በሠራተኛ ስህተት ወይም በሌላ በማንኛውም ምክንያት አምስት ደረሰኞችን ሳይቆርጥ ቢቀር ብቻ የተደራራቢ ቅጣቱ ድምር ግማሽ ሚሊዮን ብር ይደርሳል ማለት ሲሆን፣ ይህም ድርጅቶችን በቀጥታ ለኪሳራና ለመዘጋት የሚዳርግ እጅግ በጣም ከበድ ያለ ሳይንሳዊ ስታንዳርድ የሌለው የቅጣት መጠን ነው በሚል ትችት ቀርቦበታል።

 

ምንም እንኳን ይህ የቅጣት ጭማሪ የተደረገው ሕግ የሚጥሱ አጥፊዎችን ለማስተማርና ሌሎች ተመሳሳይ ጥፋት እንዳይፈጽሙ መከላከያና መቀጣጫ ለማድረግ እንደሆነ በመንግሥት በኩል ቢገለጽም፣ አሁን ባለው ተጨባጭ የገበያ ሁኔታ ግን እንዲህ ዓይነት አቅምን ያላገናዘበ የገንዘብ ቅጣት በንግዱ ማኅበረሰብ ላይ ከፍተኛ የስነ-ልቦና ጫናና ፍርሃትን በመፍጠር ነጋዴዎች ከመንግሥት ጋር በመተማመን ላይ የተመሠረተ የግብር ሥርዓት ከመዘርጋት ይልቅ ከሕጋዊው መስመር እንዲሸሹ በር ሊከፍት ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።

 

 

SM
ስለ ጸሐፊው

Samuel Mulgeta

27 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።