የባንክ አካውንትን ከብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ (ፋይዳ) ጋር የማያያዝ ሂደት የተቀመጠለት ቀነ ገደብ ሙሉ በሙሉ በማለቁ ምክንያት ህጉ ወደ ሙሉ ተግባራዊነት ተሸጋግሯል። በዚህም ታዲያ አሁን መታወቂያቸውን ያላያያዙ ደንበኞች የባንክ ሂሳብ እንዳይንቀሳቀስ ሙሉ በሙሉ ታግዷል። ይሁን እንጂ የጊዜ ገደቡ መጠናቀቅን ተከትሎ ግዴታቸውን በትክክል ተወጥተው መረጃቸውን በኦንላይን አማካኝነት ያያያዙ በርካታ ደንበኞች ጭምር አካውንታቸው በመዘጋቱ ምክንያት ከፍተኛ እንግልትና መደናገር እየደረሰባቸው እንደሚገኝ መመልከት ችለናል፡፡
ታዲያ ገበያ ሚዲያ ባደረገው ማጣራትም፤ ይህ በርካታ ጥንቁቅ ደንበኞችን ጭምር ሰለባ ያደረገው መጠነ-ሰፊ የሂሳብ መዘጋት ችግር በሁለት ዋና ዋና ክፍተቶች ዙሪያ የሚፈጠር መሆኑን ለመገንዘብ ችሏል፡፡ አንደኛው ምክንያት ደንበኞች በኦንላይን መረጃቸውን ሲያስገቡ የነበረው ከፍተኛ መጨናነቅ የባንኮቹን ሰርቨሮች አቅም በመፈታተኑ፣ መረጃው በተሳካ ሁኔታ መላኩ ቢገለጽም ሲስተሙ በትክክል ሳይቀበለውና ሳያረጋግጠው ስለቀረ ነው፡፡
ሁለተኛውና ዋናው የችግሩ ምንጭ ደግሞ በባንክ አካውንት መዝገብ እና በፋይዳ መታወቂያ ላይ ባሉ መረጃዎች መካከል ጥቃቅን የፊደል አጻጻፍ ልዩነቶች ወይም የስልክ ቁጥር አለመገጣጠሞች በመኖራቸው፣ የኦንላይን ማመልከቻቸው ተቀበባይነት ሳያገኝ ውድቅ በመደረጉ ነው።
ታዲያ ከባንኮች ባገኘነው መረጃ መሰረት ተገልጋዮች የፋይዳ መታወቂያቸውን ይዘው አካውንታቸውን ወደከፈቱበት የባንክ ቅርንጫፍ በአካል በመገኘት ማስተካከል ይችላሉ፡፡ የባንክ ሰራተኞች የደንበኛውን ማንነት በአካል ካረጋገጡ በኋላ በሲስተሙ ላይ ያለውን የተሳሳተ የፊደል አጻጻፍ ከፋይዳ መታወቂያው ጋር እኩል አድርገው የሚያስተካክሉ ሲሆን፣ የማስተካከያ ስራ እንደተጠናቀቀ የታገደው የባንክ አካውንት ምን አልባት ከሁለት ሰዓት በኋላ ውስጥ ተከፍቶ ወደ መደበኛ ስራው እንደሚመለስ ባደረግነው ማጣራት ችለናል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ከሀገር ውጭ የሚኖሩና በስደት ያሉ በርካታ ዜጎች የማረጋገጫ ኮድ (OTP) በስልካቸው ላይ ባለመምጣቱ ምክንያት ለገጠማቸው ስጋት የዲጂታል አማራጭ መፍትሄ ተዘርግቷል። በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የባንክ አካውንታቸውን ከፋይዳ ቁጥራቸው ጋር ለማስተሳሰር መረጃቸውን በኢሜል ጭምር ማስመዝገብ የሚችሉ ሲሆን፣ ይህም ስልክ ቁጥራቸው በተለያየ ምክንያት ባይሰራ ወይም የባህር ማዶ ኔትወርክ መልዕክት ባይቀበል እንኳ የማረጋገጫ ኮዱ በቀጥታ ወደ ኢሜላቸው እንዲገባ ያደርጋል። ይህ አገልግሎት በእያንዳንዱ ባንክ የዲጂታል መተግበሪያዎች ላይ ተግባራዊ የተደረገ በመመሆኑ፣ ተገልጋዮች በየትኛውም የዓለም ክፍል ሆነው የባንክ አካውንታቸውን ከፋይዳ ጋር ማያያዝ ይችላሉ፡፡
በውጭ ሀገር የሚኖሩና በአሁኑ ወቅት የፋይዳ መታወቂያ ምዝገባ አገልግሎት ጨርሶ ባልተጀመረባቸው ሀገራት ለሚገኙ ዜጎች ግን ጊዜያዊ ማመቻቻ አሰራር በስራ ላይ ውሏል። የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባው በአሁኑ ሰዓት በውጭ ሀገራት በስፋት ያልተዘረጋ በመሆኑ፣ ዜጎች ሀገር ውስጥ የሌሉ መሆኑን የሚያስረዳ አግባብነት ያለው መረጃ ለባንኮቻቸው በማቅረብ ከዚህ አስገዳጅ ትስስር ለጊዜው ነፃ (Exempt) መሆን ይችላሉ። ብሔራዊ ባንክ ለእያንዳንዱ የፋይናንስ ተቋም ባስተላለፈው ጥብቅ መመሪያ መሠረት፣ እነዚህ ደንበኞች ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ያህል የባንክ እንቅስቃሴያቸው ሳይገደብ ጊዜያዊ እፎይታ የተሰጣቸው ሲሆን፣ አገልግሎቱ በየሀገራቱ ባሉ ኤምባሲዎችና ቆንስላዎች በኩል በስፋት መተግበር ሲጀምር ግን ባሉበት ቦታ ሆነው ምዝገባውን ማከናወንና አካውንታቸውን ማያያዝ እንደሚጠበቅባቸው ተመልክቷል።