ኢራን ትራምፕን ለሚገድል አካል የ50 ሚሊዮን ዩሮ ሽልማት ልትሰጥ ነው
ግንቦት 8/2018 (ገበያ ሚዲያ) የኢራን ፓርላማ የአሜሪካውን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን ለሚገድል ማንኛውም ግለሰብ ወይም ተቋም መንግሥት 50 ሚሊዮን ዩሮ ሽልማት እንዲከፍል የሚያስገድድ የሕግ ረቂቅ እያዘጋጀ መሆኑን አንድ ከፍተኛ የኢራን ሕግ አውጪ አስታውቀዋል።
ይህ እርምጃ የተወሰደው አሜሪካ እና እስራኤል የኢራንን መሪ እና ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦችን ለደመሰሱበት ጥቃት አጸፋ ለመመለስ ታስቦ መሆኑ ተገልጿል።
በተጨማሪም ከአሜሪካ ጋር ተደርሶ የነበረው የተኩስ አቁም ስምምነት መፍረሱን ተከትሎ ዳግም ሊቀሰቅስ ከሚችለው ወታደራዊ ግጭት አስቀድሞ በትራምፕ አስተዳደር ላይ ከፍተኛ የፖለቲካ ጫና ለመፍጠር የታለመ ነው ተብሏል።
የፓርላማው የብሔራዊ ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኢብራሂም አዚዚ ለሀገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን እንደተናገሩት ባለፈው መጋቢት ወር ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ ሕግ አውጪዎች በርካታ የሕግ ረቂቆችን ሲያዘጋጁ የቆዩ ሲሆን ከእነዚህም መካከል በወታደራዊ እና በደኅንነት ኃይሎች የሚወሰዱ የአጸፋ እርምጃዎች የሚለው ይገኝበታል።

ሰብሳቢው አክለውም "የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የሴንትኮም አዛዥ ኢላማ ሊደረጉና ተመሳሳይ የአጸፋ እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል፤ ይህ መብታችን ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
የሕግ ረቂቁ ማንኛውም ግለሰብ ወይም ሕጋዊ ሰውነት ያለው አካል ይህንን ተልእኮ ካከናወነ የኢራን መንግሥት 50 ሚሊዮን ዩሮ ሽልማት የመክፈል ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋል።
ከዚህ ይፋዊ የሕግ ረቂቅ ባሻገር የኢራን መንግሥት ከግል ተቋማት ጋር በመተባበር ባለፈው መጋቢት ወር ጀምሮ ለትራምፕ ግድያ የሚውል የገንዘብ ማሰባሰብ ዘመቻ ሲያካሂድ እንደቆየና በሕዝብ የሞባይል ስልኮች ላይ የጽሑፍ መልእክት (SMS) በመላክ ቅስቀሳ እያደረገ መሆኑ ተገልጿል።
እስካሁን ባለው መረጃ ወደ 290,000 የሚጠጉ ሰዎች በዘመቻው የተሳተፉ ሲሆን የተሰበሰበው የገንዘብ መጠንም 25 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል ተብሏል።
ዶናልድ ትራምፕ እ.ኤ.አ.በ2020 የኢራን አብዮታዊ ዘብ ልዩ ሃይል አዛዥ የነበሩትን ቃሲም ሱሌይማኒን በባግዳድ እንዲገደሉ ትእዛዝ ከሰጡበት ጊዜ ጀምሮ ኢራን በፕሬዝዳንቱ ላይ የግድያ ዛቻዎችን ስታሰማ የቆየች ሲሆን የግድያ ዛቻዎች አሁን ካለው ቀውስ ጋር ተዳምረው በከፍተኛ ሁኔታ ጨምረዋል።
ባለፈው የካቲት ወር በብሩክሊን ፍርድ ቤት ይፋ በሆነ ድብቅ የካሜራ ቪዲዮ ከኢራን ጋር ግንኙነት ያለው ተላላኪ ትራምፕን ለመግደል አቅዶ እንደነበር ያሳየ ሲሆን እ.ኤ.አ.በኖቬምበር 2024 ደግሞ የአሜሪካ ፍትሕ ሚኒስቴር የኢራን አብዮታዊ ዘብ ከምርጫው በፊት ትራምፕን ለመግደል የሰነዘረውንና የከሸፈውን ሴራ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።