Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ዜና

ደረሰኝ ያልሰጠ ግብር ከፋይ በእያንዳንዱ የደረሰኝ ብዛት 100 ሺህ ብር ሊቀጣ ነው

A Administrator May 15, 2026 Updated 1d ago 2 ደቂቃ ንባብ 682 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
ደረሰኝ ያልሰጠ ግብር ከፋይ በእያንዳንዱ የደረሰኝ ብዛት 100 ሺህ ብር ሊቀጣ ነው

ደረሰኝ ያልሰጠ ግብር ከፋይ በእያንዳንዱ የደረሰኝ ብዛት 100 ሺህ ብር ሊቀጣ ነው

ግንቦት 7/2018 (ገበያ ሚዲያ) መንግሥት ሊያጸድቀው ባዘጋጀው አዲሱ የታክስ አስተዳደር አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ ላይ ደረሰኝ የመስጠት ግዴታ እያለበት ሳይሰጥ በሚቀር ማንኛውም ታክስ ከፋይ ላይ በእያንዳንዱ የደረሰኝ ብዛት የ100 ሺህ ብር ከባድ አስተዳደራዊ ቅጣት ሊጣል መሆኑ ተገልጿል። 


ይህ የሕግ ማሻሻያ በተለይም የታክስ ደረሰኝ አጠቃቀም ላይ በሚፈጸሙ ሕገ-ወጥ ድርጊቶች እና በድርጅቶች አመራሮች ኃላፊነት ላይ ያነጣጠሩ ጠንከር ያሉ የወንጀልና የአስተዳደር ማዕቀቦችን እንደያዘ ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ 


በማሻሻያ አዋጁ መሠረት ደረሰኝ የመስጠት ግዴታ እያለበት ሳይሰጥ በሚቀር ማንኛውም ታክስ ከፋይ ላይ የተጣለው ቅጣት ጨምሯል።

Advertisement
Your ad could be here — contact us


በዚህም መሠረት ደረሰኝ ሊሰጥ ሲገባው ላልሰጠ ማንኛውም ታክስ ከፋይ ለገዢ ባልሰጠው በእያንዳንዱ ደረሰኝ ብዛት 100,000 ብር (አንድ መቶ ሺህ ብር) አስተዳደራዊ ቅጣት እንዲቀጣ ተደንግጓል።


ሆኖም ይህ ደረሰኝ ባለመስጠት ጥፋት ወደ ወንጀል ክስና ተጠያቂነት የሚሸጋገረው ጥፋቱ በአንድ የግብር ዘመን ውስጥ ለሁለት ጊዜያት ያህል አስተዳደራዊ ቅጣት ከተጣለ በኋላ ለሦስተኛ ጊዜ ተደግሞ ሲገኝ ብቻ እንደሆነ በሕጉ ላይ ተመላክቷል።


ከዚህ በተጨማሪ በአንድ ግብይት ላይ ተመሳሳይ ደረሰኞችን በመጠቀም የሽያጭ ዋጋን በማሳነስ የሚፈጸሙ ማጭበርበሮች ላይ የተጣለው ቅጣት ጠንከር ያለ ሆኗል።


ለአንድ ግብይት በተሰጠ ተመሳሳይ ደረሰኝ ላይ የተለያዩ ዋጋዎችን በመመዝገብ የሽያጭ ዋጋን ያሳነሰ ወይም የሽያጭ ዋጋን በማሳነስ ደረሰኝ የሰጠ ማንኛውም ሰው ብር 100,000 (አንድ መቶ ሺህ ብር) የገንዘብ መቀጫ የሚጣልበት ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ከአምስት እስከ ሰባት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጣ አዲሱ ሕግ ይደነግጋል።


ረቂቅ አዋጁ በድርጅቶችና በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ታክስ ተቀንሶ ገቢ የመደረጉን ሂደት በሚከታተሉ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ላይም ተጨማሪ ተጠያቂነትን ጭኗል።


የታክስ ባለሥልጣኑ ጥያቄ ከመቅረቡ በፊት ታክስ ተቀንሶ መያዝ እና መከፈል እንዳለበት የማረጋገጥ ኃላፊነት እያለባቸው ይህንን ሳይወጡ በቀሩ የድርጅት ሥራ አስኪያጆች፣ የመሥሪያ ቤት የበላይ ኃላፊዎች፣ ዋና የሂሳብ ሹሞች ወይም ማንኛውም ሌላ የመንግሥትና የድርጅት ሠራተኛ ላይ ተቋሙ ከሚቀጣው ቅጣት በተጨማሪ እያንዳንዳቸው ብር 2,000 (ሁለት ሺህ ብር) መቀጫ እንዲከፍሉ ይደረጋል።


በመጨረሻም በድርጅቶች የሚፈጸሙ የታክስ ወንጀሎችን በተመለከተ ወንጀሉ በተፈጸመበት ወቅት የነበሩ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ፣ የፋይናንስ ኃላፊ ወይም በተመሳሳይ የኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ አመራሮች ድርጊቱ እንዲፈጸም የፈቀዱ፣ ያዘዙ ወይም የተባበሩ ከሆነ ወንጀሉን እንደፈጸሙ ተቆጥረው ተጠያቂ ይሆናሉ።


ይሁን እንጂ የተጠቀሱት የሥራ ኃላፊዎች ወንጀሉ የተፈጸመው ከእነርሱ ዕውቅና ውጭ መሆኑን ወይም የዚህ ዓይነቱ ወንጀል እንዳይፈጸም መከላከል የሚያስችል አስተማማኝ የውስጥ ቁጥጥር ሥርዓት የዘረጉ መሆኑን በተጨባጭ ማስረዳት ከቻሉ ከዚህ የወንጀል ተጠያቂነት ነፃ ሊሆኑ እንደሚችሉ በረቂቅ አዋጁ ድንጋጌ ላይ በዝርዝር ተመልክቷል።


በዚህም ነባሩን የታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 ለማሻሻል የተዘጋጀውን ይህንን ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ የገንዘብ ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት ጋር ግልጽ የውይይት መድረክ ማዘጋጀቱንና ጥሪ ማስተላለፉን አስታውቋል።


የሕጉ ረቂቅ ጸድቆ ወደ ሥራ ከመግባቱ በፊት በሕጉ ቀጥተኛ ተገዢ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችንና ባለሙያዎችን ማሳተፍ፣ ግብዓት መሰብሰብና ግልጽ ውይይት ማድረግ አፈላጊ በመሆኑ የታክስ አስተዳደር አዋጅ ማሻሻያ የሚመለከታቸው ግብር ከፋዮች፣ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት፣ የሕግና የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንዲሁም ፍላጎት ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች በሙሉ ግንቦት 11 ቀን 2018 ዓ.ም ከጠዋቱ 3፡00 ጀምሮ ስድስት ኪሎ በሚገኘው የገንዘብ ሚኒስቴር ዋና መሥሪያ ቤት ቅጥር ግቢ በአካል በመገኘት አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ጥሪ ተላልፏል።

A
ስለ ጸሐፊው

Administrator

12 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።