Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ስፖርት

ስፓኒያርዱ አሰልጣኝ አመቱን በመጥፎ ሪከርድ ቋጭቶ ከከክለቡ ጋር ሊለያይ ይሆን?

A Administrator May 14, 2026 Updated 4h ago 3 ደቂቃ ንባብ 72 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
ስፓኒያርዱ አሰልጣኝ አመቱን በመጥፎ ሪከርድ ቋጭቶ ከከክለቡ ጋር ሊለያይ ይሆን?

 

Advertisement
Your ad could be here — contact us

ከክለቡ ጋር ለመለያዬት የተቃረበው ታክቲሽያኑ አሰልጣኝ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሁለት ተከታታይ ሲዝን ያለ ሊግ ዋንጫ አመቱን ለማጠናቀቅ ተቃርቧል።

ስፓኒያርዱ እውቅ አሰልጣኝ በስራ ዘመኑ ከጀርመን እስከ ስፔን ፣ ከስፔን እስከ እንግሊዝ የሥኬታማነትን ደሥታ ደጋግሞ አጣጥሟል።

በተለይም በሶስት ታላላቅ የአውሮፓ ሊጎች ላይ ለማንም ምህረት የሌለው አይበገሬ ቡድን በመገንባት ሌሎች ክለቦችን እንቁልልጭ እያለ ተከታታይ ታላላቅ ዋንጫዎችን ወደካዝናው አስገብቷል።

ይህ ሰው ለአስርት አመታት በቆየበት የአሰልጣኝነት ዘመኑ ለተከታታይ ሁለት አመት የሊግ ዋንጫ አጥቶ አያውቅም።

እንዲሁም በሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት የቀመሰው ጥሩ ባልነበረበት ያለፈው አመት ብቻ ነው።
ይህ ድል በእጁ የሆነው አስደናቂ አሰልጣኝ ኃያል ክለብ ገንብቶ ተጋጣሚ ቡድንን ሲያሥጨንቅ እና የትየለሌ ዋንጫዎችን በገፍ ወደካዝናው ሲያግዝ የኖረ ነው።

ይህ ሰው በጀርመን ቦንደስ ሊጋ ባየርን ሙኒክን እየመራ አይረሴ ታሪክ የሰራ ፣ በስፔን ባርሴሎናን እያሰለጠነ አለምን አጃኢብ ያስባለ ፣ ቀጥሎም መዳረሻውን እንግሊዝ በማድረግ የማንችስተር ሲቲን ታሪክ ሙሉ ለሙሉ የቀየረ የዘመናዊ እግር ኳስ ፈላጭ ቆራጭ ነው።

በተለይም በተጠቀሱት ሶስት ታላላቅ የአውሮፓ ሊጎች ኃያላን የሆኑትን ክለቦች በመምራት አለም ላይ አሉ የተባሉ ዋንጫዎችን ሁሉ ከፍ ያደረገ እና ይህ ቀረኝ የማይል አሰልጣኝ ነው።

ይህ ሰው በእግር ኳስ ላይ ፍትሃዊ አምባገነንነት የተሞላበትን አስገራሚ የአሰልጣኝነት ጥበብን የተላበሰው ስፓኒያርዱ ታክቲሽያን ፔፕ ጋርዲዮላ ነው።

የወቅቱ የማንችስተር ሲቲው አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ በምርጥ አሰልጣኝነቱ አለም በአንድ ልብ መክሮ ፣ በአንድ ቃል ተናግሮ የሚመሰክርለት ሰው ነው።

ታዲያ ያለፈው አመት እና ዘንድሮ ግን በሜዳም ሆነ ከሜዳ ውጪ ባለው ህይወቱ የተፈተነበት ፣ የለመደውን ስኬት ለማስቀጠል የተቸገረበት አመት ሆኗል።

ፔፕ በአሰልጣኝነት ታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች በላይ የተሸነፈው ባለፈው አመት ነበር። ከአንደኛ እና ከሁለተኛ ውጪ ሆኖ ሊጉን ያጠናቀቀውም በተመሳሳይ ለመጀመሪያ ጊዜ አምና ነበር።

በርግጥ ባለፈው አመት በስፖርት ህይወቱ ብቻ ሳይሆን በቤተሠቡ ሁኔታም እጅግ የተፈተነበትና ትዳሩ አደጋ ላይ የወደቀበት አመት ነበር።

ለ36 አመታት ያህል አብሯት ከኖረችው የልጅነት ባለቤቱ ክርስቲና ሴራ ጋር ፍቺ እስከመፈፀም የደረሰው ፔፕ ጋርዲዮላ ከክርስቲያና ጋር ጋብቻ የፈፀሙት የ18 አመት ታዳጊ በነበሩበት ጊዜ ሲሆን ጥንዶቹ ከሶስት አስርት አመታት በላይ በዘለቀው ጋብቻቸው የ25 አመቷን ማረያን ፣ የ23 አመቷን ማሪያስን  እና የ18 አመቷን ቫሌንሮናን  በድምሩ ሶስት ሴት ልጆችን ለማፍራት ችለዋል፡፡

ሆኖም የአምናው ፈተና እና ስኬት አልባው ሲዝን በሜዳም ከሜዳ ውጭም ፈተና ነበረው።
እዚህ የደረሰው የአለም ምርጡ ታክቲሽያን ፔፕ ጋርዲዮላ በበርካታ ግቦች በታጀበ የህይወት ዘመኑ አይቶት የማያውቀውን ሽንፈት እየቀመሠውም በዚህ ጊዜ ነው።

የማንቸስተር ሲቲው አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ያለፈው ሲዝን የሜዳም ሆነ የሜዳ ውጭ ህይወቱ እየተዘበራረቀ እና እጅግ ፈታኝ ነበር።

በጀርመን ባየር ሙኒክ ከዛም በእስፔን ባርሴሎና አይቀመሤ ቡድን መሥርቶ ለአመታት ተከታታይ ዋንጫዎችን ሲያካብት የኖረው ስፔናዊው ራሰ-በራ
ወደ እንግሊዝ መጥቶም ያን ማድረግ ቅንጣት አልከበደውም ነበር።
በዚህም በከባዱ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ብዙም ታሪክ የሌለውን ማንችስተር ሲቲን ተረክቦ በስድስት አመታት ውስጥ አምስት ጊዜ የሊጉን ዋንጫ ሲያነሳ ለእሱ ሙዝ ልጦ የመብላት ያህል ቀላል ነበር።

ይሔን ብቻ አይደለም የሶስትዮሽ ዋንጫ ባለቤት ለመሆን  አምበሳን በቡጢ እንደመግደል በሚከብድበት ሊግ
ከአውሮፓ ታላላቅ ክለቦች ጋር አንገት ለአንገት ተናንቀቆ ያንን ማሣካት ችሏል።

ከሊግ እስከባለትልቁ ጆሮ የሻምፒንስ ሊግ ዋንጫ ደጋግሞ ያጣጣመው ጋርዲዮላ ባለፈው እና በዚህ አመት ግን የለመደው የድል ሱስ እርቆበታል።

አምና ከትልልቅ ዋንጫዎች መድረክ በጊዜ ገሸሽ ያለው ፔፕ ዘንድሮም አንድ አለኝን ሊያጣ ተቃርቧል።

ከሻምፒዮንስ ሊጉ በጊዜ የተሰናበተ ሲሆን አሁን ደግሞ ከፍተኛ ውጥረት እየታየበት በመጣው የሊጉ ዋንጫ ፉክክር አንድ እግራቸውን አውጥተውታል።

በሳቸው የሚመሩት ሲቲዝኖቹ ምንምኳ የካራባዎ ካፕ ዋንጫን ከተፎካካሪያቸው አርሰናል የነጠቁ እና ለኤፍኤ ፍፃሜ የደረሱ ቢሆንም በዋናው የሊግ ዋንጫ ፉክክር ላይ ግን ያላቸው እድል እጅግ ጠቧል።

በተለይም ባለፈው ሳምንት በኤቨርተን ነጥብ መጣላቸው ለአርሰናል ሰርግ እና ምላሽ ሲሆንለት ለእነሱ ግን እጅግ መራር ነበር።
ያንን ተከትሎ ሲቲ የነጥብ ልዩነቱን እኩል በማድረግ ፉክክሩ ላይ ነዳጅ የሚያርከፈክፉበትን እድል ባለመጠቀማቸው አርሰናልን ከጫና እንዲወጣ እና የልብ ልብ እንዲሰማው ለማድረግ ተገደዋል።

በ55 አመት እድሜው ላይ የሚገኘው ፔፕ ጋርዲዮላ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ለተከታታይ ሁለት አመት የሊግ ዋንጫ ሳያነሳ ሲዝኑን ለመቋጨት ተቃርቧል።

በተጨማሪም አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ በቀጣይ የውድድር ዘመን በማንችስተር ሲቲ ላይቀጥሉ እንደሚችሉ ፍንጭ ተገኝቷል።

የክለቡን ጉዳዮች የሚከታተሉ ታማኝ ምንጮች ፔፕ ጋርዲዮላ በዚህ አመት ክለቡን ይለቃሉ ብለው እንደሚጠብቁ ተገልጿል።
ይህን ጥርጣሬ ወደ እርግጠኝነተሰ የወሰደው አንደኛው ጉዳይ ደግሞ የክለቡ የፊትነስ አሰልጣኙ የቡናቬንቱራ ከክለቡ ጋር የመለያዬቱ ዜና ዛሬ መሰማቱ ነው።

በዚህም ፔፕ ጋርዲዮላ ያለ ፊትነስ አሰልጣኙ ሎሬንዞ ቡናቬንቱራ በክለቡ ይቀጥላል ብሎ መገመት ከባድ መሆኑ ተነግሯል።

በዚህም አሁን ላይ የነባር አሰልጣኞቹ መልቀቅ ዜና በማንችስተር ሲቲ የአሰልጣኝ ለውጥ እንደሚኖር ፍንጭ መስጠቱ ተገልጿል።

ክለቡ በበኩሉ ከፔፕ ጋርዲዮላ በኋላ የሚገጥመውን ህይወት ለመጋፈጥ ለረጅም ጊዜ ሲሰራ መቆየቱ ተነግሯል።

በዚህም ስፓኒያርዱ ታክቲሽያን ፔፕ ጋርዲዮላ ዋንጫውን አርሰናል የሚያነሳ ከሆነ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በተከታታይ ሁለት አመት ያለሊግ ዋንጫ በማጠናቀቅ አዲስ ጥቁር ታሪክ አስመዝግቦ ከክለቡ ጋር የሚለያይ ይሆናል።

ሁለቱ የዋንጫ ተፎካካሪዎች አርሰናል እና ማንቸስተር ሲቲ በቀጣይ ለዋንጫው ወሳኝ የሆኑ የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎችን ያደርጋሉ።

‎አርሰናል በርንሌይን በሜዳው እና ክርስታል ፓላስን ደግሞ ከሜዳው ውጪ ተጉዞ ሲገጥም ፤ ማንቸስተር ሲቲ በበኩሉ በርንማዉዝ ከሜዳው ውጪ ተጉዞ እንዲሁም አስቶንቪላን ደግሞ በሜዳው ኢትሐድ ያስተናግዳል።

ከእነዚህ ተጠባቂ ጨዋታዎች በኋላ የአርሰናል የ22 አመታት የዋንጫ ርሃብ ያበቃለታል ወይስ የፔፕ ጋርዲዮላ በተከታታይ ሁለት አመት የሊግ ዋንጫ ያለማጣት ሪከርድ ይቀጥላል? የሚለውን ጊዜ እስኪነግረን በቸር እንሰንብት!

በመኮነን አልማው።

A
ስለ ጸሐፊው

Administrator

12 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።