Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ዜና

ለ26 የንግድ ዘርፎች አዲስ አስገዳጅ መመርያ ወጣ

BS Bethelhem Solomon Jul 6, 2026 Updated 3h ago 2 ደቂቃ ንባብ 1090 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
ለ26 የንግድ ዘርፎች አዲስ አስገዳጅ መመርያ ወጣ

የQR ኮድ ያላቸው በእጅ የሚፃፉ ደረሰኞች እንደ የመጨረሻ አማራጭ የሚያገለግሉ ሲሆን እነርሱም ቢሆን በ72 ሰዓታት ውስጥ ወደ ማዕከላዊው ሥርዓት የመግባት ግዴታ አለባቸው ተብሏል።


የገቢዎች
ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ በስፋት የሚንቀሳቀሱ 26 የንግድ ዘርፎችን በመለየት የኢንተርኔት ግንኙነት በተቋረጠበት ወቅት የንግድ ሥራው እና የደረሰኝ አሰጣጡ እንዳይስተጓጎል የሚያስገድድ መመሪያ አውጥቷል።

ይህ
ድንጋጌ የኤሌክትሮኒክ ደረሰኝ አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 1142/2018” አካል ሲሆን በመመርያው ተጠቃሽ የሆኑ ንግዶችኦፍላይን የንግድ ቀጣይነት ሥርዓትእንዲተገብሩ ያዝዛል።


በመመሪያው መሰረት እነዚህ ተቋማት የኢንተርኔት ግንኙነት ሲቋረጥ ግብይቶችን በአካባቢያዊ የሶፍትዌር ማህደረ ትውስታ የመመዝገብ አቅም ሊኖራቸው ይገባል።

የተመዘገቡት የግብይት መረጃዎች ግንኙነቱ እንደተመለሰ ባሉት 72 ሰዓታት ውስጥ ወደ ሚኒስቴሩ ማዕከላዊ የውሂብ ማዕከል እንዲላኩ ግዴታ የተጣለ ሲሆን ይህም የግብር አሰባሰብ ሂደቱን ይበልጥ አስተማማኝ እና ከቴክኖሎጂ መቆራረጥ ነፃ ለማድረግ ያለመ መሆኑን መመሪያው ያመለክታል።

Advertisement
Your ad could be here — contact us

አዲሱ ደንብ በዕለታዊ የሸማቾች ግብይት ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸውን ዘርፎች ያካተተ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የምግብ፣ መጠጥ፣ ትምባሆ፣ አልባሳት፣ ጨርቃጨርቅ፣ ፋርማሲ፣ ያገለገሉ ዕቃዎች፣ ነዳጅ ማደያዎች እና የተሽከርካሪ መለዋወጫዎች ቸርቻሪዎች ይገኙበታል።


በተጨማሪም ምግብ ቤትና ካፌዎች፣ ሆቴሎችና ማረፊያዎች፣ ሆስፒታሎች፣ የሕክምናና የጥርስ ክሊኒኮች፣ የውበት ሳሎኖች፣ እስፓዎች፣ የእንስሳት ህክምና፣ መዝናኛ ስፍራዎች፣ የከተማና የረጅም ርቀት የህዝብ ትራንስፖርት፣ የባቡር አገልግሎት እና የፖስታ አገልግሎት ሰጪዎች በግዴታው ተካተዋል።

የቴክኒክ መስፈርቶችን በተመለከተ ማንኛውም ለዚህ አገልግሎት የሚውል የንግድ ሶፍትዌር ለገበያ ከመዋሉ በፊት በሚኒስቴሩ ተለይቶ በወጣ የቴክኒክ መስፈርት መሰረት መረጋገጥ እንዳለበት ሰፍሯል


ሶፍትዌሩ ለኦፍላይን ተግባር የተዘጋጀ መሆኑን የሚያረጋግጥ ፈተና ማለፍ የሚኖርበት ሲሆን በተለይም በስማርት ስልክ ወይም በሞባይል ፖይንት ኦፍ ሴል (POS) የሚጠቀሙ ተቋማት ተጨማሪ ጥብቅ ደንቦች ይጠብቋቸዋል።


እነዚህም የግብይቱን ትክክለኛ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ (GPS) የመመዝገብ፤ መገኛ ቦታቸውን ለሚኒስቴሩ በየጊዜው የመላክ እና በተፈቀደላቸው መልክዓ ምድራዊ ክልል ውስጥ ብቻ አገልግሎት የመስጠት ግዴታን ያካትታሉ።

የሥርዓት መቋረጥ ሲያጋጥም ንግዶች በሶፍትዌራቸው ደረሰኝ መቁረጣቸውን ሊቀጥሉ የሚችሉ ሲሆን የቴክኒክ ችግሩ ከሰባት ቀናት በላይ ከቆየ ግን ግብር ከፋዩ ወደ ሌላ ጊዜያዊ ወይም ቋሚ የሽያጭ ምዝገባ ሥርዓት እንዲሸጋገር ደንቡ ያስገድዳል።


QR ኮድ ያላቸው በእጅ የሚፃፉ ደረሰኞች እንደ የመጨረሻ አማራጭ የሚያገለግሉ ሲሆን እነሱም ቢሆን 72 ሰዓታት ውስጥ ወደ ማዕከላዊው ሥርዓት የመግባት ግዴታ አለባቸው።

ሚኒስቴሩ በበኩሉ የቴክኖሎጂ አቅም እና በንግድ ልምምዶች በሚኖረው የጊዜ ሂደት ለውጥ መሰረት በግዴታው የተካተቱ ዘርፎችን ዝርዝር ወደፊት እንደሚያሻሽል አስታውቋል።


ይህ እርምጃ የግብር አሰባሰብን ዘመናዊ ከማድረጉ ባለፈ፤ ለንግድ ተቋማት ሳይጠበቅ የሚከሰተውን የአገልግሎት መቆራረጥ ለመቀነስ እንደሚያግዝ ታምኖበታል።

BS
ስለ ጸሐፊው

Bethelhem Solomon

52 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።