Home / ገበያ ቢዝነዝ / በፍሪላንስ ወይም በርቀት የሥራ ዘዴ ገቢ በሚያገኙ ግለሰቦች ላይ የገቢ ግብር ተፈጻሚ ሊያደርግ መሆኑ ተሰማ

በፍሪላንስ ወይም በርቀት የሥራ ዘዴ ገቢ በሚያገኙ ግለሰቦች ላይ የገቢ ግብር ተፈጻሚ ሊያደርግ መሆኑ ተሰማ

የካቲት 26/2018 (ገበያ ሚዲያ) ገንዘብ ሚኒስቴር አዲስ ባዘጋጀው የገቢ ግብር ረቂቅ ደንብ፤ በኢትዮጵያ ነዋሪ ሆነው በዲጂታል አማካኝነት እና በፍሪላንስ ወይም በርቀት የሥራ ዘዴ ገቢ በሚያገኙ ግለሰቦች ላይ የገቢ ግብር ተፈጻሚ ሊያደርግ መሆኑን አስታውቋል።

በዚህም ማንኛውም በኢትዮጵያ ነዋሪ የሆነ ሰው ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ሀገር ምንጮች በዲጂታል ይዘት ፈጠራ ወይም በማንኛውም የፍሪላንስ ሥራ የሚያገኘው ገቢ (በጥሬ ገንዘብም ሆነ በዓይነት) ግብር መክፈል እንዳለበት ገልጿል።

በሌላ በኩል የዲጂታል ይዘት ፈጣሪዎች ያገኙትን የገቢ መጠን በሚመለከት ትክክለኛ እና የተሟላ የሂሳብ መዝገብ የመያዝ ግዴታ ተጥሏል ተብሏል።

ይህንን ግዴታ ባልተወጡ ግብር ከፋዮች ላይ ታክስ የሚወሰነው በሚኒስቴሩ መመሪያ መሠረት በግምት እንደሆነም ተነግሯል።

በተጨማሪም ክፍያ የሚያመቻቹ ኩባንያዎች የዲጂታል ስራ የፈጣሪዎችን ስም ዝርዝር፣ አድራሻ፣ የሲም ካርድ መረጃ፣ የአይፒ (IP) አድራሻ እና የተከፈለውን የገንዘብ መጠን በየሩብ ዓመቱ ለታክስ ባለሥልጣኑ ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል ነው የተባለው።

በዚሁ መመሪያ ባንኮች ለኪሳራ የያዙት የመጠባበቂያ ሂሳብ በብሔራዊ ባንክ መሥፈርት መሠረት የተሰላ ከሆነ፤ 80 በመቶው በተቀናሽ ወጪ እንዲያዝላቸው መደንገጉን ሪፖርተር ዘግቧል።

እንዲሁም የደረጃ ለ ግብር ከፋዮች ዓመታዊ ጠቅላላ ገቢ የሚወሰነው የታክስ ባለሥልጣኑ በየሦስት ዓመቱ በሚያደርግ የገበያ ጥናት እንደሚወሰን በአዲሱ ደንብ ላይ ተመላክቷል።

በሌላ በኩል ከመንግሥት ቦንዶችና ግምጃ ቤት ሰነዶች የሚገኝ ወለድ ወይም ትርፍ፣ እንዲሁም የአየር መንገድ የውጭ ብድር ወለድና የአውሮፕላን ኪራይ (ሮያሊቲ) ክፍያዎች ከግብር ነፃ ተደርገዋል።

የገንዘብ ሚኒስቴር ረቂቅ ደንቡ ከመጽደቁ በፊት አስተያየት መስጠት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው መጋቢት 1 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ አስተያየት መስጠት እንደሚችሉ አስታውቋል።

#ገበያ_ሚዲያ#gebeyamedia#gebeyanews#ገበያ#Ethiopia#ኢትዮጵያ#addisababa#አዲስአበባ#ethiopiatax#FreelanceTaxes#DigitalEconomy#REMOTEWORK#DigitalTax#incometax#የገቢግብር#ፍሪላንስ#ዲጂታል#የገንዘብሚኒስቴር#ታክስ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *