Home / ገበያ ቢዝነዝ / የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ “ንዋይ” የተሰኘ የሞባይል መተግበሪያ ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ “ንዋይ” የተሰኘ የሞባይል መተግበሪያ ይፋ አደረገ

የካቲት 26/2018 (ገበያ ሚዲያ) የኢትዮጵያ ሰነድ መዋዕለ ንዋይ ገበያ (ESX) በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ ዜጎች በቀላሉ በካፒታል ገበያው ውስጥ መሳተፍ እንዲችሉ የሚያስችል “ንዋይ” የተሰኘ የመጀመሪያውን የድረ-ገጽ እና የሞባይል ንግድ መተግበሪያ በይፋ አስጀምሯል።

ይህ ዛሬ የካቲት 26 ቀን 2018 ዓ.ም. ይፋ የተደረገው አዲስ ቴክኖሎጂ በኢንፎቴክ ፕራይቬት ሊሚትድ ድጋፍ የበለጸገ ሲሆን፣ የንግድ ትዕዛዞችን ለማስተላለፍ፤ የአክሲዮንና የዕዳ ሰነዶችን ለመግዛትና ለመሸጥ እንዲሁም የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን በየሰዓቱ ለመከታተል የሚያስችል ዘመናዊ መድረክ ነው ተብሏል።

የመተግበሪያው ስያሜ “ንዋይ” የሚለውን የሀብትና የንብረት ትርጉም የያዘ ሲሆን፤ ይህም የሀብት ተደራሽነትን ለህዝብ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ ያለውን ራዕይ የሚያሳይ መሆኑ ተገልጿል።

መተግበሪያው ዓለም አቀፍ የደህንነት መስፈርቶችን የተከተለና ጠንካራ የደንበኞች ማንነት ማረጋገጫ (KYC) ሥርዓት የተገጠመለት በመሆኑ፤ ኢንቨስተሮች በሙሉ እምነት ግብይት እንዲፈጽሙ ይረዳቸዋል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ሰነድ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጥላሁን እስማኤል ካሳሁን (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ይህ መድረክ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ በቀጥታ እንዲሳተፍ በማድረግ የካፒታል ገበያውን አካታች፣ ግልጽና ቀልጣፋ ያደርገዋል።

በአሁኑ ወቅት መተግበሪያው ለአንድሮይድ እና ለባለ አይ.ኦ.ኤስ (iOS) ስልኮች የቀረበ ሲሆን፤ ተጠቃሚዎች ያሉበት ቦታ ሳይገደቡ በፈለጉት ጊዜ የገበያውን እንቅስቃሴ መከታተል እንደሚችሉ ተነግሯል።

ይህም የንግድ ወጪን በመቀነስና የገበያ ተደራሽነትን በማስፋት የኢትዮጵያን የፋይናንስ ሥርዓት ለማጠናከር ትልቅ ሚና ይጫወታል ተብሎ ታምኖበታል።

#ገበያ_ሚዲያ#gebeyamedia#gebeyanews#ገበያ#Ethiopia#ኢትዮጵያ#addisababa#አዲስአበባ#ESX#NewayApp#ethiopiansecuritiesexchange#capitalmarket#digitaltrading#investment#የአክሲዮንገበያ#ንዋይ#ኢንቨስትመንት#መዋዕለንዋይ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *