የካቲት 26/2018 (ገበያ ሚዲያ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደንበኞቹን ማንነት ለማረጋገጥና አሠራሩን ለማዘመን የፋይዳ መታወቂያን ከአገልግሎት አሰጣጡ ጋር ሊያስተሳስር እንደሆነ ተገልጿል።
አገልግሎቱ ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር የካቲት 20 ቀን 2018 ዓ.ም በገባው ስምምነት መሰረት ማስተሳስሩን እንደሚያከናውን የገለጹት የአገልግሎቱ የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ አንዋር አብራር፤ ስምምነቱ በዋናነት ተቋሙ በአሁኑ ወቅት ያሉትን ከ5 ሚሊዮን 500 ሺህ በላይ ደንበኞች ማንነት ለመለየት የሚረዳ ነው ብለዋል።
የፋይናንስ እና የሰነዶች ማረጋገጫ ተቋማት አገልግሎታቸውን በፋይዳ መታወቂያ እየሰጡ እንደሆነ አስታውሰው፤ “የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትም እንደሌሎቹ ተቋማት ሁሉ የውስጥ አሠራሩን እንዲያዘምን ስምምነቱ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ይኖረዋል” ያሉት ደግም የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የኮሙኒኬሽን ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ሳሚናስ ሰይፈ ናቸው።
ስምምነቱ ተግባራዊ መሆን ሲጀምር ደንበኞች ተመሳሳይ ቅጾችንና መጠይቆችን በተደጋጋሚ እንዳይሞሉ በማድረግ የአገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋ እንደሚያደርገውም ዳይሬክተሩ ማብራራታቸውን አሐዱ ዘግቧል።
“የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የፋይዳ መታወቂያን ለአገልግሎቱ ተግባራዊ ማድረግ መቼ ይጀመራል?” የሚለው በይፋ ያልተገለጸ ሲሆን፤ ወደ ተግባር ሲገባ የተቋሙ ደንበኞች በየጊዜው የሚጠየቋቸውን ተመሳሳይ መረጃዎች በዲጂታል መንገድ በማግኘት የሥራ ጫናን እንደሚቀንስ ይጠበቃል።
ይህ አሰራር በተለይም አዳዲስ የኃይል መስመር ፈላጊዎች እና ነባር ተገልጋዮች መረጃቸው በዘመናዊ መልኩ እንዲደራጅ የሚያስችል መሆኑም ተመላክቷል።
#ገበያ_ሚዲያ#gebeyamedia#gebeyanews#ገበያ#Ethiopia#ኢትዮጵያ#addisababa#አዲስአበባ#ethiopianelectricutility#fayda#DigitalID#የኤሌክትሪክአገልግሎት#ፋይዳ#ብሔራዊመታወቂያ








