Home / ዜና / የዕለት ዜና / በተለምዶ አጠራሩ ‘ሿሿ’ በሚል የሚታወቀውን የውንብድና ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦች በእስራት ተቀጡ

በተለምዶ አጠራሩ ‘ሿሿ’ በሚል የሚታወቀውን የውንብድና ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦች በእስራት ተቀጡ

የካቲት 27/2018 (ገበያ ሚዲያ) ሚኒ ባስ ታክሲ በመጠቀም በተለምዶ አጠራሩ ‘ሿሿ’ በሚል የሚታወቀውን የውንብድና ወንጀል የፈጸሙ አራት ግለሰቦች ከ7 እስከ 12 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት መቀጣታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ አስታውቋል፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ነው የቅጣት ውሳኔውን ያሳለፈው፡፡

የቅጣት ውሳኔ የተወሰነባቸው ሰናይት ገ/እግዚአብሔር፣ ሄርሜላ ካሳ፣ መክሊት አዳነ እና ዳኛቸዉ መንግስቴ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ ድንጋጌ ተላልፈዋል በማለት፤ የፍትህ ሚኒስቴር የየካ ምድብ ዐቃቤ ሕግ በሕዳር 24 ቀን 2017 ዓ.ም በነበረ ችሎት ቀጠሮ ዝርዝር ክስ አቅርቦባቸው ነበር።

በክሱ ዝርዝር ላይ እንዳመላከተው፤ ተከሶሾቹ ተገቢ ያልሆነ ብልጽግና ለራሳቸዉ ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ በጥቅምት 15 ቀን 2017 ዓ.ም ከምሽቱ 3፡30 ሰዓት ሲሆን በየካ ክ/ከ ወረዳ 07 ሌክስ ፕላዛ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ የታክሲ አሽከርካሪ፣ ረዳት እና ተሳፋሪ በመምሰል 3 ግለሰቦችን ወደ ታክሲ ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋሉ።

በማስከተልም አንገታቸውን በማነቅ እራሳቸውን እንዳይከላከሉ በማድረግ ሦስት ተንቀሳቃሽ ስልኮች፣ የወርቅ ሀብል፣ 5 ሺሕ ጥሬ ብር እና ከአንድ የግል ተበዳይ ደግሞ በሞባይል ባንኪንግ ከ13 ሺሕ ብር በላይ ገንዘብ ወስደው ከታክሲ እንዲወርዱ ማድረጋቸው ተገልጿል።

ተከሳሾቹ በችሎት ተገኝተው ክሱ እንዲደርሳቸውና በንባብ እንዲረዱት የተደረገ ሲሆን፤ ተከሳሾቹ በክሱ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት እንዳልፈጸሙ በመግለጽ የዕምነት ክህደት ቃላቸውን በማስመዝገባቸው ዐቃቤ ሕግ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን ለችሎቱ አቅርቧል።

በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ እንዲከላከሉ በሰጠው ብይን ተከሳሾች የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መከላከል ባለመቻላቸው ጥፋተኛ ተብለዋል።

ከዚህም በኋላ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት በመመርመር ተከሳሾቹ እንደየተሳትፎ ደረጃቸው በጽኑ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑ ተገልጿል።

በዚህም ሰናይት ገ/እግዛብሔር በ11 ዓመት፣ ሄርሜላ ካሳ በ7 ዓመት፣ መክሊት አዳነ በ9 ዓመት እንዲሁም ዳኛቸው መንግስቴ በ12 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ መተላለፉ ተመላክቷል።

One Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *