የኢፌዴሪ ገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ አስተዳደሩን ዘመናዊ ለማድረግ፣ ግልጽነትን ለማስፈን እና የታክስ ስወራን በዘላቂነት ለመከላከል በማለም ያወጣውን "የኤሌክትሮኒክ ደረሰኝ ሥርዓት አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 1142/2018" በይፋ ተግባራዊ ማድረጉ ተሰምቷል።
ይህ አዲስ መመሪያ በሂሳብ መዝገብ በሚይዙ በሁሉም ታክስ ከፋዮች ላይ ተፈጻሚ የሚሆን ሲሆን ማንኛውም ግብይት ሲከናወን ወዲያውኑ ለሚኒስቴሩ ማዕከላዊ የመረጃ ቋት ሪፖርት እንዲደረግ ያስገድዳል።
በአዲሱ አሠራር መሰረት እያንዳንዱ ደረሰኝ ልዩ የደረሰኝ ምዝገባ ቁጥር እና ፈጣን መላሽ ኮድ (QR Code) እንዲኖረው ይደረጋል።
ይህም ደረሰኙ ህጋዊ መሆኑን በገዢውም ሆነ በግብር ሰብሳቢው አካል በቀላሉ ለማረጋገጥ የሚያስችል ሲሆን ታክስ ከፋዮች ለሚያደርጉት ማንኛውም ሽያጭ የተመዘገበ የኤሌክትሮኒክ ደረሰኝ የመስጠት ግዴታ ተጥሎባቸዋል።
ደረሰኞች በኢሜይል ወይም በአጭር የጽሑፍ መልእክት ለገዢው በዲጂታል አማራጮች እንዲደርሱ የሚደረግ ሲሆን የኢንተርኔት ግንኙነት በማይኖርበት ጊዜ ግብይቶች እንዳይስተጓጎሉ "ከመስመር ውጭ" (Offline) የሚሰራ አሠራር ተዘርግቷል።
ሚኒስቴሩ በዘርፉ የሚሰማሩ ሶፍትዌር አቅራቢዎች አስተማማኝ ቴክኖሎጂ ማቅረባቸውን ለማረጋገጥ ጥብቅ ደንቦችን ያወጣ ሲሆን በዚህም መሰረት ማንኛውም የሽያጭ መመዝገቢያ ሶፍትዌር ወይም የክላውድ አገልግሎት አቅራቢ በባለስልጣኑ እውቅና ማግኘት አለበት።
አገልግሎት ሰጪዎች እስከ 50,000 የአሜሪካ ዶላር የሚደርስ የመልካም አፈጻጸም ዋስትና እንዲያስይዙ የሚጠይቀው መመርያው ሁሉም ሶፍትዌሮችም ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የደህንነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ማግኘት ይጠበቅባቸዋል።
በሌላ በኩል የባንክ፣ የሰነደ መዋለ ነዋይ ገበያ፣ የዲጂታል ክፍያ አሳላጮች እና የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪዎች ከፍተኛ የግብይት መጠን ያላቸው በመሆኑ ባለስልጣኑ ልዩ ሁኔታዎችን በመመልከት ከኤሌክትሮኒክ ደረሰኝ መመዝገቢያ ሥርዓት ጋር በቀጥታ ሳይገናኙ ደረሰኝ እንዲሰጡ ሊፈቅድ እንደሚችል በመመርያው ሰፍሯል።
ሆኖም እነዚህ ዘርፎች የተጠቃለለ የሽያጭ መረጃን ለባለስልጣኑ በየጊዜው የማሳወቅ እና የሕግ መስፈርቶችን የማሟላት ግዴታ አለባቸው።
መመሪያው ግዴታቸውን በማይወጡ ወይም ህገ-ወጥ ድርጊት በሚፈጽሙ ታክስ ከፋዮች ላይ ጥብቅ እርምጃ እንደሚወስድ ይደነግጋል።
በተለይም በሥርዓቱ የተመዘገበ ደረሰኝ አለመስጠት፣ የደረሰኝ መረጃን መቀየር፣ ከባለስልጣኑ እውቅና ውጭ መረጃን ማጥፋት፣ ስርዓቱን ያለ ፈቃድ ለሶስተኛ ወገን ማስተላለፍ እና በፍተሻ ወቅት አለመተባበር በታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 መሰረት አስተዳደራዊ ቅጣት እና እንደ ሁኔታው የወንጀል ተጠያቂነትን ያስከትላል።
በተጨማሪም ባለስልጣኑ ታክስ ከፋዮች በስርዓቱ አማካኝነት ደረሰኝ የመሰረዝ ጥያቄ የሚያቀርቡበትን ድግግሞሽ እና የግብይት መጠን የመወሰን ሥልጣን እንዳለውም ተገልጿል።
ይህ መመሪያ ሰኔ 2/2018 ዓ.ም በፍትህ ሚኒስቴር የተመዘገበ ሲሆን፣ ትግበራው በባለስልጣኑ በሚወጣው መርሐ-ግብር መሰረት በየደረጃው የሚተገበር ይሆናል።