Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ዜና

ጤና ሚኒስቴርን ጨምሮ በርካታ ተቋማት ብር ያላግባብ ወጪ ማድረጋቸው ተጋለ�

BS Bethelhem Solomon Jun 18, 2026 2 ደቂቃ ንባብ 9 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
ጤና ሚኒስቴርን ጨምሮ በርካታ ተቋማት ብር ያላግባብ ወጪ ማድረጋቸው ተጋለጠ

ለዚህ ብክነት ተጠያቂ ተብለው ከተጠቀሱት መካከል ጤና ሚኒስቴር ፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በግንባር ቀደምነት ይገኙበታል።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው 2017 በጀት ዓመት የሒሳብ ምርመራ ሪፖርት የመንግሥት ተቋማት የሒሳብ አያያዝ ሥርዓትን በመጣስ በቢሊዮን የሚቆጠር ብር ማባከናቸውን አጋለጠ።


65 ገጾች በተሰናዳው በዚህ ሰነድ በተለያዩ የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ግልጽነት የጎደለው አሠራር እና ሕገ-ወጥ የፋይናንስ እንቅስቃሴዎች መስፈናቸው በግልጽ ተመላክቷል።

እንደ ኦዲተር መሥሪያ ቤቱ ግኝት መሥሪያ ቤቶቹ የተሟላ የወጪ ማስረጃ ሳያቀርቡ 1.1 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ አድርገዋል።



ከዚህ በተጨማሪም ያለምንም ማስረጃ የተፈፀመ 35.8 ሚሊዮን ብር፣ ደንብና መመሪያን ያልተከተለ 57.8 ሚሊዮን ብር፣ እንዲሁም በብልጫና በድጋሚ ክፍያ መልክ 280.6 ሚሊዮን ብር ያለ አግባብ ወጪ መደረጉ ተረጋግጧል።



ለዚህ ብክነት ተጠያቂ ተብለው ከተጠቀሱት መካከል ጤና ሚኒስቴር 231.1 ሚሊዮን ብር፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን 23 ሚሊዮን ብር እና የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ 10 ሚሊዮን ብር በላይ በማውጣት በግንባር ቀደምነት ይገኙበታል።

በሌላ በኩል የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሒሳብ አያያዝ መመሪያን በመጣስ 138 መሥሪያ ቤቶች እና 18 ቅርንጫፎች በወቅቱ ያልተወራረደ 16.3 ቢሊዮን ብር የሚገመት ተሰብሳቢ ሂሳብ መኖሩ በሪፖርቱ ተጋልጧል።




በሕግ አግባብ ለሥራ ማስኬጃ ወይም ለውሎ አበል የተሰጠ ቅድሚያ ክፍያ በሰባት ቀናት ውስጥ መወራረድ እንዳለበት ቢደነግግም ተቋማቱ ይህን ደንብ በመጣሳቸው ከፍተኛ ገንዘብ ለዓመታት ተይዞ እንዲቆይ ሆኗል።




ከዚህ ተሰብሳቢ ሂሳብ ውስጥ 4.6 ቢሊዮን ብር ከአንድ ወር እስከ አንድ ዓመት፣ 6.6 ቢሊዮን ብር ከአንድ እስከ አምስት ዓመት፣ እና 4.8 ቢሊዮን ብር ከአምስት እስከ አስር ዓመት በላይ የቆዩ ናቸው። በዚህም የጤና ሚኒስቴር 3.4 ቢሊዮን ብር በመያዝ ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል።


Advertisement
Your ad could be here — contact us

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት 2016 እና ከዚያ በፊት ባሉት በጀት ዓመታትም በተደረጉ ኦዲቶች ከህግ ውጭ የተፈጸሙ ክፍያዎች ተመላሽ እንዲደረጉ ቢታዘዝም ውጤታማነቱ ዝቅተኛ ሆኖ ተገኝቷል።



በወቅቱ ከተጠየቀው 21.5 ቢሊዮን ብር ውስጥ ተመላሽ ሊደረግ የቻለው 31 በመቶው ወይም 6.6 ቢሊዮን ብር ብቻ ነው። ወደ 15 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ እስካሁን ለመንግሥት ካዝና አልተመለሰም።



በተመሳሳይም 23 ሺህ ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ሙሉ በሙሉ ተመላሽ ሳይደረግ መቅረቱ የሪፖርቱ ሌላኛው አሳሳቢ ግኝት ነው።

የኦዲት ሪፖርቱ እንደሚያሳየው በተለያዩ የጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች እና ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ የሒሳብ መዝረክረክ የሚታይ ሲሆን  አንዳንድ ተቋማት በተሰጠው አስተያየት መሠረት የወሰዱትን የማስተካከያ እርምጃ ተከትሎ የገንዘብ ተመላሽ ማድረግ ችለዋል።



ለዚህም በምሳሌነት የቃሊቲ ጉምሩክ ቅርንጫፍ 3.2 ቢሊዮን ብር፣ የኮምቦልቻ ጉምሩክ 800 ሚሊዮን ብር በላይ፣ እና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ 120.7 ሚሊዮን ብር መመለሳቸው በሪፖርቱ እንደ መልካም ተሞክሮ ተነስቷል።


የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የመንግሥት እና የሕዝብ ሀብት በግዴለሽነት መባከኑን በማውገዝ፣ እስካሁን ተመላሽ ያልተደረገው 15 ቢሊዮን ብር በአስቸኳይ ወደ መንግሥት ካዝና እንዲገባ ጥብቅ ማሳሰቢያ ሰጥቷል።


መሥሪያ ቤቶቹ በሕግ አግባብ ተጠያቂ እንዲሆኑ ያልተወራረደ ሂሳብ በአስቸኳይ እንዲወራረድ እና ሊሰበሰብ የማይችለው ደግሞ ከመዝገብ እንዲሰረዝ ኦዲተሩ አሳስቧል።

BS
ስለ ጸሐፊው

Bethelhem Solomon

11 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።