Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
አስተያየት

የኑሮ ውድነቱ መንስኤ ነጻ ገበያ ወይስ የዶላር ጭማሪ?

SM Samuel Mulgeta Jun 10, 2026 Updated 3h ago 2 ደቂቃ ንባብ 140 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
የኑሮ ውድነቱ መንስኤ ነጻ ገበያ ወይስ የዶላር ጭማሪ?

በቤተልሄም ሰለሞን! 

 

ኢትዮጵያ በገበያ ላይ የተመሠረተ ነፃ የንግድ ሥርዓትን መከተሏን ተከትሎ አንዳንድ ነጋዴዎች በሸማቹ ማኅበረሰብ ላይ የተጋነነና ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እያደረጉ ቀጥለዋል።

Advertisement
Your ad could be here — contact us


መንግሥት ገበያውን ለማረጋጋት የተለያዩ የክትትል ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ቢገልጽም በተግባር ግን የሸቀጦች ዋጋ ከቀን ወደ ቀን እያሻቀበ ይገኛል።



በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ገበያውን ለማረጋጋት የእሁድ ገበያ አማራጮችን በማስፋፋት ነጋዴዎች የዋጋ ዝርዝር እንዲለጥፉና ሸማቹ ከተለጠፈው ዋጋ በላይ እንዳይገዛ የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋቱ በተደጋጋሚ ቢገለጽም በተጨባጭ በገበያው ላይ ያለው የምግብ የመጠጥና የሌሎች መሠረታዊ ቁሶች ዋጋ ባለበት ከመቆም ይልቅ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ ነው።



ቀደም ብሎ ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ተመንን ለገበያ መተውን ጨምሮ ሰፊ የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ማድረጓ የሚታወስ ሲሆን ይህ የነፃ ገበያ ሥርዓት በረጅም ጊዜ ሂደት ለሀገር ውስጥ ምርት ዕድገትና ለውጭ ኢንቨስትመንት መሳብ ጠቃሚ ቢሆንም በቀጥታ የኑሮ ውድነትን በማስከተል ተራው ሕዝብ ላይ ከፍተኛ የገንዘብ እጥረትና የኑሮ ጫና ፈጥሯል።


ነገር ግን ነጋዴዎች ለዚህ ተከታታይ የዋጋ ጭማሪ እንደ ምክንያት የሚያቀርቡት የውጭ ምንዛሬ (የዶላር) ተመን መጨመርንና የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያን መሆኑ ይታወቃል።

 



ይሁን እንጂ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ምንም እንኳን የዶላርና የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ መኖሩ እውነት ቢሆንም ነጋዴው በምርቶች ላይ የሚያደርገው ጭማሪ ግን እጅግ የተጋነነና ከእውነታው የራቀ መሆኑን ይገልጻሉ።


በተጨማሪም መንግሥት በትራንስፖርት ዘርፍ ላይ የታሪፍ ማስተካከያ እንደሚያደርገው ሁሉ ሀገሪቱ የነፃ ገበያ ሥርዓት የምትከተል ቢሆንም እንኳ በመሠረታዊ ሸቀጦችና ምርቶች ዋጋ ላይ ጣልቃ በመግባት ማስተካከያ ማድረግ አለባት ሲሉ ይመክራሉ።



ከገበያው መዋቅራዊ ችግር ውስጥ በተደጋጋሚ ቅሬታ የሚያስነሳው ጉዳይ ነጋዴዎች በማኅበረሰቡ ላይ ዋጋ ለመጨመር ከሚጠቀሙባቸው ምክንያቶች ውስጥ ለምሳሌ የዶላር መረጋጋት ወይም የዓለም አቀፍ ገበያ መውረድ ቢስተካከሉ እንኳ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የዕቃዎቹ ዋጋ ወደነበረበት ሲመለስ አለመታየቱ ነው።


ይህም ማለት ነጋዴዎች የዶላርና የነዳጅ ዋጋ መጠነኛ ጭማሪ ሲያሳይ የሸቀጦችን ዋጋ ወዲያውኑ እና በተጋነነ ሁኔታ የሚያሻቅቡ ቢሆንም ወጪዎች ቀንሰው ገበያው ሲረጋጋ ግን ዋጋን ፈጥኖ ለመቀነስ ፈቃደኛ የማይሆኑበትና ባለበት እንዲቀጥል የሚያደርጉበት አዝማሚያ በስፋት መታየቱ ነው።


ይህ ችግር በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ ይበልጥ የከፋ የሆነው ሸማቹ እውነተኛውን የገበያ መረጃ ማግኘት ባለመቻላቸው እና ጥቂት ነጋዴዎች መሠረታዊ ሸቀጦችን በብቸኝነት የመቆጣጠርና የመወሰን አቅም ስላላቸው በመሆኑ መንግሥት በነፃ ገበያ ስም የሚፈጸመውን ይህንን ምክንያታዊ ያልሆነ የትርፍ ፍላጎት በሕግና በቁጥጥር ሊገታው እንደሚገባ ባለሙያዎቹ ይመክራሉ።



በተጨማሪም የሚመለከተው የመንግሥት አካል ይህንን አሠራር ተከታትሎ ጥብቅ እርምጃ ካልወሰደ የኅብረተሰቡ የመግዛት አቅም ሙሉ በሙሉ እየተዳከመ በመሄድ ለከፍተኛ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንደሚጋለጥም ያስጠነቅቃሉ።

SM
ስለ ጸሐፊው

Samuel Mulgeta

53 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።